Saturday, August 11, 2012

አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው የሚጠቁሙ ጥናቶች በ ሐሰን መሐመድ ሐሰን


ምዕራፍ ሁለት፡- ክለሳ ድርሳን
2.1.አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ግንኙነት
አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ፡፡ ዴይና ባምፎርድ (1982) በጥናታቸው እንደገለፁት አመለካከቶች ሰዎች አንድን ተግባር እንዲያከናውኑ ወይም እንዳያከናውኑ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ አዎንታዊ አመለካከቶች አንድን ነገር ለማድረግ የሚያነሳሱ ሲሆኑ፣ በተቃራኒው አሉታዊ አመለካከቶች አንድን ተግባር በንቃት ለማከናወን  ተነሳሽነትን ይቀንሳሉ፡፡ በተመሳሳይ የማንበብ ተግባርም ግለሰቦች ለማንበብ ባላቸው አመለካከቶች አማካኝነት ተፅዕኖ ይደርስበታል፡፡ የማንበብ አመለካከታቸው አዎንታዊ የሆነ አንባቢያን ማንበብን መለማመድ ሲያፈቅሩ፣ ለማንበብ አሉታዊ አመለካከት ያላቸው ማንበብን ከመጥላታቸውም በላይ በማንበብ ተግባራት ለመሳተፍ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ይህ የሚያመለክተው አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ጥናት ያደረጉት ኮንሊ (1992) እንዳብራሩት የማንበብ አመለካከት ተማሪዎች አንድን ንባብ ለማንበብ ወይም ላለማንበብ ያላቸው ስሜት ሲሆን፣ ይህንን ተፅዕኖ የሚያሳድረው ደግሞ አመለካከት ነው፡፡ በተጨማሪም አዎንታዊ የማንበብ አመለካከት ስኬታማ ማንበብን ሲያጎናፅፍ አሉታዊ የማንበብ አመለካከት አንባቢያን ደካማ ፍላጎት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ አሌክሳንደርና ፊለር (1992) ጨምረው እንዳስረዱት ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከት አዎንታዊ ከሆነ የማንበብ ችሎታ ውጤታቸው ስለሚጨምር ብዙ ያነባሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የማንበብ አመለካከታቸው አሉታዊ ከሆነ ውጤቱ የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡
ሮኢና ስሚዝ (2005) እንዳብራሩት ደግሞ ተማሪዎች ንባብን ለመማር ተግባራትን ሲያከናውኑ በሂደቱ ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩት ነገሮች ዋነኞቹ የማንበብ አመለካከቶች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የቀረበላቸውን ምንባብ ለማንበብ በጐ አመለካከት ያላቸው ተማሪዎች ንባብን ለመማር ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ፣ በጐ ያልሆነ አመለካከት ያላቸው ግን በሂደቱ ለመሳተፍ እንቅስቃሴያቸው ዝቅ ያለ ነው፡፡
ተመሳሳይ ጥናት ያቀረቡት ኮንሊ (1992) እና ሜይ (1990) እንዳመለከቱት የተማሪዎችን የማንበብ አመለካት አዎንታዊ ወይም አሉታዊ የሚያደርጉት መምህራን ናቸው፡፡ ለምሳሌ መምህራኑ በመማሪያ ክፍል ውስጥ አዎንታዊ የማንበብ አመለካከትን የሚያጎለብቱ ልምዶችን ለተማሪዎች ካስተዋወቁ፣ ተማሪዎቻቸው ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ ያነበቡዋቸውን መፅሄት፣ መፀሐፍና መጣጥፍ ወደ መማሪያ ክፍላቸው ይዘው እያመጡ ካነበቡላቸው የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከት አዎንታዊ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ ሙለር (1973) የተባሉት ተመራማሪ በበኩላቸው የማንበብ አመለካከትን ለመለካት በ41 ተማሪዎች ላይ ቅኝት አድርገው ነበር፡፡ የጥናቱ ውጤት  እንደሚያመለክተው የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት በከፍተኛ ሁኔታ ለተፅዕኖ የሚያጋልጠው የመምህራን የማንበብ አመለካከት ነው፡፡ በማንኛውም ክስተት መምህራን የተማሪዎቻቸውን የማንበብ አመለካከት ከተረዱና ከተቀበሉት ለውጥ ያመጣሉ፡፡ ይህንን በሚመለከት ተመሳሳይ ጥናት ያደረጉት ሞዩር (1977) የማንበብ አመለካከትን ከመምህራን የማንበብ ልምድ ጋር አያይዘውታል፡፡ በተጨማሪም መምህራን አዘውትረው የሚያነቡ ከሆነ ተማሪዎቻቸውም የማንበብ አመለካከታቸው አወንታዊ እንዲሆን አርአያ ይሆናሉ፡፡ ይህንን በምርምር ለማረጋገጥ በተደረገው ጥናት አዘውትረው ከሚያነቡና ከማያነቡ መምህራን በመጠይቅ የተሰበሰበው መረጃ ውጤት እንዳመለከተው አንባቢ መምህራን ከማያነቡት