ምዕራፍ አንድ፡- መግቢያ
1.1.የጥናቱ ዳራ
ከ1940 እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ ባሉት ዓመታት ማንበብን በሚመለከት የተለያዩ የንባብ ንድፈ ሐሳቦች ተቀርፀዋል፡፡
ንድፈ ሐሳቦቹ አንባቢያን በተፈጥሮ ባሕሪ፣ በአካባቢ፣ በመኖሪያ ቤትና በትምህርት ቤት ተፅዕኖ ምክንያት የማንበብ ልምዳቸው እንዴት
ሊጎለብት እንደሚችል የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ለዚህ በምሳሌነት የሚጠቀሱት የንባብ ንድፈ ሐሳብ ዕይታዎች አቅመ ንባባዊ (Maturational)፣ ተፈጥሯዊ (Nativist)፣ እድገታዊ
(developmental)፣ መገናኛዊ (Connectionist)፣ የስነ ልቦናዊ ስነልሳናዊ (Psycholingustics)፣ ውልደታዊ
(Emergent)፣ የማሕበረ-ባሕላዊና (Socio-cultural)፣ የማሕበራዊ ዕውቀት ግንባታ (social constructivist) ናቸው (ብላክ 2006)፡፡
በመጀመሪያ ከ1940 እስከ 1960ዎቹ ባሉት ዓመታት የአቅመ ንባብ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡
ብላክ (2006) እንዳመለከቱት የንድፈ ሐሳቡ ዕይታ ትኩረት ወጣት ተማሪዎችን መደበኛ ንባብ ማስተማር ከመጀመር በፊት የንባብን ዕውቀት የሚረዱበት የአቅም ደረጃ ላይ መድረስ አለባቸው የሚል
ነው፡፡ ተማሪዎች በንባብ ትምህርት ዕውቀትና ክሂል ከማዳበራቸው በፊት በቅድመ ትምህርት ቤት ደረጃ የተወሰነ የንባብ ፅንሰ ሐሳብን
ቀድመው ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ለማንበብ ዝግጁ የሆኑት ተማሪዎች መደበኛ የንባብ ትምህርት በሚማሩበት ወቅት ለትምህርቱ እንግዳ አይሆኑም፡፡
ለንባብ ትምህርት ዝግጁነት የሌላቸውን ተማሪዎች ማስተማር ደግሞ አዕምሯዊ ጉዳት ያመጣባቸዋል ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ገሰል
(1965) የተባሉት ተመራማሪ የዚህ ንድፈ ሐሳብ ተከታይ ነበሩ፡፡
በመቀጠል ከ1950 እስከ 1980ዎቹ ታዋቂነት አግኝቶ የነበረው ተፈጥሯዊ የንባብ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ነበር፡፡
ብላክ (2006) እንደገለፁት የንድፈ ሐሳቡ አፍላቂዎች (ቾሞስኪ 1957፣ እና ፍሮብል 1897) ናቸው፡፡ ተመራማሪዎቹ እንደሚያምኑት
የሰው ልጆች ቋንቋን ለመልመድ ይዘውት የሚወለዱት መሳሪያ እንዳላቸው ሁሉ ንባብን የሚማሩ ተማሪዎችም ልምዳቸውን ለማዳበር የማያቋርጡና
የተጠራቀሙ ደረጃዎችን ማለፍ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ተማሪዎች የማሕበራዊና ባሕላዊ ቋንቋቸውን ተፈጥሯዊ መርሐ ግብር ቋንቋን ለመልመድ
ይጠቀሙበታል፡፡
የተፈጥሯዊ ንባብ ንድፈ ሐሳብን ተከትሎ የዕድገታዊ ንባብ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ዝነኛ ሆኖ የነገሰው ከ1960
እስከ 1980ዎቹ ባሉት ዓመታት ነበር፡፡ በወቅቱም የንድፈ ሐሳቡ አፍላቂዎች ዕይታ ያተኩር የነበረው በአካባቢ ቅድመ ንባብ ተግባራት
ላይ ነበር፡፡ በሽልማትና በቅጣት ተማሪዎች ከስሕተታቸው እንዲማሩ በማድረግ ለንባብ ዝግጁ እንዲሆኑ ባህሪያቸውና ልምዶቻው ይቀረፁ
ነበር፡፡ የተማሪዎቹ የንባብ ዝግጁነት የሚመሰረተው በአወንታዊና አሉታዊ ልምዶቻቸው ላይ ነበር፡፡ በዚህ ንድፈ ሐሳብ ተማሪዎች ንባብን
አዘውትረው ከተማሩ የማንበብ ፍላጎታቸው ይጨምራል ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ቶርንዳይክ (1971) እና ስኪነር፣ ዌልቦርንና ኮኒል
(1990) የንድፈ ሐሳቡ ተከታዮች ናቸው (ብላክ 2006)፡፡
እንዲሁም ከ1960 እስከ 1980 ባሉት ዓመታት የንግግር ድምፆችን መሠረት በማድረግ የመገናኛዊ ንድፈ ሐሳብ
ዕይታ ገኖ ነበር፡፡ በወቅቱ መምህራን በመማሪያ ክፍል ውስጥ የህትመት ውጤቶችን በማቅረብ የንባብ ትምህርትን ለማነሳሳት ጥረት ያደርጉ
ነበር፡፡ የመገናኛዊ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ንባብን ተግባር ላይ ያውሉት የነበረው በታሕታይ-ላዕላይ ሞዴል ነበር፡፡ በዚህም በፊደልና በድምፆች አማካኝነት
የቃላትን ትርጉም በቀጥታ በማስተማር በተግባር ላይ ይውላል፡፡ ተማሪዎቹ በትንሹ ጀምረው ንባብ ይማሩና ቀስ በቀስ በሰፊው እንዲያነቡ
ሰፋፊ ፅሁፎች ይቀርቡላቸዋል፡፡ አንባቢዎቹ ኮዱን ከንባቡ ጋር እያገናኙ አንድ ጊዜ ከተማሩት እያንዳንዱን ቃል ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት ማንበብ ይችላሉ፡፡ የዚህ
ንድፈ ሐሳብ ተከታዮች ፍለስች (1955) እና አዳምስ (1990) ናቸው በማለት ብላክ (2006) ያስረዳሉ፡፡
ከዚያም የስነ ልቦናዊ ስነልሳን ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ከ1980 እስከ 1990ዎቹ በነበሩት ዓመታት ተቀባይነት
ያገኘ ንድፈ ሐሳብ ነበር፡፡ ብላክ (2006) እንዳብራሩት እንደዚህ
ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ተማሪዎች ንባብን በመማር ሒደት በንቃት ስለሚሳተፉ አንብቦ ለመረዳት አይቸገሩም፡፡ ምክንያቱም ንባቡን የሚማሩት
በማህበራዊና ባሕላዊ ቋንቋቸው በመጠቀም ነበር፡፡ የንባብ ተግባራት የዕውነተኛና የተጨባጭ ችግር መፍቻ ተደርገው ይታሰቡ ነበር፡፡
ተማሪ ተኮር የሆነው የንባብ ትምሕርት የመማር ተግባራቱና የሚቀርበው ፅሁፍ በዕውነተኛ ሕይወት ላይ ማትኮራቸው ተማሪዎች ለንባባቸው
ትርጉም እንዲሰጡት አድርጓል፡፡ በዚህ ንድፈ ሐሳብ ንባብን ለማስተማር ላዕላይ- ታሕታይ ዘዴ ትኩረት ይሰጠው ነበር፡፡ የንድፈ ሐሳቡ ዋነኛ ተከታይ ጉድማን (1968) ናቸው፡፡
የውልደታዊ ንባብ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ታዋቂነትን ያገኘው ከ1980 አስከ 1990 ባሉት ዓመታት ነበር፡፡ እንደ
ብላክ (2006) አገላለፅ በዚህ ንድፈ ሐሳብ የፊደልና የንባብ ክህሎት ፅንሰ ሐሳብ የሚጀመረው ከውልደት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን ተማሪዎች
በዕውነተኛ ሕይወት የንባብ ተግባራት ላይ ከተሳተፉ እስከ ጎልማሳነት ዕድሜያቸው ድረስ ይዘልቃል የሚል እምነት አለ፡፡ ለመጀመሪያ
ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት የመጡት ሕፃናት ስለ ንባብ ያላቸው ግንዛቤ የተለያየ ነው፡፡ ይህም ከማንበብ ዝግጁነታቸው ጋር ይያያዛል፡፡
ፒያጄት (1952) እና ክሌይ (1952) የንድፈ ሐሳቡ ዕይታ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው፡፡
ብላክ (2006) እንዳመለከቱት ቆየት ብሎ በ1990ዎቹ አገልግሎት ላይ የዋለው የንባብ ንድፈ ሐሳብ የማህበራዊ ዕውቀት ግንባታ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ነው፡፡ ንድፈ ሐሳቡ የሚያተኩረው
