‹የኢትዮጵያ አባት› የሚለውን ስም ያተረፉት እምዬ ምኒልክ በስልጣን ዘመናችው የሚያዳርጉአቸው አብዛኛዎቹ ነገሮች ላይ የየዋህነት፤ የደግነት፤ ባህርይ ይታይባቸው ነበር፡፡ ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት የተጿጿፏቸው ደብደቤዎች ትልቅ ምስክር ናቸው፡፡ የሥልጣኔ መሠረት የሆኑት እምዬ ምኒልክን በተመለከተ የተለያዩ የባህር ማዶ ፀሐፊዎች ደግነትን ከርህራሄ ያቀናጁ መሪ ነበሩ ሲሉ ፅፈዋል፡፡ በእርግጥም በሃገራቸው ጉዳይ የሚመጣባቸውን ማናቸውንም ነገር በግንባር ቀደምትነት የሚመልሱት አጤ ምኒልክ ለወገኖቻቸው ግን አዛኝ፣ አንድ አዋጅ ሲያወጡ ‹ይሄ አዋጅ ሕዝቤ ይጎዳው ይሆን?› ብለው የሚጨነቁ ነበሩ፡፡ ለዚህም ሕዝቡ ‹እምዬ› የሚለውን ከስማቸው ፊት አስቀድሞ መጥራትን ጀመረ፡፡ ድሮ በዚያን ዘመን እምዬ ምኒልክ የተጿጿፏቸው ደብደቤዎች ዛሬም በዚህ ዘመን፤ ዘመን ተሻግረው ብዙ መልዕክት የሚያስተላልፉ ናቸውና ለዛሬ ምርጥ ናቸው ያልናቸውን 10 ደብዳቤዎቻቸውን እንዲህ አቅርበናቸዋል፡፡
1/ ይድረስ ከራስ ወልዴ
የእነ አዛዥ ወልደ ፃዲቅ ሰበሬ የሚባለውን ቦታ /የአፋር/ የራስ ወልዴ /ኦሮሞዎች/ መቱት፡፡ አምስት /የአፋር ሰዎች/ ሞቱ፡፡ አራት በረት ከብት ተዘረፈ፡፡ ከዚህ ቀደም ዳንዶ ላይ የጨረስነውም ነገር ሁለተኛ እንዲህ ተደረገ ብሎ ለካብኝ፡፡ ይህ ነገር አውነት እንደሆነ እጅግ ክፉ ነገር ነው፡፡ አሁንም የተዘረፈው ከብት ይመለስ፡፡ የሞተውንም /የአፋር ሰው/ ጉማውን አስከፍል፡፡ ከእንግዲህ የአንተ ሰው አገር አጠፋ፤ ሰው ገደለ፣ ከብት ዘረፈ ያሉኝ አንደሆነ አይሆንም፡፡ ከድሃው አልጣላም ካንተ ነው፡፡
ነሐሴ 13 ቀን 1898 ዓ/ም አዲስ አበባ ተፃፈ
2/ ይድረስ ከደጃዝማች ይልማ
የችሎትህን ነገር ጦም የሆነ እንደሆነ እስከአምስት ሰዓት ድረስ፤ ፍስክ የሆነ እንደሆነ እስከአራት ሰዓት ድረስ አስቻለህ ከዚያ በኋላ ግብር መግባት ነው፡፡ ከግብር በኋላ ሶስት ሰዓት አርፈህ ከሰባት ሰዓት ወዲያ እስከ አስር ሰዓት ድረስ የባለቆይታውን የባለጉዳዩን ሥራ መፈፀም ነው፡፡ እስከ ስድስት ሰዓት፣ እስከ ሰባት ሰዓት ችሎት ማድረግማ ጀሮስ መቼ ይሰማል፤ ልቦናስ መቼ ይስተውላል፡፡ ነገሩስ መቼ ያምራል፡፡ ይህን ለምን አገኘኸው፡፡ እኔ ይህን ሕግ ሰርቼልሃለሁ፡፡ ከዚያ ወዲያ ቃሌን ባትሰማ አንተ ታውቃለህ፡፡ ሽማግሌም የሆኑት ሰዎት ችሎቱ አነሰ ቢሉም ይህን ደብዳቤ አሳያቸው፡፡ ደግሞ እንደራስ መኮንን እሆናለሁ ብለህ ደርቀህ ትቀራለህ፡፡ መበሳጨትም ያመጣል፡፡
