Saturday, September 10, 2011

አዲስ አበባ የተሰጣት ለመጀመሪያ ጊዜ የከተማ አስተዳደርና ስርዓት አዋጅ


አዲስ አበባ የተሰጣት ለመጀመሪያ ጊዜ የከተማ አስተዳደርና ስርዓት አዋጅ
http://addis1879.com/inde

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አዲስ አበባ ከተማ በሌሎች ስልጡን አገር ከተሞች ዉስጥ እንደሚፈፀመው ጠቅላላ ድርጊት ሁሉ ፤ ስርዓትና ደንብ እንዲኖራት በመገንዘብ ፤ የከተማው ሕዝብ ለሚያገለግለው ክፍልና ለሚገዛው ርስት የሚያስተማምን ማስረጃ አግኝቶ ቦታውን ለሕጋዊ ዋስትና እንዲያሲዘው ወይም ለመሸጥና ለመለወጥ መብት እንዲኖረው ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ቦታ ሁሉ ስፋቱ በመሃንዲስ እየተለካ ሜትር ካሬው ተረጋግጦ የተጻፈበት ካርታ በሁለት ኮፒ ተዘጋጅቶ አንዱ ለባለንብረቱ ፤ አንዱ ደግሞ በማዘጋጃ ቤቱ ርስት ክፍል እንዲቀመጥ ለማድረግ ፤ አሰራሩን ጭምር የሚያስረዳ በ32 ተራ ቁጥርና ምዕራት የተሰናዳ ከዚህ ቀጥሎ የሰፈረውን ጠቅላላ ደንብ ጥቅምት 20 ቀን 1900 ዓ.ም አውጀው ለከተማው አስተዳደር ተሰጠ፤ ይህም ቃለ አዋዲ ወይም አዋጅ ለአዲስ አበባ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጣት የአስተዳደር ህግና አዋጅ ነበር፡፡
1ኛ ክፍል
እኔ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ላገሬ ሰዎችና በተለይ ላዘዝኩላቸው ዕንግዶች መሬት እንዲገዙ በአዲስ አበባ ፈቅጃለሁ፤ የዚህን ስርዓት ግን እንዳይተላለፉ፡፡
2ኛ ክፍል
የመንግስት መሬት ሲሸጥ ዋጋው እንደቦታው ይደረጋል፡፡ መንግስት ይህንን ዋጋ ይቆርጣል፡፡
3ኛ ክፍል
ባለመሬቱ እንደ ወደደ ቦታውን ይሸጣል ይህንን ብቻ እንዳይተላለፍ፡፡
4ኛ ክፍል
የምድር ዋጋ በሜትር ካሬ ተለክቶ ነው የሚሰራ ፤ አንዱ ሜትር ርዝመትና አንዱ ሜትር  ወርድ አንድ ካሬ ተብሎ ይቆጠራል፡፡
5ኛ ክፍል
ከመንግስት ምስለኔ መሬት ለመግዛት የተስማማ ሰው መሬቱን ለክተው ስፋቱንም አስበው የምድሩ ዋጋ ይሰላል፡፡ ከዚያ በኋላ የመሃንዲስ ሥዕል ያስደርጋል፡፡
6ኛ ክፍል
የዚህን ሥዕል ግልባጭ ለመንግስት ያሳልፋል መንግስቱ በአዲስ አበባ ሥዕል እንዲያሰጨምረው በዚህ ስዕል የተሳለ መሬት በመንግስትም መዝገብ የተጻፈው ያዲስ አበባ ከተማ ካዳስትር ይባላል፡፡
7ኛ ክፍል
ወስን ለመወስን ዋጋ ለማሰቆረጥ ስፋት ለማስለካት ስዕል ለማሳል የሁለት መሐንዲሶች ስራ ነው፡፡ ከነዚህ ከሁለቱ መሐንዲሶች አንዱ የመንግስት መሃንዲስ ሁለቱም ቢሆኑ መልካም ነው፡፡ መሃንዲሶቹ የሠሩትን ስራ ያትማሉ ፤ የመሃንዲሶቹን የስራቸውን ዋጋ መንግስት ነው የሚቆርጠው፡፡
8ኛ ክፍል
የመንግስት መሬት ሲሸጥ መሃንዲሱን ዋጋ ገዢ ነው የሚከፍለው የሌላ ሰው መሬት ሰሆን ሻጭና ገዢ ለዚህ ነገር ይስማማሉ፡፡
9ኛ ክፍል