የንባብ ዕድገት የማያቋርጥ ሒደት መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከውልደት ጀምሮ በተለያየ መጠን እያደገ በመሄድ እስከ ሕይወት መጨረሻ ይዘልቃል፡፡
ይህ የሚከናወነው ከሌሎች ቋንቋ ተጠቃሚዎች ጋር ንቁ ተራክቦ በማድረግ ነው፡፡ ተማሪዎች አዳዲስ የንባብ ክሂሎችን የሚለምዱት ሆን
ብለውና ሳያስቡት ሊሆን ይችላል፡፡ የንባብ ተግባርና ሚናቸውን የሚወጡትም ከቤተሰቦቻቸው፣ ከማህበረሰቡ ባህላዊና ማህበራዊ አካባቢዎች
ነው፡፡ ቪጎትስኪ (1978) በዚህ ንድፈ ሐሳብ ተከታይነታቸው ይታወቃሉ፡፡
በመጨረሻም የማሕበረ-ባሕል የንባብ ንድፈ ሐሳብ ከ1990ዎቹ ቀደም ብሎ እስከ አሁንም ድረስ ተቀባይነት ማግኘቱን
አላቋረጠም፡፡ የንድፈ ሐሳቡ የዕይታ ትኩረት እንደሚያመለክተው የተማሪዎች የቋንቋ ባለቤትነት ልምድ በመኖሪያ ቤት፣ በትምህርት ቤት፣
በባሕልና በማህበረሰብ አካባቢ እኩል አይደለም፡፡ እያንዳዱ ማሕበራዊና ባሕላዊ አውድ የራሱ የሆኑ ልዩ ልዩ ልምዶችና የንባብ ባሕሎች
አሉት፡፡ ተማሪዎችም በቤተሰባቸው ታሪኮችና ባህላዊ ልምዶች አስተሳሰብ ስለሚቀረፁ በመማሪያ ክፍል ተግባራቶች ላይ ይህንኑ ያንፀባርቃሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ንባብ በሚማሩበት ወቅት
ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በዚህ ንድፈ ሀሳብ አመንጭነታቸውና ተከታይነታቸው የሚታወቁት ቦርዲዩ (1997)፣ ፍሪቦዲና ሉኪ
(1990) እና ፍሪሪ (1973) ናቸው በማለት ብላክ (2006) አስረድተዋል፡፡
ከላይ በዝርዘር ከተጠቀሱት ንድፈ ሀሳቦች በተጨማሪ አመለካከት በተማሪዎች
የንባብ ትምህርትም ሆነ ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ አመለካከት በልምድ አማካኝነት የተደራጀ መልስ የመስጠት ዝግጁነት ነው
(ኢሰር 1994)፡፡ በሰዎች ባህሪ ላይ ተለዋዋጭ ተፅዕኖን የማሳደር አዕምሯዊና ስሜታዊ ስርዓትም ነው (ሊንዲዝና አሮንሰን
1996)፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚማሩት፣ አብሯቸው የሚቆይ፣ በነገሮች፣ በአስተሳሰቦች፣ በሁኔታዎች ወይም
በሰዎች ላይ የሚታይ አወንታዊ ወይም አሉታዊ ግምገማ ነው (ስኪነር 1989)፡፡ ስሜታዊ ይዘት፣ ጠቃሚ ዕምነቶች፣ ቅድመ ጥላቻዎች፣
ወደ አንድ ጎን የማድላት ዝንባሌ፣ አድናቆቶችና ሌሎችም የአመለካከት ምንነት የሚገለፅባቸው ናቸው (ፊልድማን 1996)፡፡ ከማንበብ
ጋር በተያያዘ የማንበብ አመለካከት ማለት ንባብን የመውደድና የመጥላት ስርዓታዊ ስሜት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ አንባቢ ሳይንሳዊ ልቦለድን
ማንበብ ሲወድ፣ ሌላው አንባቢ የፍቅር ልቦለድ ማንበብ ሊወድ ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አንድ ሰው በተለያዩ ሁኔታዎች ማንበብን
እንዲጠላ ወይም እንዲወድ ስለሚደረግ ነው (ፍለድና ላፕ 1983፣ ማክኪና ኪአርና ኢልስዎርዝ 1995)፡፡
ፊልድማን (1996) እንደሚያስረዱት አመለካከት ስሜታዊ፣ ባህሪያዊና አዕምሯዊ
የሚባሉ ሶስት ክፍሎች አሉት፡፡ ስሜታዊ ክፍል የሚይዘው አወንታዊም
ሆነ አሉታዊ ስሜቶች በአንድ ነገር ላይ እንዴት እንደሚፈጠሩ የሚታወቅበትን ክፍል ነው፡፡ ባህሪያዊ ክፍል አመለካከት ጠቃሚ የሆነ
የተለዬ ተግባር ለማከናወን በሰዎች ውስጥ ያለን ቅድመ ጥላቻ ወይም ዕቅድ ይመለከታል፡፡ አዕምሯዊ የሚባለው ክፍል ደግሞ የሚያካትተው
ሰዎች አመለካከታቸውን ፣ ዕምነታቸውን ወይም ሀሳባቸውን ዕውን አድርገው
የሚይዙበትን ነው፡፡ የዝምድናቸው መጠን ከፍና ዝቅ ይል እንደሆን እንጅ ማንኛውም አመለካከት በነዚህ ሶስት ክፍሎች ቅንጅት የሚካሄድ
ነው፡፡ ቫካ እና ቫካ (1999) የማንበብ አመለካከትን ከስሜታዊ፣ ከባህሪያዊና ከአዕምሯዊ ክፍሎች ጋር ያለውን ጥምረት እንዳመለከቱት
የማንበብ አመለካከት ሦስት መሰረታዊ ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ክፍል አንባቢዎች ስለማንበብ ያሏቸው ግምገማዎች ወይም ስሜቶች
ስሜታዊ የማንበብ ክፍል ነው፡፡ ሁለተኛው ክፍል አንባቢዎቹ አንድን ንባብ ለማንበብ ሲያስቡና ንባብን በተግባር ሲያውሉት የማንበብ
አመለካከታቸውን ባህሪያዊነት ይገለፃል፡፡ በሶስተኛው አዕምሯዊ ክፍል
የሚከናወኑት ደግሞ አንባቢያን ስለማንበብ ያላቸው አስተያየቶች ወይም
ስሜቶች ናቸው፡፡
ፊልድማን (1999) እንደገለፁት አመለካከትን ለመበየን የሚያገለግሉ ሶስት
ዓይነት ንድፈ ሐሳቦች አሉ፡፡ ከእነሱም መካከል ተግባራዊ ንድፈ ሀሳብ የመጀመሪያው ነው፡፡ የተግባራዊ ንድፈ ሐሳብ አመንጭዎች እንደሚያምኑት
አመለካከቶችን መማር የሚቻለው ፍላጎቶችን ለማርካት ሲባል ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ አዕምሯዊ ንድፈ ሀሳብን ያፈለቁት እንደሚያብራሩት ደግሞ የአመለካከቶች መሰረት
መረጃ ነው፡፡ ከዚህ አመለካከታቸው የተነሳም አላማቸውን የሚቀርፁት ከልምዳቸው፣ ከሌላ አካልና ከውሳኔ በመነሳት ነው፡፡
በሶስተኛነት ንድፈ ሀሳብን ያፈለቁት የባህሪያዊያን ንድፈ ሀሳብ ባለቤቶች እንደሚሉት በአንድ ወቅት ክስተት በተፈጠረ የጥሩ ወይም
የመጥፎ ስሜት አጋጣሚያዊ ክስተትን ከሌሎች በመመልከት አመለካከት ይቀረፃል፡፡ ለምሳሌ ከቤተሰብና ከብዙሐን መገናኛ ሊሆን ይችላል፡፡
አመለካከት የሚበየንባቸውን ንድፈ ሐሳቦች መሰረት አድርገው አመለካከትና
ማንበብ ያላቸውን ዝምድና የሚያረጋግጡ ሶስት የንድፈ ሀሳብ ሞዴሎችን ተመራማሪዎች ቀርፀዋል፡፡ ሞዴሎቹ የማዚውሶን፣ የሩድል ስፒከርና
የማኬና ሲሆኑ፣ እነሱም በተለይ በማንበብ ሂደት ወቅት አመለካከት ከአንባቢያን ስሜት ጋር ያለውን ዝምድና ይገልፃሉ፡፡ የማዚውሶን
ሞዴል (1985) የሚያካትታቸው የአመለካከት ስሜታዊ ሂደቶች ፍላጎት፣ ዕሳቤና አካላዊ ስሜቶች ናቸው፡፡ ሩድልና ስፒከር በማዚውሰን
ሞዴል ላይ የቃላት ግንዛቤ በሚል በሞዴላቸው ላይ ንዑስ ሂደት በማካተት
ለማሻሻል ሞክረዋል፡፡ የሁለቱን ንድፈ ሀሳባዊ ሞዴሎች (የማዚውሶንና የሩድል ስፒከር ሞዴሎች) ያሉባቸውን ችግሮች በመመርመር
(ማኬና 1994) የተባሉት ተመራማሪ አዲስ የማንበብ አመለካከት ንድፈ ሐሳባዊ ሞዴል ይዘው ብቅ ብለዋል (ስችማይት 2009)፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የሶስቱ ንድፈ ሀሳባዊ ሞዴሎች ባለቤቶች የማንበብ አመለካከት
እንዴትና ለምን እንደሚፈጠር በጥናታቸው ግኝት አብራርተዋል፡፡ ማዚውሶን (1994) እንዳመለከቱት አንባቢያንን ለማንበብ እንዲወስኑ
የሚያደርጓቸው ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ውጫዊ አነሳሾችና ውስጣዊ
ግለሰባዊ ስሜቶች ናቸው፡፡ እነዚህም የሚያካትቱት የይዘትና የአላማ ግምገማ፣ የተለየና አዲስ አይነት ንባብ የማንበብ ፍላጎት እንዲሁም
የንባብ ተግባርን ለማከናወን መነሳሳት ናቸው በማለት ተመራማሪው ጠቅሰዋቸዋል፡፡ የሩድል ስፒከር (1995) ሞዴል አራት ተራክቧዊ ክፍሎች አሉት፡፡ እነሱም የአንባቢው አካባቢ፣ የዕውቀት አጠቃቀምና
ቁጥጥር፣ ሥርዓታዊ ዕውቀትና የአንባቢው ውጤት ናቸው፡፡ የአንባቢው አካባቢ ለንባብ የቀረበውን ፅሁፍ፣ ውይይቶችንና የማስተማር ገፅታዎችን
ያካትታል፡፡ እነዚህ የተራክቦ ክፍሎች በመረጃውና በሥርዓቱ ሒደቶች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ከፍተኛ ፍላጎት የሚቀሰቅስ ፅሁፍ ዝቅተኛ
ፍላጎት ከሚያነሳሳ ፅሁፍ ጋር ሲወዳደር የሚያሳድረው የማንበብ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ የማክኪና (1994) ሞዴል ንድፈ ሀሳብ
ለአመለካከት ለውጥ ዋና ዋና የሚባሉት ሶስት ምክንያቶች ፡- (1) አንባቢዎች ስለንባብ ውጤቱ ያላቸው ዕምነቶች፤ (2) ከንባቡ
የሚጠብቁት እምነት ፍላጎታቸውን ለማነቃቃት ያለው ስምምነትና፤ (3) ከንባብ አጋጣሚዎቻቸው የተለየ ውጤት መጠበቃቸው በማለት ይዘረዝራሉ፡፡
አመለካከት ለምንና እንዴት እንደሚፈጠር ተመራማሪዎች የደረሱበትን ውጤት
ተመርኩዘው አወንታዊ የማንበብ አመለካከት በወላጆችና በመኖሪያ ቤት አካባቢ፣ በመማሪያ ክፍል ውስጥ፣ በተማሪዎች አመለካከቶችና ባሕሪ፣ እንዲሁም በመምህራን አማካኝነት እንዴት ማሳደግና ማጠናከር
እንደሚቻል አስተያየት ያላቸው ተመራማሪዎች አሉ፡፡ ሁሉም እንደሚስማሙበት የማንበብ አመለካከት እያደገና እየተጠናከረ መሄድ የሚጀምረው
በአብዛኛው በወላጆች አማካኝነት ነው (ስፒገል 1994፣ አሌክሳንደርና ፊለር 1976፣ ክላመር 1994፣ ማክኬና ኪአርና ኤልስዎሪዝ 1995፣ ራስንስኪና ፓዳክ 2000)፡፡
ስፒገል (1994) እንዲሚያስረዱት ወላጆች ለልጆቻቸው የማንበብ አመለካከት
አወንታዊ መሆንና የንባብ ስኬታማነት ዋነኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ወላጆች ከሚጫወቷቸው ሁለት ሚናዎች መካከል አንደኛው በመኖሪያ ቤት
አካባቢ የሕትመት ውጤቶችን ለልጆቻቸው በማቅረብ የልጆችን የማንበብ ፍላጎት ማነሳሳት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ መፃሕፍትን በመኖሪያ
ቤት እያነበቡላቸው መልካም አርአያ መሆን ናቸው፡፡ አሌክሳንደርና ፊለር (1976) እንደሚገልፁት የወላጆችና የመኖሪያ ቤት አካባቢ
ለማንበብ አመለካከት ጠቃሚ አስተዋፅኦ ማበርከቱ አወንታዊ አመለካከትን በማጠናከር ከትምህርት ቤቶች ጋር በቅርበት ለመስራት ጠቃሚ
ነው፡፡ ወላጆች የልጆቻቸውን የማንበብ አመለካከት እንዴት መለወጥ እንደሚቻል ዕውቀቱ ከሌላቸው በመምህራኑ አጋዥነት ተሳትፎ እንዲያደርጉ
ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡
ከወላጆች በተጨማሪ የመማሪያ ክፍል አካባቢ በወጉ መደራጀቱ ለተማሪዎች የማንበብ
አመለካከት በጎነት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ አለ (ክራመር 1994፣ አሌክሳንደርና ፊለር 1976)፡፡ አወንታዊ የማንበብ አመለካከት
መፍጠሪያ አንዱ መንገድ የንባብ ቁሳቁስን በብዛት በመምረጥ በክፍል ውስጥ ማስቀመጥ ነው፡፡ መምህራኑ በውሰት መፃህፍትም ቢሆን እንኳ
በመማሪያ ክፍል ውስጥ ቤተ-መፃህፍት ለመክፈት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ በመማሪያ ክፍል ቤተ-መፃህፍቱ ተማሪዎቹ የንባብ ናሙናዎችን
በማንበብ ፍላጎታቸው ሊነሳሳ ይችላል፡፡ ይሁን እንጅ በቤተ-መፃህፍቱ ለተማሪዎቹ የሚቀርቡት መፃህፍት በፍላጎታቸው መሰረት መሆኑ
ግምት ውስጥ ካልገባ ተማሪዎቹ አወንታዊ የማንበብ አመለካከትን አያዳብሩም፡፡ ይህ እንዳይሆን መምህራን ከመማሪያ መፃህፍቱ በተጨማሪ
እያዝናኑ የሚያስተምሩ መፃህፍት፣ መፅሔትና ጋዜጦች በቤተ-መፃህፍት ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡
በሌላም በኩል የተማሪዎች አመለካከቶችና ባህሪ የማንበብ አመለካከት አወንታዊ
እንዲሆን ምክንያት ይሆናል (ማክኪና፣ኪአርና ኤልስዋርዝ 1995፣ አሌክሳንደርና ፊለር 1976፣ አስኮቨና ፊስችባች 1973)፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የመማሪያ ክፍሎች በመዝናኛ ንባብ ተማሪዎችን ማስተማር በትምህርታቸው ላይ አሉታዊ አመለካከት ያሳድራል የሚለው
ንድፈ ሐሳብ ጫና በማሳደሩ ክሂሉ ያላቸው አንባቢዎች ለአሉታዊ ተፅዕኖ ተጋልጠዋል፡፡ በተመሳሳይ በጠንካራና ደካማ አንባቢያን መካከል
ያለው ክፍተትም ያሳደረው ተፅዕኖ አለ (ማክኪና፣ኪአርና ኢልስዋርዝ 1995)፡፡ ክፍተቱን ለማጥበብ በዝቅተኛ የክፍል ደረጃዎች ለሚማሩ
ተማሪዎችም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ልምዱን መሰረት በማድረግ መምህራን ጎበዝ ተማሪዎችን ከደካማ ተማሪዎች ጋር እያነፃፀሩ
የማንበብ አመካከታቸውን መገመት የለባቸውም (አሌክሳንደርና ፊለር 1976)፡፡
በአጠቃላይ ከንድፈ ሐሳቦቹ ለመረዳት እንደሚቻለው የንባብ ንድፈ ሐሳቦቹ
ዕይታዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ እንደ ንድፈ ሐሳቦቹ ተከታዮች ዕምነት በተፈጥሮና በአካባቢ ተፅዕኖዎች ምክንያት የማንበብ ልምድ እየዳበረ
ይሄዳል፡፡ በነዚህ ብቻ ሳይሆን በአንባቢዎች አመለካከትም በሚደርስ ተፅዕኖ ንባብን የመውደድና የመጥላት ስሜት ሊፈጠር ይችላል፡፡
የማንበብ አመለካከት በልምድ ወይም በመማር ምክንያት ሰዎች ለአንድ
ነገር የሚኖራቸው አወንታዊ ወይም አሉታዊ አመለካከት ሲሆን፣ ስሜታዊ፣
ባሕሪያዊና አዕምሯዊ ክፍሎችንም ይይዛል፡፡ በተጨማሪም አንባቢዎች ለአንድ ንባብ የሚኖራቸው የመውደድና የመጥላት ሥርዓታዊ ስሜት
ነው፡፡ ይህም በተማሪዎች ባህሪ፣ በወላጆች፣ በመምህራን፣ በቤተሰብና በአካባቢ ተፅዕኖዎች ምክንያት እየጎለበተ ይሄዳል፡፡ ይሁን
እንጅ የሚካሄደው ጥናት አመለካከትና ማንበብ ያላቸውን ዝምድና ከሚያረጋግጡት
ሶስት የንድፈ ሐሳብ ሞዴሎች መካከል በአሁኑ ዘመን ተቀባይነት ያገኘውን የማኬና (1994) ሞዴል ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ሞዴሉ መሠረት የሚያደርገው
አንባቢዎች ስለንባብ ውጤቱ ያላቸውን ዕምነቶች፣ ከንባቡ የሚጠብቁት እምነት ፍላጎታቸውን ለማነሳሳትት ያለውን ስምምነትና ከንባብ
አጋጣሚዎቻቸው የተለየ ውጤት መጠበቃቸውን ነው፡፡ የዚህም ጥናት ትኩረት በባሕር ዳር ከተማ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ቤት በ10ኛ ክፍል ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለውን ተዛምዶ መመርመር ነው፡፡
1.2.የጥናቱ መነሻ ችግር
በማንበብ አመለካከት ላይ በማተኮር ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች
እንደሚገልፁት የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት አወንታዊና አሉታዊ በማድረግ ተፅዕኖ የሚያደርሱ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ እነሱም
የመኖሪያ አካባቢ፣ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤትና ፆታ ናቸው (ብላክቢ 2006)፡፡ ከተመራማሪዎቹ መካከል ዱቢንና ዞርካኢያ
(2010) እንዲሁም ሊን (2010) የመኖሪያ አካባቢዎች በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ያመጣሉ በሚለው ሐሳብ ተቃራኒ አስተያት
አላቸው፡፡ ዱቢንና ዞርካኢያ (2010) ባደረጉት ምርምር በአንድ አካባቢ ለማንበብ ምቹ ሁኔታዎች ካልተሟሉ በማንበብ አመለካከት
ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ተመራማሪዎቹ በጥናት ውጤታቸው እንዳመለከቱት አንባቢዎች ለመፃሕፍት መግዣ
የሚሆን ገንዘብ በማጣታቸው በብዛት የቴሌቭዥን ስርጭት ስለሚከታተሉ በማንበብ አመለካከታቸው ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የመፅሔት አንባቢዎች ቁጥራቸው ቀንሷል፣ መፃሕፍትን በመደበኛነት የሚያነቡ ጥቂት ሆነው ተገኝተዋል፣ አማካይ የመፃሕፍት የቅጅ መጠን
6% በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሊን (2010) ባካሄዱት ጥናት
በገጠር ወይም በከተማ መኖር በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ እንዳለውና እንደሌለው በማተኮር ጥናት አድርገዋል፡፡ ጥናቱ
የተካሄደው በ12 የመማሪያ ክፍል ተማሪዎች ላይ ነው፡፡ የማንበብ አመለካከት ከትምህርታዊ ንባብ፣ ከመዝናኛ ንባብ፣ ከአጠቃላይ አመለካከትና
ከተጨማሪ ጥያቄዎች ጋር ተዛምዶ በተደረገው ዳሰሳ ጥናት የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው በከተማና በገጠር ትምህር ቤት ተማሪዎች መካከል ልዩነት አልታየም፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ከተለያዩ ጎሳዎች መገኘት በማንበብ አመለካከት ላይ ያለውን አዎንታዊና አሉታዊ ሚና በሚመለከት
ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች ያገኙት ውጤት የተለያየ ነው፡፡ በመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ አፍሪካዊ አሜሪካዊያን
ተማሪዎች ለማንበብ ባላቸው አመለካከትና አንብቦ በመረዳት መጠን መካከል ስላለው ዝምድና ዌብ (2009) አጥንተዋል፡፡ ተመራማሪው
የማንበብ አመለካከት ከተማሪዎች የማንበብ አመለካከት፣ ከጠቅላላ ንባብ፣ ከፆታ፣ ከንባብ ብቃት ጋር ያለውን ተዛምዶ ቃኝተዋል፡፡
በጥናታቸውም ከአምስት ግኝቶች ላይ ደርሰዋል፡፡ እነሱም (1) ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከት አወንታዊ ነው፤ (2) ለጠቅላላ
ንባብም አወንታዊ ተዛምዶ ተመዝግቧል፤ (3) ፆታ ከማንባብ አመለካከት ጋር ተዛምዶው በጣም ከፍተኛ ሆኗል፤ (4) የተማሪዎች የማንበብ
አመለካከትና የንባብ ብቃት በስታትስቲክስ ተዛምዶ አላሳየም፤ (5) ፆታ በማንበብ አመለካከትና ብቃት ላይ ተፅዕኖ የለውም፡፡ በተመሳሳይ
ማክኪና፣ ኪአርና ኢልስዎርዝ (1995) በተለያዩ
ጎሳዎች ላይ ባደረጉት ጥናት በመዝናኛና በትምህርታዊ ድርሳናት የማንበብ አመለካከት መካከል ያለው ተዛምዶ አሉታዊ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህም በሒስፓኒክ፣ በአፍሪካዊ አሜሪካውያንና በነጮች መካከል በተደረገው
ጥናት ልዩነቱ በጥቂቱ ተስተውሏል፡፡
በሌላም በኩል
ፆታ በማንበብ አመለካከት ላይ ያለውን ተፅዕኖ በተመለከተ በጥናት የተደረሰበት ውጤት ተመሳሳይ ነው፡፡ ሎጋንና ጆንስተን
