67 ዓመት የሞላው የግርማዊነታቸው የ‹ሊግ ኦፍ ኔሽን› ንግግር |
ክቡር ፐሬዝዳንት
ክቡራን የመንግስታት መልዕክተኞች
በፈረንሳይ ቋንቋ ብነግራችሁ እወድ ነበር፡፡ ነገር ግን ሃሳቤን በመንፈሴ ኃይል ሁሉ ከልቤ ለመናገር የሚቻለኝ በአማርኛ ቋንቋ ስለሆነ፣ በፈረንሳይ ቋንቋ በመናገሬ የመንግስታት ማኅበር ዋና ጉባኤ ይቅርታ እንዲያደርግልኝ እለምናለሁ፡፡
እኔ ቀዳማዊ ኃይሌ ሥላሴ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት፣
የዛሬ ስምንት ወር ሃምሳ ሁለት መንግስታት የዓለምን መነግስታት ሕግ የተላለፈ የአጥቂነት ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ መደረጉን አረጋግጠው ካስታወቁ በኋላ ለሕዝቤ ይደረግለታል ብለው ቃል የገቡለትን እርዳታና የሚገባውንም ትክክለኛ ፍርድ ለመጠየቅ ዛሬ ከዚህ ቀርቤአለሁ፡፡
ለእነዚህም ለአምሳ ሁለት መንግስታት የኢትዮጵያን ሕዝብ አቤቱታ ለማቅረብ ከንጉሠ ነገስቱ የሚበልጥ ሌላ ሰው አይገኝም፡፡በዚህ ጉባኤ ያንድ መንግስት ንጉሠ ነገሥት ወይም ፐሬዝዳንት ቀርቦ ሲናገር ምናልባት ገና ዛሬ መጀመሩ ነው፡፡ ደግሞ ያንድ አገር ሕዝብ ይህን የመሰለ ሕግ ሲሰራበትና አሁንም በአጥቂው እጅ ለመውደቅ ሲደርስ የታየው በእርግጥ ዛሬ ብቻ ነው፡፡
ደግሞ አንዱ መንግስት የሌላውን መንግስት አገር በጦርነት እንዳይወስድበትና ንፁሐን የሆኑትንም የሰው ወገኖች ኃይለኛ በሆነ በጋዝ ቶክሲክ መርዝ እንዳይፈጃቸው ተብሎ በዓለም ካሉ መንግስቶች ጋር በተዋዋለው ውል በክብርና በግልጥ የሰጠውን ቃል ኪዳን ተላልፎ በጨካኝነት መሣሪያ ያንዱን ሕዝብ ዘር በቁርጥ ለማጥፋት ከዚህ ቀድሞ የተነሳና ምሳሌ የሆነ መንግስት አልታየም፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትነቴ ወደ ጄኔብ የመጣሁበት ምክንያት ለጦር ሠራዊቴ ዋና መሪ ሆኜ ራሴ ከተዋጋሁ በኋላ ከብዙ ሺህ ዘመናት በፊት ጀምሮ የቆየውን ነፃነቱን ለመጠበቅ ስለሚታገለው ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ለመከላከልና ይህንም ከፍ ያለ የተገባኝን ስራ ለመፈፀም ነው፡፡ እነዚህም የተከተሉኝ ሹማምንቶች ራሳቸው ከደረሰባቸውና ምስክር ከሆኑት ከሚያሰቅቅ ነገር በሕዝቤም ላይ ከተደረገው ስቃይ የዓለምን መንግስታት እግዚአብሔር እንዲጠብቃቸው እለምናለሁ፡፡
በጄኔብ የተሰበሰቡትና ለብዙ ሚሊዮን ሰዎች ሴቶችና ሕፃናት ሕይወት አላፊ ለሆኑት መንግስታት እንደራሴዎች በእነዚህ ፍጥረቶች የደረሰባቸውን የሞት አደጋ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰባትን እድል በዝርዝር አስረዳለሁ፡፡የኢጣልያ መንግስት ጦርነት ያደረገው በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከጦርነቱ ስፍራ በራቁት በሠላማዊ ሕዝብ ላይ በድንጋጤ ለመግደልና ዘራቸውንም ለማጥፋት አደጋ እየጣለ ወጋቸው፡፡ጦርነቱ እንደ ተጀመረ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1928 ዓ.ም በኢጣልያ አይሮፕላኖች በጦር ሠራዊቶቼ ላይ ጋዝ ላክሪሞዤን ያለበት ቦምብ ጣሉባቸው፡፡ ይህም ቦምብ እጅግ አልጎዳቸውም ነበር፡፡ ምክንያቱም ወታደሮቹ ቦምብ በወደቀ ጊዜ ጋዙን ነፋስ እስኪወስደው ድረስ መበታተኑን ስለ ዐወቁበት ነው፡፡