ነሐሴ 28 ቀን 1898 ዓ/ም አዲስ አበባ ተፃፈ
3/ ይድረስ ከራስ ተሰማ
ክፉ ለምጄ ልቤ ዋለለብኝ ያልከው እውነትህን ነው፡፡ ከራስ ወልደጊዮርጊስ ጋር እለት እለት በስልክ እንነጋገራለን፡፡ ይህ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ ወደአንተ አገር የሄደውን ስልክ የት ላይ ይሆን የምታገኘው፡፡ ይኸው እስካሁን አልተነጋገርንም፡፡ ያን ትንሽ ልጅ ይዤ ሄድኩ ያልከውም መልካም ነው፡፡ ፈንጣጣ ያልወጣለት ልጅና ያልተተኮሰ ሸክላ አንድ ነውና ፈንጣጣውን ተከትቦ በሌላ ጊዜ ይመጣል፡፡ ልጁ ግን አፍ እንዲለምድ ካንተ ጋር ይክረምና ኋላ ወደዚህ ይመጣል፡፡
ጳጉሜ 5 ቀን 1898 ዓ.ም አዲስ አበባ ተፃፊ
4/ ይድረስ ከአዛዥ ባደግ
የከተማውን ጉድባ የግቢው ካብ ጨርሼ ደግሞ የውጪውን ጀምሬአለሁ፡፡ ውሃውም ብዙ ምንጭ ተገኘ ብለህ ብትልክልኝ ደስ አለኝ፡፡ መልካም ሆነ፡፡ ዳናሚት ያልከውን ግን ለዚያ አገር ድንጋይ ባሩድ ይሻላል ብዬ ይኸው ሁለት ቁና ባሩድ ከነገመዱ ሰድጄልሃለሁ፡፡ የስልኩም ስራ ተከምባታ የሚጋጠመው ብቻ አይደለም፡፡ ደግሞ ወደ ሲዳማ የሚሄደውን በዱግና በኩል ከአባይ በላይ አድርገህ ከሲዳሞ ወሰን ድረስ የምታስተክል ነህና ለዚህም የሚሆን የስልክ እንጨት እንድታሰናዳ ይሁን፡፡
መስከረም 13ቀን 1899 ዓ.ም አዲስ አበባ ተፃፈ
5/ ይድረስ ለአቶ በሻህ
ለሆቴል ቤት የሚሆን አስር እንጨት ቁመቱ አስራ ሁለት ሜትር፤ ስፋቱ አስራ ሶስት ሳንቲ ውፍረቱ ዘጠኝ ሳንቲ፣ ስድስት እንጨት፤ ቁመቱ አስር ሜትር ስፋቱ አስራ ሶስት ሳንቲ ውፍረቱ ዘጠኝ ሳንቲ፣ አስራ አምስት እንጨት፤ ቁመቱ ስምንት ሜትር ተኩል ስፋቱ አስራ ሶስት ሳንቲ ውፍረቱ ዘጠኝ ሳንቲ፤ ይህን እፈልጋለሁና የቤተክርስቲያኑን እንጨት ሲያደርስልህ ይህንን እንድትሰራ፡፡ ነገሩን ታውቀው ብዬ ነው፡፡ ደግሞም ከዚህ ቀደም የተሰራ ለቤተክርስቲያኑ የማይሆን ለፃፍኩልህ የሚሆን እንጨት የተገኘ እንደሆነ ቁመቱና ስፋቱን እየላክህ ለዚሁ ማድረግ ነው፡፡
ህዳር 21 ቀን 1899 ዓ.ም አዲስ አበባ ተፃፈ
6/ ይድረስ ከወህኒ አዛዥ ወልደ ፃድቅ