በተሻለ ለተማሪዎች የማንበብ አመለካከት አርዓያ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ከዚህ በተለየ ኢስቴስ (1971) የተባሉት ተመራማሪ ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸው የሚለወጥበትን ምክንያት ለማወቅ ጥናት አድርገዋል፡፡ ይህንንም ዕውን ለማድረግ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት መለኪያ መጠይቅ አዘጋጅተው ነበር፡፡ በጥናቱ ከሶስተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከሚማሩ ተማሪዎች መካከል ናሙና በመውሰድ የማንበብ አመለካከታቸውን ለክተዋል፡፡ ከትንተናው የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው ማንበብን በተመለከተ የወጣት ተማሪዎች አመለካከት አወንታዊ ነው፡፡
ከዚህ ምርምር ጋር የሚቃረን ጥናት ያቀረቡት ተመራማሪ ራንስበሪ (1973) ናቸው፡፡ ተመራማሪው በጥናታቸው 65 የጥናት ተሳታፊ ተማሪዎችን፣ መምህራንና ወላጆችን በመምረጥ ለማንበብ የሚያስደስታቸውንና የማያስደስታቸውን ንባብ  እንዲገልፁ አድርገዋል፡፡ ተማሪዎቹ አንድን ንባብ እንዲያነቡና እንዳያነቡ የሚገፋፉት በንባብ መማሪያ  መፃህፍት አማካኝነት መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ወላጆች ንባብን እንዲጠሉት ያደረጋቸው ምክንያት አዘውትረው አለማንበባቸው ነው፡፡ መምህራን በበኩላቸው የማንበብ አመለካከት አወንታዊና አሉታዊ እንዲሆን የሚያደርገው የተማሪዎች አዕምሯዊ ችሎታ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ በጥናቱ ማጠቃለያ ላይ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ተፅዕኖ የሚያሳድርበት ዋነኛ ምክንያት የንባብ ችሎታ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ሒዚግነቶንና አሌክሳንደር (1984) ባካሔዱት ጥናት ደግሞ አወንታዊ የማንበብ አመለካከትን ለማዳበር የመምህራንና የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ገምግመዋል፡፡ በጥናቱ 100 መምህራን በማስተማር ልምዳቸው መሰረት ተመርጠው ንባብን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ሲያስተምሩ ምን፣ ምን ተግባራትን እንደሚያከናውኑ አጠቃላይ መጠይቅ ቀርቦላቸዋል፡፡ በመጠይቁ ላይ ትኩረት በመስጠት የሚጠቀሙባቸውን 9 የማስተማር ልምዶችን በቅደም ተከተል እንዲዘረዝሩ ተጠይቀዋል፡፡ በመጠይቁ የቀረቡላቸው ዝርዝሮችም አንብቦ መረዳት፣ ቃላዊ ንባብ፣ የዝምታ ንባብ፣ ቃላዊ ትርጉም፣ ቃላትን መምረጥ፣ መዋቅራዊ ትንተና፣ የማንበብ አመለካከቶችና የክህሎት ጥናት የሚሉ ነበሩ፡፡ ከመጠይቁ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው በርካታዎቹ መምህራን የማስተማሪያ ክፍለ ጊዚያቸውን ለማንበብ አመለካከት ማጎልበቻነት አይመድቡም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ መምህራኑ ክህሎትን በማስጨበጥ ላይ ስለሚያተኩሩና የክህሎት እድገት የማንበብ አመለካከትን አዎንታዊና አሉታዊነት ለመጨመርና ለመቀነስ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡
ማና እና ማይሽፍ (1987) ከላይ ያለውን ጥናት በመቃረን ባደረጉት ጥናት በዩኒቨርስቲ የስነ-ፅሁፍ ተማሪዎች ለምን ለአሉታዊ የማንበብ አመለካከት እንደተጋለጡ መርምረዋል፡፡ ምክንያቱንም ለመገንዘብ ጥረት አድርገዋል፡፡ ጥናቱን ተግባራዊ ለማድረግ በጥቅም ላይ የዋለው የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያ ተማሪዎቹ ግለ ታሪካቸውን እንዲሞሉ በማድረግ ነበር፡፡ ከተማሪዎቹ ግለ ታሪክ በዳግም ግምገማ ከተገኘው ውጤት ለመረዳት እንደተቻለው በተማሪዎቹ ላይ አሉታዊ የማንበብ ተፅዕኖ ያሳደረው የተማሪዎቹ ወላጆችና መምህራን አርዓያ በመሆን የማንበብ አመለካከታቸው እንዲጎለብት ድጋፍ ስላላደረጉላቸው ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሞሪሰን፣ ጃኮብስና ስዊንያርድ (1999) መምህራን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ለተማሪዎቻቸው የሚያነቡላቸው ግላዊ የመዝናኛ ንባብ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ለመለወጥ ያለውን ፋይዳ በሚመለከት አጥንተዋል፡፡ በመጠይቅ ከተሰበሰበው የማስተማርና ግላዊ የንባብ ልምድ መረጃ ከተገኘው ውጤት ለመረዳት እንደተቻለው መምህራን በአብዛኛው የሚያነቡት የሚያስተምሩትን ትምህርት መፃሕፍት ንባቦችን ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ተማሪዎቹ ማንበብን መሰረት በማድረግ እየተዝናኑ ስለማይማሩ ለማንበብ ያላቸው አመለካከት ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ ወደ መሆን አዘንብሏል፡፡