ከዚህ በኋላ የኢጣልያ አይሮፕላኖች ኤፒሪት የተባለውን ጋዝ መጣል ጀመሩ፡፡ በኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት ላይ ኤፒሪት ያለበት በርሜል ወደቀባቸው፣ ይኸውም ሆኖ የኤፒሪቱ ጋዝ ያደረገው ጉዳት የለም፡፡ ምክንያቱም የኤፒሪቱ ውሃ የሚያገኛቸው ወታደሮች ጥቂቶች ስለነበሩና በርሜሉ በመሬት ላይ ሲወድቅ ወታደሮቹ ሕዝቡም መርዝ ያለበት መሆኑን ስለዐወቁት ነው፡፡ የኢጣልያ የጦር ጠቅላይ ሹም መቀሌ የኢትዮጵያ ወታደሮች በከበቡ ጊዜ የኢጣልያ የጦር ሠራዊት መፈታቱን ስለ ተረዳውና ስለ ሠጋ ሌላ አይነት የኤፒሪት አጣጣል አደረገ፡፡ ይህንም አደራረግ አሁን ለዓለም ገልጦ ማስታወቅ የተገባኝ ነው፡፡
በአይሮፕላኖቹ ላይ የኤፒሪቱን ውሃ የሚረጭ መኪና ተዘጋጅቶ ሰፊ በሆነው አገር ላይ ሞትን የሚያመጣ ረቂቅ ዝናብ እንዲወርድበት ተደረገ፡፡ የኢጣልያም አይሮፕላኖች አንድ ጊዜ 9፣ 15፣ 18 እየሆኑና እየተመላለሱ የኤፒሪት ዝናብ ሳያቋርጥ እንዲወርድ አደረጉ፡፡ በጥር መጨረሻ 1928 ዓ.ም ጀምሮ በወታደሮቻችን፣ በሴቶች በልጆች፣ በከብቶችና በፈሳሽ ወንዞች በኩሬዎችና በከብት መሰማሪያዎች ቦታዎች ላይ ሳያቋርጥ ሞት የሚያመጣ ይህ ዝናብ ዘነበባቸው፡፡ ፍጡር የሆኑትን ሁሉ በፍፁም ለማጥፋት ውሃውንና ለከብት የሚሆነውንም ሳር መረዝ ብቻ ለማድረግ የኢጣልያ የጦር ሹም አይሮፕላኖቹ ይህንኑ ስራቸውን እየተመላለሱ እንዲሰሩ አደረገ፡፡ ዋና የጦርነት መሣሪያ ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡
ይኸም በረቂቅነት የሚሰራ የጭካኔ ስራ ጦርነት ከሚደረግበት ቦታ በራቁት ቦታዎች የሚገኙትን ሕዝብ አጠፋቸው፡፡ አገራቸውንም ምድረ በዳ አደረገው፡፡ አሳቡም በሚበዛው በኢትዮጵያ ግዛት ክልል ላይ ድንጋጤንና ሞትን ለመዝራት ነበር፡፡እጅግ የሚያሳዝን ነገር የሚያመጣ ይህ ብልሃት ተፈፀመበት፡፡ ሰው ከብቱም በፈፁም አለቀ፡፡ ከአይሮፕላንም የሚወርደው የሞት ዝናብ የሚነካውን ሁሉ እያሰቃየ ያባርር ነበር፡፡ ይህም የመርዝ ዝናብ የዘነበበትን ውሃ የሚጠጡ መርዙም የሚነካውን ምግብ የሚመገቡ በታላቅ ስቃይ አለቁ፡፡ በኢጣልያ ኤፒሪት ምክንያት በብዙ ሺህ የሚገመቱ ሰዎች ሞቱ፡፡ እኔም ወደ ጄኔብ ለመምጣት የቆረጥሁት የኢትዮጵያ ሕዝብ የደረሰበትን ስቃይ ለሰለጠነው ዓለም ለማስታወቅ ነው፡፡
ይህንንም የማያከራክር ምስክርነት ከእኔና ከነዚህ ከተከተሉኝ በጦርነቱ ላይ ከነበሩት ሰዎች የተሻለ ለመንግስታት ማኅበር የሚያስረዳ አይገኝም፡፡አውሮጳም ይህን ነገር እንዳለቀ አድርጎ ቢቆጥረው በራሱ የሚደርስበትን የሚጠብቀውን ይህን እድል ማሰብ ይገባዋል፡፡ይህ ሁሉ መከራ በጦር ሠራዊቴና በሕዝቤ ላይ ሲወርድበት መላክተኞቼ መንግስታት ማኅበር የሚያቀርቡት አቤቱታ ምላሽ ሳያገኝ ቀረ፡፡ መላክተኞቼም በጦርነቱ ውስጥ አልነበሩምና በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን መከራ እነሱ ያላዩት ስለ ሆኑ በሕዝቤ ላይ የተፈፀመበትን የወንጀል ስራ ለማስረዳት ራሴ ለመምጣት ቆረጥሁ፡፡በኢትዮጵያ ላይ በየጊዜው የደረሰውን ዛሬ ለተሰበሰው ለመንግስታት ማኅበር ዋና ጉባኤ ማሳሰብ የሚያስፈልግ አይደለምን?
ከሃያ ዓመት በፊት ጀምሮ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስት መንግስት አልጋ ወራሽና እንደራሴ ሆኜ በኋም ንጉሠ ነገሥት ተብዬ የሕዝቤ መሪ ሆኜ ስሰራ ላገሬ ያዲሱ ሥልጣኔ ጥቅም እንዲደርሰው በተለይም ጎረቤት ከሆኑት መንግስቶች መልካም የጉርብትና መገናኛ ለማቆም መድከሜን አላቋረጥሁም፡፡ በተለይም ከኢጣልያ መንግስት ጋር በማናቸውም ምክንያት ቢሆን ጦርነት እንዳይነሳ የሚከለክል በሁለቱ መነግስቶች መካከል የሚነሳው ክርክር በወዳጅነትና በሽምግልና ዳኞች እንዲጨረስ የሚያደርግ የሰለጠኑት ዓለም መንግሥታት ለሕዝብ ሰላም እንዲሆን መሠረት ያደረጉትን የወዳጅነት ውል በ1920 ዓ.ም ተዋዋልሁ፡፡የአስራ ሶስቱ መንግስታት ጉባኤ በመስከረም 26 ቀን 1928 ዓ.ም ባቀረበው ማስታወቂያ የደከምሁበትን ሥራ አውቆ በግልጥ ተናግሮልኛል፡፡የተናገረውም ይህ ቃል ነው፡፡
‹ኢትዮጵያ ወደ መንግስታት ማኅበር በመግባትዋ ግዛትዋ እንዳይነካባትና ነፃነትዋ እንዳይጠፋ አዲስ መተማመኛ በመስጠት አሁን ካለችበት የሥልጣኔ ደረጃ ከፍ ወዳለው እንድትደርስ መንግስታት አስበው ነበር፡፡ አሁን ባላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በ1915 ዓ.ም ይታይ የነበረው የፀጥታ ማጣትና የሽብር ኑሮ አይታይባትም፡፡ ይልቁንም አገሩ ከፍተኛው ይበልጥ አንድ ሆኗል፡፡ የዋናውም መንግስት ሥልጣን ከቀድሞው ይበልጥ ይከበራል› ይላል፡፡ ይህንም የወዳጅነት ውል የፈረመው አሳቡን ለመሸፈኛ እንዲያገለግለው ኖርዋል፡፡የኢጣልያ መንግስት በኢትዮጵያ ሽብር ለማንሳት አንዳንድ ሰው በመግፋት፣ ለዐመፀኞችም መሣሪያ በመስጠት ይህንም የመሰለ ብዙ አይነት ችግር ባያደርግብኝ ለሕዝቤ የሠራሁት ሥራ ከዚህ የበለጠ ፍሬ አፍርቶ ይጠቅም ነበር፡፡የሮማ መንግሥት ዛሬ በግልጥ ማድረግ እችላለሁ ብሎ የተነሳበትን ኢትዮጽያን በጦርነት ለመውሰድ ያሰበውን አሳብ ባለማቋረጥ ሲያዘጋጅ ኖረ:: እንዲሁም ከእኔ ጋር የፈረመው ውል ሁሉ ከልቡ አልነበረም፡፡ ይህንንም የወዳጅነት ውል የፈረመው ሃሳቡን ለመሸፈኛ እንዲያገለግለው ኖሯል፡፡
የኢጣልያ መንግስት ዛሬ በጉልበት ያገኘውን ለመስራት ከ14 ዓመት ጀምሮ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ስለዚህ በ1915 ዓ.ም ኢትዮጵያ በመንግስታት ማኅበር እንድትገባ በነገሩ መደገፍና መረዳቱ በ1920 ዓ.ም የወዳጅነት ውል መዋዋሉ ጦርነት ከሕግ የወጣ ነገር ለመሆኑ በፓሪስ ላይ የተደረገውን ውል መፈረሙ የዓለምን እምነት የሚጎዳ ስራ ለመስራት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ግን በዚህ ታላቅ ክብር በተደረገው ውል ሁሉ የታየው የነበረው በሰላም መንገድ ላይ ሆኖ ሀገሩን ወደ ስልጣኔ ለመምራት በሙሉ ልቡና በሙሉ ኃይሉ ለመስራት የጀመረውን ስራ ለመፈፀም እንዲቻለው እንደገና መተማመኛ የሚሆነው ነገር ማግኘቱ መስሎት ነበር፡፡
በህዳር ወር በ1927 ዓ.ም የተደረገው የወልወል ጠብ ለእኔ በድንገት ከሰማይ እንደወረደ መብረቅ ቁጣ ሆኖ ተሰማኝ፡፡ ኢጣልያ ጠብ እንዲነሳ መፈለጓ ግልፅ ነበር፡፡ እኔም ይህንኑ ለመንግስታት ማኅበር ማሰማቴን አልተኹም፡፡ ስለዚህ በ1920 ዓ.ም በተደረገው ውል በተፃፈው ቃል የመንግስታት ማኅበር በቆመበት መሠረት በሽማግሌ ዳኝነት በዚሁ መንገድ ነገሩ እንዲታይ ጠየቅሁ፡፡
ይኸውም በመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው የመንግስታት ማኅበር ውል መሻር አንድ ጊዜ ብቻ ሆኖ አልቀረም፡፡ የሮማ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን ፖለቲካ የሚያበረታታለት ስለሆነ በኢትዮጵያ ላይ በመጫን የተጀመረው ስራ የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢጣልያን ገዢነት እንዲቀበል ለማድረግ የማይበቃ የሆነ እንደሆነ በጦርነት አደርጋለሁ ብሎ ይዘጋጅ ጀመር፡፡ ለዚህም ጊዜ ማግኘት የሚያስፈልግ ሆነበት፡፡ ለእርቅ የተመረጡት የሽምግልና ዳኞች ስራቸውን ለመጀመር እንዳይችሉ በብዙ አይነት ተንኮል እየተደረገ በልዩ ልዩ ረገድ ነገሩ እንዲጎተት ሆነ፡፡ ይኸውም የሽምግልና ዳኞች ስራ እንዳይፈፀም ብዙ አይነት መሰናክል ተደረገበት፡፡ አንዳንዶቹ መንግስቶች ለዚሁ ለሽምግልና ዳኝነት የሚሆን ሰው ከዜጎቻቸው ውስጥ እንዳይመረጥ ለመከልከል ፈለጉ፡፡ የሽምግልናውን ዳኝነት ስራ ከተቋቋመ በኋላ ነገሩ ለኢጣልያ በመልካም መንገድ እንዲፈረድ ዳኞቹ ተጭነዋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ በከንቱ ተደከመበት፡፡ ሁለት የኢጣልያ ሰዎች የነበሩትን የሽምግልና ዳኞች በአንድ ቃል ሆነው በወልውልም ነገር ቢሆን ከዚያም በኋላ በተደረገ ነገር ቢሆን ኢትዮጵያን በአለም መንግስታት ፊት ኃላፊ የሚያደርጋት ነገር የለም ብለው ፈረጁ፡፡ይህም ፍርድ ከተፈረደ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኢጣልያ ጋር አዲስ የወዳጅነት ዘመን ይጀምራል በማለት በእርግጥ ተማምኖ ነበር፡፡ለሮማም መንግስት በእውነተኛ መንገድ ለማግኘት እጄን ዘረጋሁ፡፡
ከህዳር ወር በ1926 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 23 ቀን በ1928 ዓ.ም በየጊዜያቱ የሆነውን ነገር ሁሉ በዝርዝሩ በመስከረም 25 ቀን 1928 ዓ.ም የተሰበሰቡ የ13 መንግሥቶች ኮሚቴ ባደረገው ራፖር ለዋናው ማኅበር ጉባኤ አስታወቀ፡፡በዚሁም ራፖር ከተፃፈው የተቆረጠው ነገር በቁጥር 24፣ 25 እና 26 ብቻ የተፃፈው ቃል አሁን አስታውሳለሁ፡፡
የኢጣልያ ማስታወሻ ለምክሩ ጉባኤ የተሰጠው በነሐሴ 29 ቀን በ1928 ዓ.ም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ማስታወሻ የተሰጠው ግን የመጀመሪያው አቤቱታ በታህሳስ 5 ቀን በ1926 ዓ.ም ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ጊዜያቶች መካከል የኢጣልያ መንግስት ነገሩ በምክሩ ጉባኤ ፊት ቀርቦ እንዳይታይ ሲል በ1920 ዓ.ም በኢትዮጵያና በኢጣልያን መካከል በተደረገው ውል በተፃፈው ቃል ብቻ ነገሩ ይፈፀማል እያለ እንዲቆይ አደረገ፡፡ በዚህም ጊዜ ሁሉ በምስራቅ አፍሪቃ የኢጣልያ ወታደር እየተከታተለ ይላክ ነበር፡፡ የኢጣልያ መንግስት ወታደር የላከበት ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት ለጦርነት የሚዘጋጅ በመሆኑ ለቅኝ አገሩ የሚያሰጋው ስለሆነ ለመከላከል የሚያስፈልገው በመሆኑ ነው ብሎ ነገሩን ለምክሩ ጉባኤ ምስጢሩን ሰውሮ አመለከተ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ይልቁንም በኢጣልያ አገር በኦፊሲዬል በተነገረው የዲስኩር ቃል እንደሚታየው የኢጣልያ መንግስት ለጠብ ማሰቡ ምንም የማያጠራጥር ነው ሲል በየጊዜያቱ አስታወሰ፡፡
ጠቡ ከተነሳ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ነገሩን በሰላም ለመጨረስ ፈለገ፡፡ በመንግስታት ማኅበር ውል በተፃፈው ቃል ነገሩ እንዲታይ ጠየቀ፡፡ የኢጣልያ መንግስት ግን በ1920 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኢጣልያ መካከል በተደረገው ውል ቃል ብቻ ነገሩ እንዲታይ ስለፈቀደ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንኑ ተቀበለ፡፡ የሽምግልና ዳኞች ነገሩን በመልካም ሳይፈርዱለት ቢቀሩ እንኳ ፍርዱን በመልካም ፈቃድ እፈፅማሁ ብሎ አስታወቀ፡፡ የሽምግልና ዳኞቹ ወልወል የማን ግዛት እንደሆነ ነገሩን እንዲያዩ ኢጣልያ ሳትፈቅድ ስለቀረች ኢትዮጵያ ይሄንንም ተቀበለች፡፡ ይሄንም ነገሩ የሚመረምሩ ነፃ የሆኑ ሰዎች በአገሩ እንዲላኩ የምክር ጉባኤ ጠየቀ፡፡የምክሩ ጉባኤ በፈቀደው አይነት የቆረጠውን ምርመራ ለመቀበል የተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የኢጣልያ መንግስት በበኩሉ የወልወል ነገሩ በሽማግሌዎች ታይቶ ከላቀ በኋላ የፈቀደውን ስራ ለመስራት እንዲችል ነፃነቱን ለመጠየቅ የማመልከቻውን ዝርዝር ለምክሩ ጉባኤ አቀረበ፡፡