ለባላምባራስ ዘለቀ ከገደራ ስልሳ ስምንት ገባር የጠሚትን ሁዳድ ከነአትክልቱ ከነጥማዱ ሰጥቼዋለሁና አንተ ከአስራት በቀር በምንም በምን አትድረስ፡፡ አስራቱ ግን የኔ ነውና እንደዚህ ቀደሙ እየተሰበሰበ እዚያው ከእኛው ጎተራ እንዲገባ ይሁን፡፡
ታህሳስ 1 ቀን 1899 ዓ.ም ተፃፈ
7/ ይድረስ ከወይዘሮ አፀደ
ግራዝማች አደራ የሚባል የአባትሽ አሽከር የደጃዝማች አስፋውን ገንዘብ ደብቋል ቢሉኝ አስሬዋለሁ፡፡ አሁንም እውነት የአባትሽን ገንዘብ መደበቁን ልብሽ የሚያውቀው እንደሆነ መርምሬ ገንዘቡን እንዳስወጣልሽ እውነቱን ነገር ላኪብኝ፡፡ ገንዘብ መደበቁን አላውቅም የምትይ እንደሆነ ግን ሁሉንም ነገር ላኩብኝ፡፡
ሚያዝያ 26 ቀን 1899 ዓ.ም አዲስ አበባ ተፃፈ
8/ ይድረስ ከደጃዝማች ባልቻ
ይህ ግራዝማች ሱድቄ የሚባል የአንተ አገልጋይ እኔ ዘንድ መጥቶ ያስታርቀኝ አለኝ፡፡ ያንተ ሰዎች እኔ ዘንድ መጥተው ያስታርቁኝ ከማለት በቀር ባንተ ክፋት ነገር ተናግረው አያውቁም፡፡ አሁንም በእውነት ከልብ ምረኸው የተወረሰውንም ገንዘቡን አገሩን መልስለት፡፡ ታርቀህ ተስማምቶ እንደወትሮው እንዲቀመጥ ይሁን፡፡ ደግሞ በተረፈ ቀኝ አዝማች ተገኝን አስታርቅ ብየዋለሁና እሱ ያስታርቅ፡፡
ሰኔ 20 ቀን 1899 ዓ.ም አዲስ አበባ ተፃፈ
9/ ይድረስ ከደጃዝማች ይልማ
ሐረርጌ ራስ መኮንን አሠርቶት የነበረውን የበሽተኛ ማስታመሚያ ሆስቢታል ቤት የፈረንሳይ መንግስት ሐኪም አስመጥቶ ያገራችንን ሕመምተኛ ሊያስታምምልን በኢትዮጽያ ልዩ መልክተኛና ባለሙሉ ስልጣን ሚኒስትር ውሌ እሎቢኮብስኪ ስለፈረንሳይ መንግስት ሪፐብሊክ ሆኖ ገዝቶታልና ይህንኑ የሆስቢታሉን ቤት የቦታውን ልኩንና መጠኑን ለክተህ የመሄጃውንም ወረቀት አፅፈህ ለሐረርጌ ለፈረንሳይ መንግስት ቆንሲል ለሙሴ ናጀር እንድትረካከብ ይሁን፡፡
ነሐሴ ቀን 1899 ዓ.ም አዲስ አበባ ተፃፈ
10/ ይድረስ ከአፈ ንጉሥ ነሲቡ
የኢትዮጵያ መንግስት የፍርድ ሚኒስትር
ሜርታት የሚባል የአርመን ሰው ከሱናፊ ጋር በገንዘብ ተጣልቼ ሳልተሳሰብ ክፈል አሉኝ ብሏልና እንደነጋዴ ስርዓት በፊት እነነጋድረስ ኃይለጊዮርጊስ ላይ እንድተሳሰብ ይሁን፡፡ ነገሩ እዚያ የላለቀላቸው እንደሆነ ግን በኋላ አንተው ዘንድ ይጨርሳሉ፡፡
መጋቢት 29 ቀን 1900 ዓ.ም አዲስ አበበ ከተማ ተፃፈ
|
No comments:
Post a Comment