የምድርን ዋጋ ለመንግስት ምስለኔ ይሰጣል ፤ መሬት ቶሎ እንዲሸጥ ምንግስት ለገዢዎች ፈቃድ ይሰጣል ዋጋ ቀስ ብለው እንዲሰጡ፡፡ ነገር ግን ወሰን ይደረጋል ዋጋ እስኪሞላ ድረስ፡፡ ዋጋ ሳይሞላ ወሰን ያለፈ እንደሆነ መንግስት የወደደ እንደሆን መሬቱን ይወስድና ለባለቤቱ የከፈለውን ገንዘብ ያለወለድ ይመልስለታል፡፡
10ኛ ክፍል
መሬት ሲገዛ መንግስት ለገዢው ወረቀት የሰጣል ፤ መሬት ጉዳዩን እንዲሠራ ከዚህ ከተጻፈ ሥራት እንዳይተላለፍ እንጂ ፤ የርስቱን የምስክር ወረቀት አይቀበልም የገዛውን መሬት ዋጋ እስከሞላ ድረስ የዚህንም የተጻፈውን ሥራት እያደረገ፡፡
11ኛ ክፍል
መንግስት የሚሰጠው የርስት ወረቀት በመዝገብ ይገለበጣል የሚጻፍበት ነገር ይህ ነው፡፡ 1ኛ/ ኑሜሮ 2ኛ/ የሻጭ ስም 3ኛ/ የገዢ ስም 4ኛ/ የመሬቱ ስፋትና ያለበት ነገር 5ኛ/ የመሬት ወሰን 6ኛ/ የጎረቤቶቹ ስም 7ኛ/ የአምባ ስም 8ኛ/ የመሬት ዋጋ 9ኛ/ የመሸጫ ቀንና ዓመተ ምሕረት ናችው፡፡
12ኛ ክፍል
የርስት ወረቀት በመንግስት ማህተም ይታተማል፡፡ የዚህ ማኅተም ዋጋ 10 ብር ነው፡፡ ከዚሀ በላይ እንደመሬቱ ዋጋ ከመቶ አንድ ይከፍላል፡፡
13ኛ ክፍል
ሰው ለሰው መሬት ሲሸጥ የመሬቱ ወረቀት በመንግስት ምስለኔ ላይ ይደረግና በሁለት የታወቁ እማኞች ፊት እነዚህ እማኞች ወረቀቱን ያትማሉ፡፡
14ኛ ክፍል
ሰው ለሰው መሬት ሲሸጥ የመሸጫ ወረቀት በመንግስት ላይ ይጻፍና በመንግስተ መኅተም ይታተማል በ12ኛ ክፍል እንደተባለው 10 ብር ይከፍላል ከዚያ በላይ እንደመሬቱ ዋጋ ከመቶ አንድ ይከፍላል፡፡
15ኛ ክፍል
ወንጀል የተገኘ እንደሆነ ማለት ገዢውና ሻጭ በመንግስት ፊት አብለው ዋጋ የነገሩ እንደሆነ፡፡ ገዢው ተበይኖበት ለመንግስት የሚደርሰውን ግብር አራት እጥፍ ይከፍላል ፤ ሻጭም እማኞችም የገዢው ዋስ ይሆናሉ፡፡ ወንጀል ከተደረገ ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፤ ወንጀለኞቹ ተበይኖባቸው አይቀጡም፡፡
16ኛ ክፍል
በተለይ የተፈቀደለትም ዕንግዳና የዕንግዳ ኩባንያ ከአሥር ሔክታር በላይ እንዳይገዛ ተከልክሏል ፤ መንግስት ግን የወደደ እንደሆነ ይፈቅዳል፡፡ ተላላፊዎቹ በብርቱ ቅጣት ይቀጣሉ ፤ ደግሞ መንግት የተገዛውን ይወስዳል፡፡ የተገዛበትን ዋጋ እየከፈለ፡፡
17ኛ ክፍል
ይህ አዋጅ ከወጣ በኋላ እስከ 25 ዓመት ድረስ መንግስት የተገዛ መሬት በበለጠ ዋጋ የተሸጠ እንደሆነ ሻጩ የትርፉን ሲሶ ለመንግስት ይሰጣል፡፡ ከተባለው ከ10 ብር በቀር ፤ ወንጀለኞቹ በአሥራ አምስቱ ክፍል እንደተባለው ይቀጣሉ፡፡
18ኛ ክፍል
ሙሉ ዋጋ ለመንግስት ሳይከፍሉ መሬቱ የተሸጠ እንደሆነ ገዢ ሻጭ እርስ በርሳቸው በመንግስት ላይ ይባባላሉ፡፡ የቀረውን ዋጋ ገዢው ለመንግስት ቶሎ እንዲከፍል ወይም ገዢው ከመንግስት ጋራ ተስማምተው እንደነበር በመሬቱ ወረቀት ይህ ነገር ይጻፋል፡፡
19ኛ ክፍል
የመንግስት ዕዳ ስለመሬት ዋጋና ፤ ስለ መሬት ግብር ከሁሉ በፊት ይከፈላል የተረፈው ለወራሾች ይሰጣል፡፡
20ኛ ክፍል