አፕሊጌትና አፕሊጌት (2004) ያደረጉት ጥናት የመምህራንን የማንበብ ልምዶችና አመለካከቶች የሚመርምር ነው፡፡ በልቅ መጠይቅ አማካኝነት በመምህራን ላይ በተደረገው ቅኝት 54% የሚሆኑት መምህራን የማንበብ ጉጉት የሌላቸው መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ለዚህም ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የተገመተው መምህራኑ በቀድሞ የትምህርት ዘመናቸው ወቅት የማንበብ አመለካከታቸው አሉታዊ ተፅዕኖ አድሮበት ስለነበር ነው፡፡ በጥናቱ ማጠቃለያ  ላይ እንደሰፈረው የመምህራን ማንበብን ያለመውደድ ልምድና የአመለካከት አለመዳበር የተማሪዎቻቸውን የማንበብ አመለካከት በዕጅጉ እንደሚጎዳ ተገልጧል፡፡
የብላክቢ (2006) ጥናት ከአፕሊጌትና አፕሊጌት (2004) የተለየ ነው፡፡ ተማሪዎች እንደሚኖሩበትና እንደተማሩት አግባብ የማንበብ ክሕሎታቸው ዕድገት ለተፅዕኖ ይጋለጣል፡፡ በማንበብ አመለካከቶች ላይ አወንታዊና ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ ለማድረስ ምክንያት የሚሆኑት ጉዳዬች ተፈጥሮ (innate) ፣ ቤተሰብና ትምህርት ቤት ናቸው፡፡ እነዚህ የተፅዕኖ ምክንያቶች ተማሪዎች ለማንበብ በሚነሳሱበት ወቅትና ራሳቸውን እንደ አንባቢ መቁጥር በሚጀምሩበት ጊዜ ማንበብን እንዲወዱ ወይም እንዲጠሉ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ብላክቢ (2006) ጨምረው እንደገለፁት፣ ቤተሰብ በማንበብ ላይ አንዳንድ ተፅዕኖዎች ያሳድራል፡፡ ማህበራዊ መደቦችና የቤተሰብ ባሕል የተማሪዎች ማንነት ላይ ጫና በመፍጠር ተፅዕኖ የሚያሳድረው አመለካከታቸውና የንባብ ተግባራቶች ላይ ነው፡፡ ተማሪዎች በቤተሰባቸው አማካኝነት የማንበብና የመፃፍ ችሎታቸው ሲያድግ አመለካከታቸውም አብሮ ያድጋል፡፡
ሞሮውና ያንግ (1997) በተመሳሰይ እንዳጠኑት ወላጆች በመኖሪያ ቤት ልምዶቻቸው በልጆቻቸው ላይ ተፅዕኖ እንዲሚያሳድሩ ያምናሉ፡፡ የቀን ተቀን የቤተሰብ ተግባራት በልጆች የማንበብ ዕድገት፣ በአመለካከቶቻቸውና በማንበብ ተግባራት የተሳትፎ ፍላጎታቸው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ወላጆች ወይም ልጆችን ተንከባካቢዎች መልካም አርዓያ በመሆን ተፅዕኖ ለማሳደር የሚችሉበት ምክንያት ልጆቻቸው በማንበብ ልምምድ ወቅት ምን፣ እንዴት፣ መቼና ለምን እንደሚያነቡ ስለማያስረዷቸው ነው፡፡
ይሁን እንጁ ማዩንግሱንና ሒኪዩንግ (2002) ባደረጉት ጥናት የማንበብና የአመለካከት ዕድገት የሚመጣው በትምህርት ቤት ብቻ የሚመስላቸው በርካታ ወላጆች እንዳሉ አረጋግጠዋል፡፡ በእርግጥ በቤተሰብ ብቻ ሳይሆን፣ በትምህርት ቤት አማካኝነትም በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አዩናላና ሌሎች (2002) በትምህርት ቤት ውስጥ የማንበብ አመለካከትን ለተፅዕኖ የሚያጋልጡ ናቸው በማለት የዘረዘሯቸው፡- ተማሪዎችን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ለመዝናናት ማስነበብ፣ በራሳቸው ምርጫ ፅሁፎችን እንዲያነቡ ማድረግና በክፍል ውስጥ ለጓደኞቻቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማስነበብ ናቸው፡፡
ጋምብሪል (2004)፣ በጥናታቸው ግኝት እንደደረሱበት መምህራን ተማሪዎችን አዝናኝ ንባቦች መርጠውላቸው ማስነበብ የማንበብ አመለካከታቸው አወንታዊ ቅርፅ እንዲይዝና የራስ ግላዊ ውጤታማነታቸው እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ተማሪዎቹ በመደበኛነት የመዝናኛ ንባብ የሚያነቡ ከሆነ በስፋትና በጥልቀት ማንበብ እንዲለምዱ፣ የማንበብ ክህሎት ብቃታቸው እንዲያድግ፣ የአንብቦ መረዳትና የቃላት ችሎታቸው እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ምናባቸውን ለማስፋት፣ የፈጠራና የክህሎት ዕድገታቸውን ከፍ ለማድረግ ይረዳል፡፡ የጉዝሪ (1999) የጥናት ውጤት ከጋምብሪል (2004) ጋር ይቃረናል፡፡ ተማሪዎች በራሳቸው ምርጫ ብቻ  የመዝናኛ ፅሁፎች ወይም ድርሳናትን መርጠው ማንበባቸው ከራሳቸው ፍላጎትና አመለካከት ጋር የሚገጣጠም ርዕስ እንዲያነቡ ስለሚያደርጋቸው በራሳቸው ሙከራዎች ስሌት ዕውቀትና ልምዶቻቸውን በማስፋት ግላዊ ዓላማቸውን ለማሳካት ያገለግላቸዋል፡፡
ከዚህ ጥናት በተለየ ድሪኸር (2003) እንደገለፁት ተማሪዎች ድምፃቸውን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ከፍ አድርገው እንዲያነቡ ማድረግ አወንታዊ የማንበብ አመለካከታቸው እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ ተማሪዎቹን ከንባብ በኃላ በቁልፍ ሐሳቦች ላይ ማወያዬት ፍላጎታቸውን ያጠናክራል፡፡ አወንታዊ የማንበብ አመለካከታቸውን ያሳድጋል፡፡ ብራስል (2003) እንደጠቀሱት ደግሞ የመዝናኛ ምንጭ ይሆናቸዋል፣ የቃላት ክምችታቸው መሰረት ይይዛል፣ ውጤታማ የንባብ ብልሐቶችን ይማራሉ፡፡
በመጨረሻም ስችማይት (2009) እንደሚገልፁት የማንበብ አመለካከትን በሚመለከት   ተመሳሳይና ተቃራኒ ጥናቶች አሉ፡፡ የጥናቶቹ ግኝቶች የማንበብ አመለካከት በወላጆችና በመኖሪያ ቤት አካባቢ፣ በመማሪያ ክፍል እንዲሁም በተማሪዎችና በመምህራን አመለካከትና ባሕሪ ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ያላቸውን ግንኙነት የሚጠቁሙ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ከተደረጉት ጥናቶች ቅኝት ለመገንዘብ እንደሚቻለው ማንበብና የማንበብ አመለካከት ጥብቅ ግንኙነት አላቸው፡፡ አመለካከት በማንበብ ላይ የሚያሳድረው የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ የማንበብ አመለካከት ተለዋዋጭ ሲሆን፣ ምክንያቶቹም ወላጆች፣ ቤተሰብ፣ መምህራንና አካባቢ የሚያሳድሩት አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም አመለካከትና የማንበብ አመለካከትን ግንኙነት ጠንቅቆ በመረዳት በትምህርት ቤት ውስጥ በተማሪዎች የማንበብ አመለካከት ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ መፈለግ ያሻል፡፡
2.2. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከት
ኩሊክና ኩሊክ (1982) በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በችሎታ አቅም የተደራጀ ቡድን ለአመለካከት ለውጥ ያለውን አስተዋፅኦ በሚመለከት ጥናት አድርገዋል፡፡ ጥናቱ የተካሄደው 52 ተማሪዎችን በከፍተኛ፣ በመካከለኛና በዝቅተኛ ችሎታ ቡድኖች በማደራጀት ነበር፡፡ የጥናቱ ውጤት እንዳመለከተው ተማሪዎችን በቡድን ማደራጀት ለአመለካከት ለውጥ ጠቀሜታ አለው፡፡ በጥናቱ በቡድን የተደራጁት ተሳታፊዎች ለሚማሩት የትምህርት ዓይነት በርካታ አዎንታዊ አመለካከቶችን ሲያሳድጉ፣ በቡድን ያልተደራጁት ግን አመለካከታቸው አሉታዊ ሆኗል፡፡ በቡድን ከተደራጁት መካከልም ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች አመለካከታቸው ከፍተኛ ሲሆን፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ችሎታ ያላቸው የአመለካከታቸው ደረጃ መካከለኛዎቹ መካከለኛ፤ ዝቅተኛዎቹ ደግሞ ወደ ዜሮ የሚጠጋ አመለካከት አስመዝግበዋል፡፡
በተመሳሳይ ሊናና ካሪም (2007) የማንበብ አመለካከት፣ ቤተሰባዊ ቅድመ ሁኔታና በራስ ጥረት መማር በማንበብ ችሎታ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በሚመለከት ጥናት አድርገዋል፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በ4018 የጥናቱ ተሳታፊ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ መጠይቅና አንብቦ የመረዳት ፈተና በማቅረብ ነው፡፡ ከጥናቱ የተገኘው ውጤት እንደጠቆመው የቃላዊ/የአጠቃላይ ትምህርት በራስ ጥረት መረዳት (Verbal/General academic self-concept) የማንበብ ችሎታ ከፍተኛ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም የፆታ ልዩነት በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ እንዳለውና እንደሌለው ተፈትሿል፡፡ በጥናቱ ውጤት እንገተገለፀው ሴቶቹ ተማሪዎች ከወንድ ተማሪዎች በተሻለ አዎንታዊ የማንበብ አመለካከት አላቸው፡፡ ወንዶቹ ተማሪዎች የተሻሉ ሆነው የተገኙት ትምህርትን በራስ ጥረት በመረዳት፣ በራስ ውጤታማነት፣ በማስታዎስ፣ በማብራራትና በመነሳሳት ናቸው፡፡
በተጨማሪም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አስቸጋሪ አጫጭር ታሪኮችን(ንባቦችን) የማንበብ አመለካከት፣ አንብቦ የመረዳትና የማስታዎስ ችሎታ ለመመርመር ግራቪስ፣ ላበርግና ኩኪ (1983) ጥናት አድርገው ነበር፡፡ ለጥናቱ ተሳታፊ 72 ተማሪዎች በደረጃቸው አንብቦ ለመረደት ቀላልና አስቸጋሪ አጫጭር የንባብ ታሪኮችን በማቅረብ ጥናቱ ተካሂዷል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንዳመለከተው አንብቦ ለመረደት ቀላል ለሆኑት ታሪኮች የተማሪዎቹ አመለከካት አዎንታዊ ሲሆን፣ የመረዳትና የማስታዎስ ችሎታቸውም ከ13% እስከ 38% ጨምሯል፡፡
በሌላም በኩል ክሪስቲናና ጆናታን (2011) የታላቋ እንግሊዝ ወጣት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸው ለምን እንደቀነሰ ለማወቅ ጥናት አድርገዋል፡፡ በጥናቱ በ17,000 ተማሪዎች ላይ ለማንበብ አመለካከታቸው መቀነስ የትምህርት ቤት የማንበብ ብቃት፣ የፆታ ወይም የጎሳ ልዩነት ምክንያት እንደሆን ቅኝት በማድረግ ባህሪያቸውን ለመመርመር ጥረት ተደርጓል፡፡ በጥናቱ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከት ከ2005 እስከ 2009 ባሉት አምስት ዓመታት  ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ ምክንያቱ ደገሞ  ወጣቶቹ በማንበብ ስለማይደሰቱ ማንበብን ማቆማቸው ነው፡፡
በመጨረሻም በትምህርት ውጤታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸውን አመለካከት፣ የማንበብ ችሎታ ውጤታቸውንና በራስ ጥረት ማንበብን በማጐልበት የትምህርት ብቃታቸውን ማሳደግ ይቻልና አይቻል እንደሆን ለመመርመር ቲዎዶር (2010) ጥናት አድርገው ነበር፡፡ ጥናቱን ለማካሄድ በትምህርታቸው ውጤታማ የሆኑ ተማሪዎችን በሁለት ቡድን በማደራጀት አንደኛው ቡድን በንባብ ማሻሻያ መርሐ ግብር (Remedial Reading Program) እንዲሳተፍ ሲደረግ ሌላው ቡድን ግን አልተሳተፈም፡፡ በተጨማሪም ሁለቱም ቡድኖች የማንበብ አመለካከት መጠይቅ እንዲሞሉ ተደርጓል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደጠቆመው በንባብ መፍትሄ መርሐ ግብር የተሳተፉት ተማሪዎች ካልተሳተፉት ጋር ሲነፃፀሩ የማንበብ አመለካከታቸው ተሻሽሏል፣ በራስ ጥረት የማንበብ ውጤታማነታቸው ደረጃው ከፍተኛ ሆኗል፡፡
ለማጠቃለል ያህል ከጥናቶቹ ውጤት ለመገንዘብ እንደሚቻለው የሁለተኛ ደረጃ ትህርት ቤት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከት በተለያዩ ምክንያቶች ለተፅኖ ይጋለጣል፡፡ ተማሪዎችን በቡድን ማደራጀት ለአመለካከት ለውጥ ጠቀሜታ አለው፡፡ የማንበብ አመለካከት፣ ቤተሰባዊ ቅድመ ሁኔታና በራስ ጥረት መማር በማንበብ ችሎታ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ አንብቦ ለመረደት ቀላል የሆኑ ታሪኮች(ንባቦች) የተማሪዎቹን የማንበብ አመለከካት አዎንታዊ ያደርጋሉ፤ የመረዳትና የማስታዎስ ችሎታን በእጅጉ   ይጨምራሉ፡፡ በማንበብ የማይደሰቱ ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ ቢሆንም አመለካከታቸውን በተለያዩ ዘዴዎች በማሳደግ ማሻሻል ይቻላል፡፡
2.3. የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ
ሳላበስ (2008) በ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ መኖርና አለመኖሩን በሚመለከት ባደረጉት ጥናት የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ ደረጃው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከትና የትምህርት ውጤታቸው ተዛምዶ እንዳለው ተጠንቶ ተዛምዶው ዝቅተኛ ደረጃ እንዳለው ተረጋግጧል፡፡ በጥናቱ በፆታ ምክንያት የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ልዩነት እንዳለው ታውቋል፡፡ ለዚህም በጥናቱ  እንደ ምክንያት የተጠቀሱት ተማሪዎቹ የቀረበላቸውን ንባብ በግልፅና በትክክል አለመረዳታቸው፣ የንባቡን መዋቅር፣ ይዘትና ቴክስት ለመተቸት አለመቻላቸው ናቸው፡፡
ፒትስቸር (2010) በተመሳሳይ ባደረጉት ጥናት በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የማንበብ ችሎታ ውጤት መካከል ያለውን ተዛምዶ ቃኝተዋል፡፡ በ32 ተማሪዎች ላይ በተደረገው ጥናት የተገኘው ውጤት እንደጠቆመው የተዛምዶው መጠን ዝቅተኛ ነው፡፡ በጥናቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የማንበብ ውጤታማነት መካከለኛ ተዛምዶ ሲኖረው፣ በመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩት ዝቅተኛ ተዛምዶ አስመዝግበዋል፡፡    
ከዚህ ጥናት ጋር በተያያዘ ናንሲ (1989) ከ 1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎችን ለማንበብ ያላቸውን አመለካከትና የማንብ ችሎታ ውጤት ተዛምዶ አጥንተዋል፡፡ በጥናቱ የተሳተፉ 876 ተማሪዎች ከሞሉት የማንበብ አመለካከት መለኪያ መጠይቅና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ፈተና  የተገኘው ውጤት እንደሚያስረዳው (1) በተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከትና የንባብ ውጤታማነት መካከል ተዛምዶው  ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፤ (2) የማንብቦ ችሎታ ውጤታቸው ደረጃው መካከለኛ ሆኗል፤ (3) እስከ ስምንተኛ ክፍል ባሉት የትምህርት ደረጃዎች የማንበብ አመለካከታቸው ቀንሷል፤ (4) ከወንዶቹ ተማሪዎች በተሻለ የሴት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የንባብ ውጤታማነት ተዛምዶ ከፍተኛ ሆኗል፤ (5) የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች የማንበብ አመለካከት አዎንታዊ እንደነበር ተጠቁሟል፤ (6) በሴትና በወንድ ታሪዎች መካከል የማንበብ ብቃትን በሚመለከት ጉልህ ልዩነት አልታየም፤ (7) ዝቅተኛ የማንበብ ችሎታ ውጤት (achievement) ያላቸው ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸውም ቀንሷል::
በተጨማሪም ባስ (2012) የተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የመፃፍ ዝንባሌ ተዛምዶ እንዳላቸውና እንደሌላቸው አጥንተዋል፡፡ ተመራማሪው በቱርክ ሐገር ኒጋዳ ትምህርት ቤት በ450 ተማሪዎች ላይ ባደረጉት ጥናት በመጠይቅ የተሰበሰበው መረጃ ውጤት እንዳመለከተው በማንበብ አመለካከትና በመፃፍ ዝንባሌ መካከል አዎንታዊ ተዛምዶ አለ ፡፡ እንዲሁም የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት የመፃፍ ዝንባሌያቸውን የመተንበይ ድርሻው የጎላ ነው፡፡
በተመሳሳይ ተራቪስ (2010) የተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና ስነፅሁፍ የማንበብ ልምዳቸው ተዛምዶ መኖርና አለመኖሩን መርምረዋል፡፡ ለ18 ወራት በተደረገው ጥናት የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከት፣ የንባብ ልምድና በተጓዳኝም ሥነ ፅሁፍን የማንበብ ተነሳሽነታቸው በመጠይቅ መጠናዊና ዓይነታዊ መረጃ ተሰብስቦ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸው በጐለበተ መጠን ልምዳቸው በመዳበሩ የማንበብ ተነሳሽነታቸው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊለወጥ ችሏል፡፡ በጥናቱ ተማሪዎች ለረጅም ጊዜ እያነበቡ የመቆየት ልምዳቸው በአመለካከታቸው ላይ ለውጥ አልታየበትም፡፡
ከዚህም ሌላ የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ በፆታ ልዩነት ተዛምዶ እንዳለውና እንደሌለው ለመመርመር የተደረጉ ጥናቶች አሉ፡፡ ዊዊ (2009) በቻይና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የፆታ ልዩነት ከአንብቦ በመረዳት ችሎታ ጋር ያለውን ተዛምዶ መርምረዋል፡፡ በመጠይቅና በክለሳ ድርሳን ሪፖርት የተሰበሰቡት መረጃዎች እንዳመለከቱት ሴት ተማሪዎች ከወንድ ተማሪዎች በተሻለ ሁኔታ ብልሐቶችን በመጠቀም፣ የንባብ ጭንቀትን በመቋቋም እንዲሁም አንብቦ በመረዳት ችሎታ የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሮዊል (1972) የማንበብ አመለካከትን የሚለውጡ ምክንያቶችን ለመመርመር ጥናት አድርገዋል፡፡ በጥናታቸውም የማንበብ አመለካከት አንብቦ ከመረዳት ችሎታ፣ ቃላትን ከመለየት፣ ከፆታ፣ ከዕድሜና ከማሕበራዊ ደረጃ ጋር ያለውን ተዛምዶ አጥንተዋል፡፡ ተመራማሪው የጥናቱን ተሳታፊዎች በሙከራ ቡድንና በቁጥጥር ቡድን በመከፋፈል ከሰበሰቡት መረጃ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው የማንበብ አመለካከት በፆታ፣ በዕድሜና በማህበራዊ ደረጃ ተዛምዶው በስታስቲክስ ጉልህ ልዩነት አልተገኘበትም፡፡ ልዩነት የታየው ቃላትን ተገንዝቦ በመለየት ላይ ነው፡፡
በጥናቶቹ እንደተጠቆመው የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ እንዳይጎለብት የሚያደርጉት ምክንያቶች አዎንታዊ የማንበብ አመለካከት እንዲዳብር ትኩረት ባለመሰጠቱ፣ መምህራን የበርካታ ተማሪዎቻቸውን የማንበብ አመለካከት ዝንባሌ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ማከናዎናቸው እንዲሁም ወላጆች ማንበብን የትርፍ ጊዜ ተግባር አድርገው መቁጠራቸው ናቸው (ሮዊል 1972፣ ዊዊ 2009)፡፡                    
ከዚህ በተለየ አቡ-ራቢያ (1996) አመለካከቶችና ባሕላዊ ዳራ በሁለተኛ ቋንቋ አንብቦ ከመረዳት ችሎታ ጋር ያላቸውን ተዛምዶ ከሶስት ማሕበራዊ አውዶች ጋር በማነፃፀር ጥናት አድርገዋል፡፡ በጥናቱ ከተሳተፉት እስራኤላዊ አረብ፣ እስራኤላዊ አይሁድና ካናዳዊ አረብ ተማሪዎች የተገኘው ውጤት እንደሚያስረዳው በራሳቸው ባሕል የቀረበላቸውን ፅሁፍ የተፈተኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች የማንበብ አመለካከትና ፍላጎታቸው እንዲሁም አንብቦ የመረዳት ችሎታቸው የተሻለ ሆኖ ተገኝተል፡፡ የካናዳዊ አረቦቹ ቡድን ውጤት ከእስራኤል አረቦቹና ከአይሁድ አረቦቹ ጋር ሲነፃፀር የቴክስቱ ይዘት ሳይሆን የቴክስቱ ቋንቋ አንብቦ ለመረዳት ተፅዕኖ አሳድሮባቸዋል፡፡
በተጨማሪም ግሪአኒ (1987) የማንበብ አመለካከት፣ የመኖሪያ አካባቢና የማንበብ ፍላጎት ከማንበቢያ ትርፍ ጊዜ (leisure-time reading) ጋር ያላቸውን ተዛምዶ በሚመለከት በጥናታቸው ቃኝተዋል፡፡ ከጥናቱ የተገኘው ውጤት እንደሚያስረዳው የመኖሪያ አካባቢና የማንበቢያ ትርፍ ጊዜ ተዛምዶ አላቸው፡፡ ከሌሎቹ ተለዋዋጮች በላቀ ሁኔታ የማንበብ አመለካከት ከማንበቢያ ትርፍ ጊዜ ጋር በጥብቅ ይዛመዳል፡፡ የማንበብ ፍላጎትና የማንበቢያ ትርፍ ጊዜ ያላቸውን ተዛምዶ በሚመለከት ጥናቱ እንዳመለከተው ለመዝናኛ ንባብ ካልሆነ በስተቀር ትርፍ የማንበቢያ ጊዜ ለትምህርታዊ ንባብ ብዙም ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡
ቡክሆረስት-ሄንግና ፔሪራ (2008) በአንድ የሲንጋፖር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዓመቱ የትምህርት ማብቂያ ተማሪዎች አሉታዊ የማንበብ አመለካከት ሊያድርባቸው የቻለበትን ምክንያት አጥንተዋል፡፡ ለዚህም ትርፍ ጊዜን በንባብ ተግባር ላይ አለማዋል በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ታውቋል፡፡ በጥናቱ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው በማንበብ አመለካከት በሴቶችና በወንድ ተማሪዎች መካከል የጎላ ልዩነት አልታየም፤ ሁሉም የጥናቱ ተሳታፊዎች የማንበብ ውስጣዊ ፍላጎታቸው ግን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡
በአጠቃላይ ከጥናቶቹ ውጤት ለመረዳት እንደሚቻለው የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ተዛምዶ አላቸው የሚሉ ተመራማሪዎች አሉ ለምሳሌ ሳላበስ (2008)፣ አቡ-ራቢያ (1996)ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሌላም በኩል ተዛምዶው ቢኖርም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙ ተመራማሪዎች አሉ (ግሪአኒ 1987፣ ቡክሆረስት-ሄንግና ፔሪራ 2008)ን መጥቀስ ይቻላል፡፡
 2.3. የማንበብ አመለካከት አንብቦ ለመረዳት ያለው ሚና
ወላጆች የማንበብ አመለካከትን ለማሳደግና ለማጠናከር በመኖሪያ ቤት ውስጥ  ሁለት ሚናዎችን  ይጫወታሉ፡፡ የመጀመሪያው ሚና ማንበብን ባህላቸው አድርገው የሚነበቡ ነገሮችን በመኖሪያ ቤት ውስጥ ማስቀመጣቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ሚና በማንበብ ልምዳቸው አማካኝነት  ለልጆቻቸው አዝናኝና አስተማሪ ድርሳናትን እያነበቡላቸው ተፅዕኖ ማሳደራቸው ናቸው፡፡ ወላጆች የማንበብ ልምዳቸውን በማዳበር ለልጆቻቸውም አርአያ ከሆኑ ልጆቻቸው በመኖሪያ ቤት ውስጥ እንዲያነቡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ (ስፓይገል 1994)፡፡ ወላጆችና የመኖሪያ ቤት አካባቢ በአመለካከት ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በጎ ከሆነ በትምህርት ቤት አወንታዊ አመለካከትን ለማጠናከር ለሚደረገው ጥረት በቅርበት አብሮ ለመስራት ያግዛቸዋል (አሌክሳንደርና ፊለር 1976)፡፡
በተጨማሪም ስችማይት (2009) የተማሪዎችን አወንታዊ የማንበብ አመለካከቶች ማሳደጊያና ማጠናከሪያ ናቸው በማለት የሚዘርዝሯቸው 5 መንገዶች አሉ፡፡ እነሱም በመኖሪያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ወላጆች፣ በትምህርት ቤት አካባቢ ያሉ የመማሪያ ክፍሎች፣ በተለያዩ መሳሪያዎች የሚሰበሰቡ የአመለካከት ግምገማዎች፣ የማስተማር ልምዶች፣ የተማሪዎችና የመምህራን አመለካከትና ባህሪያት ናቸው፡፡
ይህንን ሀሳብ በመቃረን ክራመር (1994)፣ ዊየርና ዊየር (1994)ና ብሮፊ (2004) የማንበብ አመለካከትን ለማሳደግና ለማጠናከር የሚቻለው በመኖሪያ ቤት ሳይሆን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ብቻ ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ ለዚህ አባባላቸው በምክንያትነት የሚጠቅሱት የመምህራንና የተማሪዎች የመማሪያ ክፍል ውስጥ ተራክቦ፣ ንቁ የሆነ የመማር መነሳሳት ካለ፣ የመማሪያ መፃሕፍት  በተማሪዎች ፍላጎት መሰረት ከተመረጡ፣ መምህራን በተማሪዎች የመማሪያ ክፍል ውስጥ ቤተ- መፃህፍት ካዘጋጁ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ብቻ የማንበብ አመለካከትን ማሳደግና ማጠናከር ይቻላል፡፡
በዚህ ሀሳብ የማይስማሙት ማክኪና፣ ኪአርና ኢልስዋርዝ (1995) የመምህራንና የተማሪዎችን አመለካከቶችና ባህሪያት ጠንቅቆ በማወቅ የማንበብ አመለካከትን ማሳደግና ማጠናከር ይቻላል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸውን አዎንታዊና አሉታዊ ምክንያት በመገንዘብ ለችግሮቹ መፍትሔ ፈልጎ ያላቸውን ማጠናከር፣ የሌላቸውን መፍጠር ይቻላል፡፡ ልጆች በመኖሪያ ቤትም ሆነ በትምህርት ቤት በትርፍ ጊዜያቸው እንዲያነቡ ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸው፣ ወላጆችና መምህራን ደካማና ጎበዝ እያሉ በአንባቢያን መካከል ልዩነት ካልፈጠሩ፣ መምህራን በትምህርት ቤት ውስጥ  ጎበዝ ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸው አዎንታዊ ሲሆን፣ የሰነፍ ተማሪዎች ግን አሉታዊ ነው በማለት ተማሪዎችን ካልከፋፈሉ፤ በፃታ ፣በዕድሜና በጎሳ አማካኝነት የማንበብ  ተፅዕኖን አጥንቶ መፍትሔ ከተፈለገ የማንበብ አመለካከትን የትም ቢሆን ማሳደግና ማጠናከር ይቻላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ራሲኒስኪና ፓዳክ (2000) እንዳመለከቱት የተማሪዎች ንባብ ስኬታማ እንዲሆን መምህራን መፃሕፍትን ማንበብ በመውደድ አርዓያ ሊሆኗቸው ይገባል፡፡ መምህራኑ ለተማሪዎቻቸው የማንበብ አርአያ ከሆኑ፣ በመማሪያ ክፍል ውስጥ የማንበብ ፍላጎትን ለማነሳሳት ተቀባይነት ያገኛሉ፡፡ አርአያ በሚሆኑበት ወቅት ከመምህራኑ የሚጠበቀው ክንውን ተማሪዎቻቸው በዝምታ ንባብን ሲያነቡ እንዲመለከቷቸው ማድረግ ሳይሆን፣ ካነበቡት ምንጭ እየጠቀሱ ማንበብ ሕይወታቸውን እንዴት እንደለወጠው ለተማሪዎቻቸው ቢነግሯቸው ተማሪዎችም ከማንበብ የሚገኘውን ጥቅም በመረዳት አንባቢ የመሆን አመለካከታቸው ሊያድግና ሊጠናከር ይችላል፡፡ ጋምብሪል (1996) እንዲሚገልፁት፣ ተማሪዎቻቸው ፈላስፋ፣ ተማራማሪ፣ ደራሲና ሐያሲ እንደሚሆኑላቸው የሚመኙ መምህራን እነሱም ተፈላሳፊ፣ ተመራማሪ፣ ተባባሪ፣ አንባቢ፣ ፀሐፊና ገምጋሚ መሆን አለባቸው፡፡
በተመሳሳይ ራስኒስኪና ፓዳክ (2000) እንዳመለከቱት ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከት አዎንታዊ እንዲሆን የሚፈልጉ መምህራን እነዚህን አራት ጠቃሚ ዕምነቶች አዋህደው መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነሱም(1) ሁሉም ተማሪዎቻቸው ለመማር እንደሚፈልጉ ተስፋ ማድረግ፤(2) ተማሪዎች ወደ መማሪያ ክፍል ይዘዋቸው የሚመጡትን ከማንበብ ጋር የተያያዙ ነገሮች ትኩረት መስጠት፤(3) ተማሪዎች በንባብ ትምህርት ተግባራት ከማይተገብሩት ይልቅ የሚተገብሩትን ተግባር በትኩረት መቃኘት፤(4) በተማሪዎች ፍላጎትና ጠቀሜታ ላይ ተመስርቶ የተቃኘ ማስተማር፣ መማርን ቀላል  እንደሚያደርገው ማመን ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በምርምሮቹ እንደተገለፀው የማንበብ አመለካከት ለተማሪዎች የማንበብ አመለካከት ሚናው የጎላ ነው፡፡ መምህራንና ወላጆች አዘውትረው ለማንበብ ያላቸው አመለካከት አሉታዊ ከሆነ ተማሪዎችም ለማንበብ ያላቸው አመለካከት እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ስለዚህም የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት እንዲያድግና እንዲጠናከር የተማሪዎች፣ የወላጆችና የመምህራን አመለካከት አዎንታዊ መሆን አለበት፡፡

No comments:

Post a Comment