ኢትዮጵያ ጋር ያለውን ነገር ሁሉ ለመጨረስ በማኅበሩ ውል የተፃፈውን ቃል ለማስፈፀም ብቻ የሚበጅ ነገር የለበትም ብሎ አስረገጠ፡፡ ደግሞ ለኢጣልያ ይሄ ነገር ዋና የሕይወት ጥቅም ያለበት ስለሆነና ራሱን ለመጠበቅ ዋና መጀመሪያ የሚያስፈልገው ስለሆነ ተስፋውን በጭራሽ በኢትዮጵያ ላይ ካላነሳና የራሱን ጥቅምና ቅኝ አገሩን ለመጠበቅ የሚያስፈልገውን ለማድረግ ሙሉ ነፃነት ካላገኘ በቀር ኢጣልያ ከሁሉ ያነሰ መጀመሪያ ማድረግ የሚገባውን ስራ ማጉደል ይሆንበታል ብሎ አደላድሎ አስታወቀ፡፡
የ13ቱ መንግስታት ምክር ቤት ያቀረበው ራፖር ቃል ይህ ነው፡፡ የምክሩና ዋናውም የማኅበሩ ጉባኤ በአንድነት ሆነው ‹የኢጣልያ መንግስት የማኅበሩ ውል ቃል ማፍረሱንና አጥቂ መሆኑን› በግልጥ አስታወቀ፡፡እኔም በግድ የመጣብኝን ጦርነት ለማድረግ አለመፈለጌን በየጊዜው ከማስታወቅ አላቋረጥሁም፡፡ የምዋጋውም የሕዝቤ ነፃነቱና የኢትየጵያም ሙሉ ግዛት እንዳይነካባቸው በማለት ብቻ መሆኑና በዚሁም ጦርነት የምከላከለው የታላቅ መንግስቶች ጎረቤት የሆኑ ትንንሽ መነግስቶች ሁሉ በኃይል አገራቸውን ለመውሰድ እንዳይችል የነርሱን ጉዳይ ጭምር ነው፡፡በ1928 ዓ.ም በጥቅምት ወር ዛሬ የሚሰሙኝ 52ቱ መንግስቶች ‹አጥቂው አያሸንፍም የሕግ መንግስት እንዲኖርና እንዲፀና ከሕግ ተላልፎ በኃይል የሚሰራ ስራ እንዲፈርስ በማኅበሩ ውል የተፃፈው ቃል ሁሉ እንዲፈፀም እናደርጋለን› ብለው ቃል ሰጥተውኝ ነበር፡፡በዓለም ሁሉ አጥቂነቱ ከተፈረደበት መንግስት ሕዝቤ እንዲከላከል ያደረግሁት እምነቴን የገለጥሁት የዛሬ ስምንት ወር 52ቱ መንግስቶች የተከተሉትን ፖለቲካ እኔም ተከትዬ ነውና ይህንኑ ፖለቲካቸውን እንዳይዘነጉት አሳስባለሁ፡፡
ምንም የጦር መሣሪያዬ ከአጥቂው ያነሰ ቢሆን አይሮፕላን መድፍ ሌላም መሣሪያ የቁስለኛ ማሳከሚያ በጭራሽ ባይኖረኝ ተስፋዬ በመንግስታት ማኅበር ውል ላይ ነበር፡፡ 52ቱ መንግስቶች ከነዚሁም በዓለም የበለጡ ያሉባቸው በአንድ አጥቂ በሆነ መንግስት ብቻ ሊሸነፉ የማይቻል ነው ብዬ አስብ ነበር፡፡ በውል ኃይል ተማምኜ በአውሮጳ አንዳንድ ትንንሽ መንግስቶች እንደደረሰበቸው ሁሉ ለጦርነት አልተዘጋጀሁም ነበር፡፡ አደጋው የሚያጣድፍ በሆነ ጊዜና በሕዝቤም ፊት ያለብኝ ኃላፊነት ህሊናዬን የሚነካ ስለሆነ በ1928 ዓ.ም መሣሪያ ለማግኘት ሞከርኩ፡፡ ብዙ መንግስቶችም እኔን ለመከላከል ሲሉ መሣሪያ ከአገር እንዳይወጣ ከለከሉ፡፡ የኢጣልያ መንግስት ግን በካናል ስዊዝ በኩል መሣሪያና ጥይት ወታደርም ሳያቋርጥና ማንም ሳይከለክለው ለማስተላለፍ ችሎ ነበር፡፡ በመስከረም 23 ቀን የኢጣልያ ወታደር ግዛቴን ለማስተላለፍ ችሎ ነበር፡፡ በመስከረም 23 ቀን የኢጣልያ ወታደር ግዛቴን አገሬን ወረረው፡፡ ከጥቂት ሰዓት በኋላ ብቻ ወታደር እንዲሰበሰብ የክተት ዐዋጅ አደረግሁ፡፡ ሰላምን ጠብቆ ለመኖር በመፈለግ አሳብ በታላቁ ጦርነት ጊዜ ጦርነቱ ሊደርስ አቅራቢያ አንድ ታላቅ መንግስት እንዳደረገው ሁሉ በማናቸውም ምክንያት እንዳደረገው ሁሉ በማንኛውም ምክንያት ጠብ ፈላጊነት እንዳይነሳ በማለት ወታደሮቼ ሰላሳ ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ኋላ እንዲመለሱ አደረግሁ፡፡ ከዚያም በኋላ ጦርነቱ ለምክሩ ጉባኤ እንዳመለከትኩት ሁሉ በታላቅ ግፍ ይቀጥላል፡፡
በዚህ በማይወዳደር ጦርነት 42 ሚሊዮን ሕዝብ የሚገዛው የሚያስፈልገውንም መሣሪያና ገንዘብ ለማግኘት የሚችል የሰው ሕይወት ለማጥፋት በያይነቱ የሆነ መሳሪያ ለመስራት የቴክኒክ ጥበብ ሁሉ ያለው መንግስት ያለመሳሪያ ያለገንዘብ ትክክል ፍርድንና የነገስታትን ማኅበር ቃል ብቻ ተማምኖ ከተቀመጠው ትንሽ ከሆነው ከ12 ሚሊዮን ሕዝብ ጋር በተደረገው በዚህ በማይወዳደር ጦርነት የሮማ መንግስት የማኅበሩን ውል አፍርሷል ተብሎ ከተፈረደና አጥቂውም እንዳያሸንፍ እንከላከላለን ከተባለ በኋላ በኢትዮጵያ መንግስት የተደረገው ያገኘውም እርዳታ እንደሌለ እናንተ ልትገምቱት ትችላላችሁ፡፡በማኅበሩ ያለው አንዳንድ መንግስት ሁሉ በማኅበሩ ውል በ17ኛው ክፍል ተፅፎ የፈረመው ፊርማ እንደሚያዘው ሁሉ አጥቂው ያደረገው ጦርነት በእያንዳንዱ ማኅበርተኛ ላይ በራሱ እንደተደረገበት ሁሉ ቆጥሮት የለምን?
ይህ ውል የተገባበት ቃል ይፈፀማል ብዬ ሙሉ ተስፋዬን በእሱ ላይ አድርጌ ነበር፡፡ ተስፋዬም ደግሞ አጥቂው ዋጋ አያገኝም ኃይልም በሕግ ፊት እንዲሸነፍ ይደረጋል ተብሎ በማኅበሩ ጉባኤ የተነገረው ቃል የሚያደላድል ተስፋ አግኝቶ ነበር፡፡በታህሳስ ወር 1928 ዓ.ም ኢትዮጽያ እንድትከፋፈል ተብሎ የቀረበውን ድርድር በዓለም ሁሉ ያለው ብዙ መቶ ሚሊዮን የሚሆን ሰው አስታውቆ ነበር፡፡ ብዙም ጊዜ ‹ይህ የተነሳው ጠብ የኢትዮጵያና የኢጣልያ መንግስት የመንግስታት ማኅበር ጠብ ነው› ተብሎ ተነግሮ ነበር፡፡እኔም ራሴ ሕዝቤም የመንግስታት ማኅበርን ውል የሚያስወግድ ለራሴ አቅም የሚሆን የቀረቡኝን ድርድር ሁሉ አልቀበልም ብዬ መመለሴ ስለዚህ ነበር፡፡ እኔም የተከላከልሁት ለጥቃት የሚያሰጋውን የትንንሾች መንግስቶች ጉዳይ ጨምሬ ነበር፡፡ እናደርግልሃለን የተሰጡኝ ቃሎች ሁሉ ወዴት ደረሱ?
ከታህሣሥ ወር 1928 ዓ.ም ጀምሮ ሶስት መንግስቶች በማኅበሩ ውል የገቡበትን ግዴታ ዋጋ እንደሌለው ሁሉ አድርገው በማየታቸው በታላቅ ሃዘን ተመከትሁ፡፡ ከኢጣልያ ጋራ ያላቸው አገባብ ኢጣልያ በአጥቂነት ያደረገችውን ስራ ለማቆም ማናቸውንም ነገር እንዳይቀበሉ አደረጋቸው፡፡ይልቁንም ደግሞ ለእኔ የተስፋዬን አሳብ የቆረጠብኝ ያንዳንዳቹ መንግስቶች ስራ ነው፡፡ እነዚሁም መንግስቶች በመንግስታት ማኅበር ላይ ያላቸውን እምነት ሳያቋርጡ እየተናገሩ የመንግስታት ማኅበር ሕግ እንዳይፈፀም ደግሞ ሳያቋርጡ ይደክማሉ፡፡ አንዳንድ መንግስቶች የአጥቂውን ስራ በቶሎ የሚያስቀር ደህና ነገር በቀረበ ጊዜ እንኳንስ ነገሩ እንዲፈፀምና ነገሩ ለክርክር እንዳይቀርብ በብዙ ምክንያት ያቆዩታል፡፡ በጥር ወር 1928 ዓ.ም የተደረገው የምስጢር ውል ይህን የመሰናክል ስራ አስቀድሞ ያመለከተ ኖሯልን?
የኢትዮጵያ መንግስት በቀጥታ ጥቅማቸው ያልተነካባቸው ሌሎች መንግስቶች የመንግስታትን ማኅበር ውል ለመከላከል የወታደሮቻቸውን ደም ያፈሰሱ ብሎ አልጠበቀም፡፡ የኢትዮጵያ ጦረኞች ጠይቀው የነበሩት ለመከላከል የሚሆናቸውን ነገር ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህም ብዙ ጊዜ መሣሪያ ለመግዣ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ጠይቄ ነበር፡፡ ይህንም እርዳታ ተከለከልሁ፡፡ በመንግስታት ማኅበር ውል በ16ኛው ክፍል የተፃፈው ቃልና መንግስቶች እየተባበሩ በመረዳት ፀጥታ እንዳይጠፋ ያደርጋሉ የተባለው የአፈፃፀሙ ትርጓሜ ምን ይሆን?
ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ ያለው የምድር ባቡር ለኢትየጽያ የሚሆን መሳሪያ እንዲተላለፍበትና ለኢትዮጵያ መንግስት እንዲያገለግል በተጠየቀ ጊዜ መሣሪያው በዚያ በኩል እንዳይገባ ብዙ ችግር ተደረገ፡፡ ላሁኑ ሰዓት ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ያላገባብ ለገባው ለኢጣልያ ሠራዊት ዋግ የሥንቅና የመሣሪያ ማመላለሻ ሆኗል፡፡ የገለልተኝነት (የኑትራሊቴ) ደንብ እንኳ የኢጣልያ ወታደሮች እስካሉበት ድረስ ይህን የመሰለው ነገር እንዳይጫን ይከለክላል፡፡ ይህ ከሆነ የመንግስታት ማኅበር ውል በ16ኛው ክፍል በተፃፈው ቃል ማኅበርተኞች የሆኑት መንግስቶች ሁሉ አንድ መንግስት ሌላውን በአጥቂነት የወጋው እንደሆነ ሌሎች ገለልተኛ መሆናቸው ቀርቶ መርዳት የሚገባቸው ለአጥቂው ሳይሆን ለተጠቂው ስለ ሆነ የነትራሊቴ ደንብ እዚህ መነሳት አይገባውም፡፡ በዚህ አኳኋን የመንግስታት ማኅበር ውል ከዚህ ቀድሞ ተጠብቋልን? ዛሬም እንደ ተጠበቀ ነው ለማለት ይቻላልን?
አሁን በመጨረሻው በመንግስታት ማኅበር ታላቅ አገባብ ያላቸው ታላቅ መንግስቶች በምክር ቤታቸው አጥቂው የኢጣልያ መንግስት ታላላቅ መንግስቶች በምክር ቤታቸው አጥቂው የኢጣልያ መንግስት የኢትዮጵያን መሬት አንዱን ክፍል ከያዘ በገንዘብ ጥቅም ረገድ ይህ እንዳይሆን ያቆምነውን መከላከያ መቀጠል አያስፈልግም ብለው አስታወቁ፡፡በአርጀንቲና መንግስት ጠያቂ በአጠቂው በኢጣልያ ምክንያት የሆነውን ነገር ለመመርመር የተሰበሰበው የመንግስታት ማኅበር ዋና ጉባኤ ዛሬ በፊቱ የሚገኘው አኳኋን ይህ ነው፡፡
ዛሬ የመንግስታት ማኅበር ዋና ጉባኤ በፊቱ ያለው ጉዳይ ኢጣልያ በአጥቂነት የሰራችውን ለመጨረስ ብቻ አይደለም፡፡ በሙሉ የዓለምን መንግስታት የሚነካ መሆኑን አረጋግጬ አስታውቃለሁ፡፡ ይህም ጉዳይ ለዓለም ፀጥታ እንዲሆን መንግስታት ለመረዳዳት የሚገባቸው የጋራ ፀጥታ (ሴኩሪቲ ኮሌክቲቭ) የተባለው የመንግስታት ማኅበር ሕይወተ የዓለም መንግስቶች ለተዋዋሉት ውል መሰጠት የሚገባቸው እምነት ትንንሾቹም መንግስቶች አገራቸውና ነፃነታቸው እንዳይነካ የተቀበሉት ቃል ኪዳን የሚከበርበትና ዋጋው የሚገመትበት የመንግስቶች ትክክለኛነት የተመሠረተበት መሠረት ይህን ለማፅናት ወይም ትንንሾች መንግስቶች የኃይለኞች መንግስቶች ተገዥ ለመሆን መቀበል ይገባቸው እንደሆነ ለመፍረድ ነው፡፡ በአጭር ቃል የተነካውና የተበደለው የዓለም ሕዝብ የተገባ አነዋወር ነው እንጂ ኢትዮጵያ ብቻ አይደችም፡፡ በአንድ ውል ላይ የተፈረሙ ፊርማዎች ዋጋቸውን የሚያገኙ አንዱ በሌላው ላይ የግል ጥቅሙን በቀጥታና በፍጥነት ለማግኘት ለመፈፀም እንዲችል እንዲረዱት ሲሆኑ ነውን?
በረቂቅ መንገድ መበላለጥ ዋናውን ነገር ሊለውጠው ወይም የክርክሩን መንገድ በሌላ በኩል ሊመራው አይገባም፡፡ ይህንም ማመልከቻ ለመንግስታት ማኅበር ዋና ጉባኤ የማቀርበው በእውነተኛነት ከልቤ ነው፡፡ከእግዚአብሔር መንግስት በስተቀር የፍጡር መንግስት ሁሉ አንዱ ካንዱ የሚያበላልጥ ስራ የለውም፡፡ ነገርግን በምድር ላይ ኃይለኛ የሆነው የሚገባው መስሎት የተነሳበት ጊዜ፣ ተጠቂው ወገን ለመንግስታት ማኅበር የተበደለውን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው፡፡ እግዚአብሔርና ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ምስክር ሆነው ይመለከታሉ፡፡
ሕዝቤ ዘሩ ሊጠፋ በደረሰበት የመንግስታት ማኅበርም እርዳታ ከጥፋት ለማዳን በሚችልበት ጊዜ ማናቸውንም ሳላስቀርና ሳላቆይ በተዘዋሪ ቃል ሳይሆን አውነቱን አውጥቼ እንድናገር ሊፈቀድልኝ የተገባ ነው፡፡ከዚህ ቀደም የተደረገው ሳይበቃ የቀረው ሳንክሲዮን የታሰበውን ፍሬ አላፈራም ተብሎ በማረጋገጥ ቃል ሲነገር እሰማለሁ፡፡ በማናቸውም ጊዜ በማናቸውም ምክንያት ቢሆን በፈቃድ እንደማይበቃ የተደረገና ደግሞ አፈፃፀሙ እንደሚገባ ስለሆነ ሳንክሲዮን አጥቂውን ለማቆም እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ አጥቂውን ሳናቆመው ቀረን ያሰኛል እንጂ የማይቻል ስለሆነ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ የገንዘብ እርዳታ እንዲደረግላት ከዚህቀደም ጠየቀች፡፡ አሁንም ትጠይቃለች፡፡ ይህስ ሊፈፀም የማይቻል ነውን?
የመንግስታት ማኅበር ግን በሰላም ጊዜ እንኳ በአጠቂው ላይ ሳንክሲዮን አናደርግበትም ላሉ ለሌሎች መንግስቶች በገንዘብ እርዳታ አድርጎላቸው ነበር፡፡ የኢጣልያ መንግስት የጨካኝነት መሣሪያ እንደያገለግለው በማድረጉ ብዙ ጊዜ እየደጋገመ የዓለምን መንግስታት ሕግ ሁሉ በመተላለፍ ምክንያት ዛሬ ሳንክሲዮን ይነሳለት የሚል አሳብ መታሰቡን ልቤ እጅግ እያዘነ ተመለከትሁ፡፡ ይህስ አደራረግና አሳብ ኢትዮጵያን አጥቂው መንግስት የፈቀደውን ይፈፅምባት ብሎ መተው አይደለምን? በመንግስታት ማኅበር ዋና ጉባኤ ፊት ለሕዝቤ በታላቅ ብርታት ለመከላከል ባቀረብሁበት ጊዜ ጥቂት ቀደም ብሎ ይህ አሳብ መታሰቡ የመንግስታት ማኅበር ማኅበርተኞች ከሆኑት መንግስቶች ኢትዮጵያ እርዳታንና መተማመኛ እንዳታገኝ አንደኛውን መጨረሻውን እድሉን የሚቆርጥባት አይደለምን? የመንግስታት ማኅበር ስራ መሪ ለመሆን ስልጣን ባላችሁ በታላላቅ መነግስቶች እርዳታ የሚገኘው የመንግስታት ማኅበርና ማኅበርተኞች በሚገባ ተስፋ አድርገው የሚጠብቁት ይህን የመሰለውን ፍፃሜ ነውን?
ኢጣልያ በአጥቂነት በሰራችው ስራ ነገሩ እዚህ ቢደርስ የመንግስታት ማኅበርተኞች የሆኑት መንግስቶች የኃይለኛውን ፈቃድ በመፈፀም ምሳሌ ለመተው ፈቃዳቸው ይሆናልን?
የመንግስታት ማኅበር ውል እንዲሻሻልና የመንግስታት መረዳዳት የሚሰጠው መተማመኛ የተፈተነ እንዲሆን ለማድረግ ተብሎ በእርግጥ ለመንግስታት ማኅበር ዋና ጉባኤ አሳብ መቅረቡ ነው፡፡ መለወጥ የሚገባው ውሉን ኖርዋልን? ውሉን የፈረሙት በሙሉ የተፃፈውን ቃል ለመጠበቅ ፈቃዳቸው ካልሆነ ውሉ ቢለወጥስ እንዲጠበቅ ምን መተማመኛ ይገኛል? የጎደለው ከዓለም መንግስታት አሳብ ነው እንጂ ከመንግስታት ማኅበር ውል አይደለም፡፡የመንግስታት ማኅበርተኛው በሆነው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ሆኜ የመንግስታት ማኅበር ውል እንዲከበር የሚያስፈልገው ነገር እንዲፈፀም ጉባኤውን እጠይቃለሁ፡፡በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከውል የተላለፈ ነገር ስለተደረገበት በዚሁ በተደረገበት ግፍ ምክንያት ከዚህ ቀድሞ ያቀረብሁትን በመቃወም አሁንም እንደገና እቃወማለሁ፡፡ በዓለም ፊት ሆኜ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የኢትዮጽያ መንግስትና ሕዝብ በኃይል የተደረገባቸውን ነገር አይቀበሉም፡፡ስርዓት እንዲያሸንፍ የመንግስታት ማኅበር ውል እንዲከበር የሚገባቸውም ስልጣንና ግዛት እንዲመለስላቸው የሚቻላቸውን ነገር ሁሉ ማድረጋቸውን እገልጣለሁ፡፡
በተጠቃችሁ ጊዜ አጥቂ እንዳያሸንፋችሁ እንረዳችኋለን ብለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል ኪዳን የገቡት 52 መንግስቶች ቃል ኪዳናቸውን አፅንተው እንዲረዱ እርዳታቸውን እጠይቃለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ምን ልታደርጉላት ትፈቅዳላችሁ? ታናናሽ መንግስቶች እንዳይጠፉ በኢትዮጵያ የደረሰባት እድል እንዳይደርስባቸው መንግስቶች እንዲረዳዱ መተማመኛ ለማድረግ ቃል ኪዳን የገቡትም ታላላቅ መንግስቶች የኢትዮጵያ ነፃነት እንዳይጠፋ፣ ግዛቷም እንዲከበር ምን አይነት እርዳታ ለማድረግ አስባችኋል?እዚህ የተሰበሰባችሁ የዓለም እንደራሴዎች ሆይ፣ አንድ ንጉሠ ነገሥት በደረሰበት ሃዘን ማድረግ የሚገባውን ሥራውን ለመፈፀም ጄኔብ ወደ እናንት መጥቻለሁ፡፡ለሕዝቤ ምን ምላሽ ልውሰድለት??
|
No comments:
Post a Comment