የመሬት ሙሉ ዋጋ ሲከፈል ወረቀቱም እንደ ስራት ሲደረግ ባለቤቱ መሬቱን እንደወደደ ያደርጋል፡፡ ለወራሾቹ አሳልፎ ይሰጣል፤ ያሳግደዋል ፤ ገንዘብ እንዲበደር ሁሉንም ወይም ዕኩሌታውን እንደወደደ ይሸጣል ፤ ነገር ግን ስለ ከተማ ነዋሪዎች ጤና ከአራት መቶ ሜትር ካሬ እንዳያንስ ማለት ሃያ ሜትር ርዝመት ሃያ ሜትር ወርድ ያህል ነው፡፡
21ኛ ክፍል
ዛሬ ያለው ርስት ስፋቱ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በኋዋላ ግን እንዳይከፈል ተከልክሉዋል፡፡ በዚህ በተጻፈው ስራት ያልሆነ እንደሆነ፡፡
22ኛ ክፍል
ለመሬቱ ሙሉ ዋጋ ሳይከፍል የሞተ እንደሆነ የቀረዉን ዋጋ ወራሾች ቶሎ ይከፍላሉ ፤ ወይም አውራሽ ከመንግስት ጋር ተስማምቶ እንደነበረው እምቢ ያሉ እንደሆነ መንግስት መሬቱን ይወስዳል ፤ በ9ኛው ክፍል እንደተባለው በቦታው ላይ ቤት ተሰርቶበት እንደሆነ ቤቱንና መሬቱን ፤ ሽጠው ያውራሽን ዕዳ ከፍለው የተረፈው ለወራሾች የሰጠል፡፡
23ኛ ክፍል
ወራሾች የግድ የሆነባቸው እንደሆነ ርስታቸውን ለመካፈል ከመንግስት ያሰፈቅዳሉ ፤ ርስታቸውን ከ400 ሜትር ካሬ እንዳያሳንሱ፡፡
24ኛ ክፍል
ወራሾች ከደረሳቸው ርስት እንደዋጋው ከመቶ ሁለት ለመንግስት ይከፍላሉ፡፡
25ኛ ክፍል
ስለ ከተማ ደህንነት መንግስት ከባለ መሬቶቹ ቦታቸውን ወይም ዕኩሌታውን መግዛት የፈቀደ እንደሆነ ፤ በቦታውም ውስጥ ቤት ቢኖር ባለቤቱ ለመንግስት በግድ ይሸጣል ፤ የቤት ዋጋ አዋቂዎች እንደገመቱት መንግስት ይከፍላል፡፡
26ኛ ክፍል
ስለ ትንሽ ነገር የሆነ እንደሆነ ከሁለት ሜትር ወርድ የሚበልጥ ያስፈለገ እንደሆነ፡፡ መንግስቱ እንደሸጠ ቁጥር ዋጋ ይከፍላል ፤ ቁመቱ ምንስ ረዥም ቢሆን አሥር ዓመት ያለፈ እንደሆነ ፤ መንግስት መሬት ከተሰጠ ግን ለሥራው የሚያስፈልውን መሬት ዋጋውን እንደተገመተ ይከፍላል፡፡
27ኛ ክፍል
ነገር ግን ቤት እንዳለ መንግስት የቤቱን ዋጋ ከባለቤቱ ጋር ተስማምቶ የከፍላል፡፡ ወይም ሌላ የሚያክልን ነገር ይሰጣል፡፡

28ኛ ክፍል
ዕንግዳ ባለመሬት የሞተ እንደሆነ ፤ ባገር ወራሾች ሳይኖሩት ቢቀር አንድም ቆንሲል ሳይኖረው መንግስት ቦታዉን ያከራያልና ፤ ኪራዩን ይቀበላል እውነተኛ ወራሾች በመጡ ቀን መንግስት የተቀበለውን የርስታቸውን ኪራይ ይከፍላቸዋል፡፡ ከዚህም ገንዘብ ለራሱ የሚያሰቀረው ይህ ነው 1ኛ/ የተወራሽ ለመንግስት ያለበትን ዕዳ 2ኛ/ ቦታ ለማስበጀት የተከፈለውን ገንዘብ ፤ 3ኛ/ በ25ኛው ክፍል እንደተባለው በመቶ ሁለት እንደ ቦታው ዋጋ፡፡
29ኛ ክፍል
ሠላሣ ዓመት ያለፈ እንደሆነ ርስቱ ለመንግስት ይገባል፡፡
30ኛ ክፍል
 ያለወራሽ የሞተ ሰው ርስቱ ወደ መንግስት የገባል፡፡
31ኛ ክፍል
በርስት ነገር ክርክር የተነሳ እንደሆነ እንዳገሩ ሥራት ይፈረዳል፡፡ ሥራት ያነሰ እንደሆነ ዳኛው የናፖሊዮንን ሕግ ይጠየቃል፡፡
32ኛ ክፍል
ይህ ሥርዓት ተጽፎ ወረቀቱ በከተማ ይሰቀላል፡፡
ተጻፈ ጥቅምት 20 ቀን 1900 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment