Friday, September 16, 2011

የኢጣልያ ምርኮኞችና ስለ እነሱ የተደረገ ስምምነት


  • Error loading feed data.

የኢጣልያ ምርኮኞችና ስለ እነሱ የተደረገ ስምምነት

E-mailPrintPDF
User Rating: / 2 http://www.ethiopianreporter.com/pre-rep/index.php?option=com_content&view=article&id=1382:2010-03-03-11-42-35&catid=103:2009-11-13-13-46-23&Itemid=576
PoorBest 
ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ የተማረኩ የኢጣሊያ ጦር ምርኮኞች እንዳይገደሉ፤ ወይም ያለወገን በሆነ ዓይነት ሠራዊታቸው እንዳያጉላላቸው አወጁ፡፡ ወደ መናገሻ ከተማቸው ዙሪያ አምጥተውም በምግብ እንዳይጎዱ ከምሪት አስቀመጧቸው፡፡ በተቻላቸው መጠንም የታረዘውን አለበሱት፡፡ በኢጣልያ አገር ሠራዊታቸው በጦርነቱ ድል ከመሆኑ ይልቅ፤ ምርኮኛውን የሚገጥመው ዕድል ሽብር አመጣ፡፡

ምርኮኞቹ የዓድዋ ድል ከተገኘበት ከ (1888 ዓ.ም". የካቲት 23 ቀን አንስቶ እስከ ጥቅምት 19 ቀን 1989 ዓ.ም. ድረስ ቆይተው ከ8 ወር በኋላ ውጫሌ ላይ በ1881 ሚያዝያ 25 ቀን የተደረገው ውል ፈጽሞ መፋቁን ኢጣልያ አወቀችና የምርኮኞቹን መለቀቅ ተስማሙበት፡፡ ይህም በሰደደችው ልዩ መልዕክተኛ በሜጀር ናራዚኒ ተረጋገጠ፡፡
በአጤ ምኒሊክና በኢጣልያ መካከል አዲስ የስምምነት ውል ተደረገ፡፡

*    *    *   
አነፍናፊ አይጦች

አንዳንድ ሰዎች አይጥ ሲያዩ በጣም ይፈራሉ፡፡ የፍራቻቸውን ምክንያት ግን ከነሱ በስተቀር የሚያውቅ ያለ አይመስልም፡፡ አይጥ ከማስፈራቷና ከጉዳቷ ይልቅ ለሰው ልጅ ጥቅሟ ያመዝናልና፡፡

አይጥ ለሰው ልጆች የተለያዩ በሽታዎችን ለመፈወስ የሚያስችሉ መድኃኒቶችን ለመሞከሪያነት ለበርካታ ዓመታት እያገለገለች ትገኛለች፡፡ በቅርቡ በቤልጅግ የተደረገው ሙከራ አይጦች የበርካታ የዓለማችን አገሮች ችግር የሆነውን የተቀበረ ፈንጂ ለማምከን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው አረጋግጧል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገራችንን ጨምሮ በዓለማችን 69 ሀገሮች ከ60 ሚሊዮን በላይ የተቀበሩ ፈንጂዎች ይገኛሉ፡፡ ለዚህም በመፍትሄነት እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ ከአፍሪካ የተወሰዱት ተለቅ ተለቅ ያሉ አይጦች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው እንደሚችል የጥናት ቡድኑ ኃላፊ ዊት ጆንስ ገልፀዋል፡፡

ቀደም ሲል በተለያዩ ሀገሮች የተቀበሩ ፈንጂዎችን ለማፈላለግ ውሾች ሥራ ላይ ይውሉ እንደነበር የጠቆሙት ዊት ጂንስ፣ ለዚህ ሥራ ከውሾች ይልቅ አይጦችን ማሰልጠን ይቀላል ብለዋል፡፡ በዋነኛነት አይጦች ክብደታቸው ቀላል በመሆኑ የሚያገኙት ፈንጂ ላይ ቢወጡ እንኳን አያፈነዱትም፡፡ አይጦቹን ለዚህ ተግባር ለማራባትና ለማሳደግ የሚያስፈልገው ወጪ በጣም ርካሽ ከመሆኑም በላይ፣ በርካታ ፈንጂዎች በተቀበሩባቸው የትሮፒካል የአየር ንብረት ባላቸው አካባቢዎች መኖር የሚችሉ ናቸው፡፡

(ስነምግባር 2001 ዓ.ም)

*    *    *   
እቴጌ ተዋበች 

ዐፄ ቴዎድሮስ ሸዋን ሁለተኛ ድል አድርገው ሹመቱን በኋላ ለከዷቸው አቶ በዛብኽ መርቀው ወደ በጌምድር እንደ ተመለሱ የሚወዷቸው ባለቤታቸው ክፉውንና ደጉን መከራውንና ደስታውን ሲካፈሏቸው የኖሩት ይልቁንም በተናደዱና በተበሳጩ ጊዜ መክረው የሚያበርዷቸውና የሚያጽናኗቸው እቴጌ ተዋበች በጽኑ ሕመም ታመው ወደቁ፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስም ያየር መለወጥ የሚያሽል መስሏቸው ወደ ወረ ይመኑ አመጧቸው፡፡ ነገር ግን ለሰው ተወስኖ ከተሰጠው ዕድሜ ካለቀ በኋላ ያየር መለወጥ የሐኪም ዕውቀት የዘመድም ብዛት የዘርም ታላቅነት ሊያድን አይችልምና ሞቱ፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስም ሬሳቸውን በሣጥን አድርገው ወደ ግሼን ለመቅበር ተጓዙ፡፡

እቴጌ ተዋበች ዐፄ ቴዎድሮስን ገና ልጅ ካሳ ሲባል ካገቧቸው አንስቶ ሞት እስኪለያያቸው ድረስ ካገጠባቸው አልተለዩም፡፡ ዕድላቸውም ከባላቸው ጋር የተያያዘ በመሆኑ ዐፄ ቴዎድሮስ ካያታቸው ከእቴጌ መነን ወይም ካባታቸው ከራስ ዐሊ በተዋጉ ጊዜ ላባታቸውና ላያታቸው አድልተው ካፄ ቴዎድሮስ አልተለዩም፡፡ ከዚህ ቀደም ዳዊት ለመንግሥቱ ሲል ከጉልበቱ ከወጣው ልጁ ከአቤሴሎም ጋር ተዋግቷል፡፡ ዐፄ ዮሐንስም ለመንገሥ ዐፄ ተክለ ጊዮርጊስን ወግተው ከማረኩ በኋላ ያለርኅራኄ አስረው ለሞት ሲያደርሷቸው የእኅታቸው ባል መሆናቸውን እግምት ውስጥ አግብተው ሊያመዛዝኑት እንዳልቻሉ እንደዚሁም እቴጌ ተዋበች የባላቸው ክብር የራሳቸው በመሆኑ ካባት ከናታቸው ክብር አብልጠው ለባላቸው ያደሉ ነበር፡፡

(ተክል ጻድቅ መኩሪያ፣ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣1961)

*    *    *   
የቄሱ ትንቢት 

"ምነው አባ" ለምንድነው እንደዚህ አፍጥጠው ፊቴን የሚያዩት?" በማለት የሰባት ዓመቷ ሜሪ ሮዝ ጆሲፊን የወደፊት ዕድል የተደነቁት ኮከብ ቆጣሪ ቄስ "ይህ የማይታመን ነው" በማለት አጉረመረሙ፡፡ "ቢሆንም ኮከቧ የሚተነብየውን ልነግራት ይገባል" አሉና ለጆሲፊን "የፈረንሳይ ንግሥተ ነገሥት ተብለሽ ዘውድ ትጭኛለሽ፤ ከባልሽም ጎን በዙፋን ላይ ትቀመጫለሽ" አሏት፡፡

እንዲህ አይነቱን ትንበያ ለማመን በርግጥ አዳጋች ነበር፡፡ ምክንያቱም ጆሲፊን ገረድ ነበረች፡፡ አንዲት ገረድ የፈረንሳይ ንግሥተ ነገሥት ለመሆን እንዴትስ ይቻላታል? ጆሲፊን የኮከብ ቆጣሪውን ትንበያ ትርጉም ለመገንዘብ በጣም ጨቅላ ነበረች፡፡ እናትየዋም ኮከብ ቆጣሪው የተናገሩትን ማመን አልቻለችም፡፡ ኮከብ ቆጣሪው ግን በርግጠኝነት "የኔ ጥረት አንቺን ማስደሰት ወይንም አንቺን ማጭበርበር አይደለም፡፡ በትንበያዬ ብትከፊ ባትከፊ ደንታ የለኝም፡፡ የምናገረው እውነቴን ነው፡፡ የምገልፅልሽ ልደርስበት የቻልኩትን ሀቅ ነው፡፡ ልጅሽ ንግሥት ትሆናለች፡፡ ይሁንና እስከሕይወቷ ፍጻሜ ንግሥት ሆና አትቆይም" አሉ፡፡

ሉዊስ አስራ ስድስተኛ መላውን ፈረንሳይ አሸንፈው የቦርቦ ሥርወ መንግሥት በፈረንሳይ ይቀጥል ዘንድ ከሚወዷትና ከቆንጆዋ ሚስታቸው ከንግሥት ሜሪ አንቶኔቲ ወንድ ልጅ ወለዱ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፈረንሳይ የባህር ማዶ አስተዳደር ሥር የምትተዳደረውና በምዕራብ ኢንዲስ የምትገኘው የማርቲኒኩዊ ደሴት መስፍን የቤት ሠራተኛውን አግብቶ ጆሲፊን ተወለደች፡፡ በኮከብ ቆጣሪው ቄስ ትንበያ መሰረት የንጉሱ የሉዊስ የመጀመሪያ ልጅ ጆሲፊንን አግብቶ ወደዙፋኑ ይዟት ይወጣል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ትንቢት ለጆሲፊን አባት የማይታመን ፌዝ ነበር፡፡ ጆሲፊን ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ አባቷ አሌክሳንደር ቤዮሀርኔስ ለተባለ የፈረንሳይ መስፍን ዳሯት፡፡ ከመስፍኑም ወንድና ሴት ልጆች ወለደች፣ የጆሴፊን ሕይወት ግን በዚህ አልተጠናቀቀም፣ ብዙ ታሪኮች ካለፉ በኋላ የፈረንሳዩ ንጉሠ ነገሥት ናፖሊዮንን አግብታ ንግሥት ሆናለች፡፡

(ሰለሞን ኃይለ ማርያም፣ የታላላቅ ሰዎች እውነተኛ የፍቅር ታሪክ፣1990)

*    *    *   
የቋንቋ ተማሪ ቤት ስለ መከፈቱ

ዳግማዊ ምኒልክ የአውሮጳውያንን ሥልጣኔ በአገራቸው ለማስገባት ብርቱ ምኞት ነበራቸው፡፡ ስለዚህም የቋንቋ ትምህርት ማስተማሪያ ተማሪ ቤት በዋና ከተማው በአዲስ አበባ እንዲከፈት ከወሰኑ በኋላ ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር ስለ አስተማሪ ጉዳይ ለእስክንድርያ ፓትርያርክ ለአቡኑ ቄርሎስ አንድ ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡

ይደረስ ከአቡነ ቄርሎስ፤

በአዲስ አበባ ከተማችን ትልቅ የተማሪ ቤት ማድረግ አስበናል፡፡ ይህንን አሳባችንን አቡነ ማቴዎስ ሰምተው በሀገራችን በግብጽ ብዙ የተማሩ ለማስተማር የበቁ ሰዎች አሉ ቢሉን እርስዎ ወደ አቡነ ቄርሎ ልከው እንዲሰዱልን ያድርጉ ብለን ነግረናቸው ይኸው ጽፈንልዎታልና የአቡነ ማቴዎስን ማኅተም አይተው የሚገኝልዎ እንደሆነ ያለ ትዕግሥት በስልክ በቶሎ ቢያስታውቁን እንወዳለን፡፡ ወደርስዎ መላካችን ከሌላ አገር ከማስመጣት ለትምህርትም ለሁሉም ነገር የሃይማኖት ወንድሞቻችን ቢመጡ ይሻላል ብለን ነው፡፡

ሰኔ 26 ቀን 1898 ዓ.ም. አዲስ አበባ ተፃፈ፡፡
ከዚህ በኋላ ሦስት ግብጻውያን አስተማሪዎች መጥተው በ1899 ዓ.ም በጥር ወር በአዲስ አበባ አንድ ተማሪ ቤት ተከፍቶ ማስተማር ጀመሩ፡፡ የተማሪ ቤቱ ዲሬክተር ሙሴ ሐና ቤይ ሰሊብ ይባላል፡፡

ዳግማዊ ምኒልክ የወደፊት አልጋ ወራሻቸውን ልጅ ኢያሱንና የመኳንንቱን ልጆች እነ ሊቀ መኳስ ብሩን እነ ደጃዝማች ተፈሪ መኮንንን ሌሎችንም ወደ ተማሪ ቤቱ ገብተው እንዲማሩ አደረጉ፡፡ ሌላውም ሰው የጃንሆይን አርአያ በመከተል ልጁን እየላከ ለትምህርት ያስገባ ጀመረ፡፡

ትምህርት ቤቱ የዳግማዊ ምኒልክ ተማሪ ቤት ተብሎ በስማቸው ተሰየመ፡፡ የተከፈተውም የሙሴ ኤልግ መኖሪያ በነበረው ቤት ነው፡ በኋላ ግን ይህ አሁን ያለው የተማሪ ቤቱ ሕንጻ በአቡን ሰፈር አጠገብ በጥሩ ሆኖ ተጀምሮ ተቋቋመ፡፡

(መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ 1999)

*    *    *   
የሰው ልጅ ባዶነት

አወይ የኛ ሀጢያት
የእርካታ ትኩሣት
የስሜት እንስሳት
የስም አዳምነት
የስም ሄዋንነት
የሰው ልጅ ባዶነት
መሠልጠን ተብሎ
መሠይጠን ተይዞ
እድሜ መቁጠር ቀርቶ
ህጻናትን መድፈር ትልቅ ዝና ሆኖ
አባት እንኳ ጨክኖ ከልጁ ሲጠጋ 
ለፍትወተ ስጋ
እርካታን ፍለጋ
ወንድም እህትነት
ቀርቶ እንደዘበት
አሁንማ እንስሳነት
አሁንማ እንስሳነት
ታዲያ ምን ይሰማ
ከዚህ የመረረ
ለጆሮ የሻከረ
ለወሬ የቸገረ
አይ የሰው ባዶነት
የስም አዳምነት
የስም ሔዋንነት
ለእርካታ ነጻነት
የስሜት ባርነት

(ማለዳ፣ ጂማ ዩኒቨርስቲ ኪነ ጥበባት ክከብ፣ 1993)

"""""""////""""""
ገራገር

ሰውየው ራሱን ለመግደል ባደረገው ሙከራ ላደረሰው ጉዳት ቅጣት ተጣለበት


ራሱን ለመግደል በመስኮት የተወረወረው ሩሲያዊ የ7 ዓመት ሴት ልጅ ላይ በመውደቁ ልጅቷ ላይ ላደረሰባት ጉዳት እና ቤተሰቦቿ ላወጡት የህክምና ወጪ ከ45ሺህ ብር በላይ እንዲከፍል ባገሩ ፍርድ ቤት ተፈረደበት፡፡

ሰውዬው ከዘጠነኛው ፎቅ ላይ ተወርውሮ ህፃኗ ላይ ከወደቀባት ጊዜ ጀምሮ ለወራት ያህል ሆስፒታል ስትታከም ቆይታለች፡፡ ሰውየው ለሙከራው የተገፋፋው ቤቱ ውስጥ ከፈታት ሚስቱ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ነበር፡፡

"""""""///"""""""
ቢራ ጠጪውና ሲጋራ አጫሹ ቺምፓንዚ ወደ ፀባይ ማረሚያ ተላከ


የሩሲያው ቺምፓንዚ ከለመደው ቢራ የመጠጣትና ሲጋራ የማጨስ ልምድ ለመፈወስ ወደ ፀባይ ማረሚያ ቤት በእንስሳት ጠባቂዎች አማካኝነት ተላከ፡፡

ይህ ቺምፓንዚ የሰርከስ ትርዒትን ያሳይ የነበረ ሲሆን፣ ተተናኳሽ እየሆነ በመምጣቱ ወደ እንስሳት ማቆያ እንዲዛወር ተደርጓል፡፡ የእንስሳት ማቆያውም የበርካታ ልጆች አባት ለመሆን የበቃበት ቦታ ሲሆን፣ በማርከር መሳልና ሁለት የተለያዩ ድምፆችን ማውጣትንም ተለማምዶበታል፡፡

"""""""////""""""
በ24 ሠዓት ውስጥ አንድን ባንክ ሁለት ጊዜ የዘረፈው ተያዘ


በባንክ ዝርፊያ እስር ቤት ቆይቶ የነበረው ጀርመናዊ ዘራፊ ከተፈታ በአንድ ሣምንቱ አንድን ባንክ በ24 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ በመዝረፋ ተያዘ፡፡

የፖሊስ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት የ50 ዓመቱ ዘራፊ ወደ ባንኩ በመሄድ ሽጉጡን ደግኖ "ትናንት እዚህ ነበርኩ እናም ተጨማሪ ገንዘብ ዛሬ እንደገና እፈልጋለሁ" እንዳለ ገልጸዋል፡፡

ይህ ዘራፊ ከስምንት ሺህ ብር በላይ የዘረፈ ሲሆን፣ ባንኩ ውስጥ ተገጥሞ በነበረው ካሜራ አማካኝነት በፖሊስ ታድኖ በሶስት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ተይዟል፡፡ ይህ ሰው በባንክ ዝርፊያ ምክንያት እ.ኤ.አ. በ2002 እና 2004 ዓ.ም ታሥሮ ነበር፡፡

"""""""""///"""""
ዶሮዋ ከተለመደው መጠን በላይ እንቁላል ጣለች


ቁመቱ ዘጠኝ ሴንቲ ሜትር ስፋቱ ደግሞ ሃያ አንድ ሴንቲ ሜትር የሆነ እንቁላል አንዲት ዶሮ እንደጣለች እና ይህም መጠን ከተለመደው የእንቁላል መጠን አራት እጥፍ እደሆነ የዶሮዋ ባለቤት ማርክ ኮርኒሽ ገለፁ፡፡

"ከመደንገጤ የተነሳ ዝይ በስህተት ቦታው ላይ የተገኘ መስሎኝ ነበር" ያሉት ኮርኒሽ፣ የእንቁላሉ ቅርፊት እንደ ወረቀት የሣሣ በመሆኑ መሠነጣጠቅ ጀምሯል፡፡ "ምናልባትም ቶሎ መብላት ሳይኖርብኝ አይቀርም" ብለዋል፡፡ ይህቺ ዶሮ ግፋ ቢል ለአምስተኛ ጊዜ እንቁላል የጣለች ሲሆን፣ የዓለምን ሪከርድ መስበር ግን አልቻለችም፡፡ እስከዛሬ ድረስ የተመዘገበው ትልቁ የዶሮ እንቁላል መጠን አምስት አስኳል ያለውና ቁመቱ 31 ሴንቲ ሜትር፣ ስፋቱ 22.8 ሴንቲ ሜትር፣ ክብደቱ ደግሞ ወደ 340 ግራም የሚጠጋ ነው፡፡

1 comment:

  1. I am regular visitor, how are you everybody? This article posted at this web site is actually pleasant.
    umpan tikus

    ReplyDelete