(2009) ፆታ በማንበብ አመለካከት ላይ ተዛምዶ እንዳለው ይገልፃሉ፡፡
ፆታን ከማንበብ ችሎታ፣ ከንባብ ድግግሞሽና ከማንበብ አመለካከት ጋር ያለው ተዛምዶ ተቃኝቶ የተገኘው ውጤት እንደሚያመለክተው በአጠቃላይ
ሴቶች የተሻለ አንብቦ የመረዳት ችሎታ፣ ደጋግሞ የማንበብና እንዲሁም ለትምህርታዊ ንባብ አወንታዊ አመለካከት አላቸው፡፡ በጥናቱ
ውጤትም በማንበብ ድግግሞሽና በብቃት ደረጃ መካከል ተዛምዶ ታይቷል፡፡ የወንዶች የማንበብ ችሎታ ከማንበብ አመለካከታቸው ጋር ተዛምዶ
እንዳለውም በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ በተመሳሳይ ኩሽና ዋትኪንስ (1996) በፆታ ልዩነት ምክንያት በማንበብ አመለካከት ለረጅም ጊዜ
ወጥ ሆኖ በመቆየት ከወንዶችና ከሴቶች ማን የተሻለ እንደሆን መርምረዋል፡፡ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት በመቃኘት የተገኘው የጥናት ውጤት እንዳመለከተው የመዝናኛና የትምህርታዊ ድርሳናት
ወይም ፅሁፎች የማንበብ አመለካከቶች ውጤት ዝቅ ብሏል፡፡ ሴቶች ከወንዶች
ጋር ሲነፃፀሩ ለመዝናኛ ንባብ ያላቸው አመለካከት አወንታዊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የሴቶቹ የማንበብ አመለካከት ከወንዶቹ በላቀ ደረጃ
ለረጅም ጊዜ ወጥ ሆኖ የመዝለቅ ሁኔታም ታይቶበታል፡፡ በአጠቃላይ በጥናቱ እንደተጠቆመው ከወንዶቹ ይልቅ የሴቶቹ የማንበብ አመለካከት
ለረጅም ጊዜ በዘላቂነት መቆየት እንደሚችል ተረጋግጧል፡፡
ሌሎች ተመራማሪዎች
የማንበብ አመለካከትን ከማንበብ ችሎታ ውጤታማነት፣ ከማንበብ ብቃትና ከአንብቦ መረዳት ችሎታ ጋር ያለውን ተዛምዶ አስመልክተው ባደረጉት
ጥናት ያገኙት ውጤት ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ያኮቭ (2010) ባደረጉት
ጥናት በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና በንባብ ችሎታ ውጤታቸው መካከል ያለውን ተዛምዶ መርምረዋል፡፡ የተዛምዶው አማካኝ ውጤትም
መካከለኛ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ የተዛምዶው ውጤታቸው
ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ማርቲንዝና ሌሎች (2008) ከማንበብ አመለካከት ጋር በተዛመደ በማንበብ ብቃት ላይ ተፅዕኖ
የሚያሳድሩ ምክንያቶችን በጥናታቸው ለይተዋል፡፡ የስምንተኛ ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ ሳለበስ
(2008) ባደረጉት የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ተዛምዶ ጥናት ተዛምዶው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ለዚህም ተጠቃሽ
ምክንያቶቹ ተማሪዎቹ የቀረበላቸውን ንባብ በግልፅና በትክክል ለመረዳት አለመቻል፣ በአካባቢ፣ በወላጆችና በትምህርት ቤት ተፅዕኖ
አመለካከታቸው በመዛባቱ ንባብን መጥላታቸው ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የማንበብ
አመለካከትንና የአንብቦ መረዳትን ችሎታ በሚመለከት የተደረጉ ተመሳሳይና ተቀራራቢ ጥቂት ጥናቶች አሉ (ታፈረ 2000፣ ዘላለም 2010)፡፡ ጥናቶቹ እንደሚያስረዱት
አጥኝዎቹ በማንበብ አመለካከትና በአንብቦ መረዳት መካከል ተመሳሳይ ውጤት አላገኙም ፡፡ ለምሳሌ ታፈረ (2000) በተማሪዎች የማንበብ ዳራና በአንብቦ መረዳት ችሎታ
መካከል ያለውን ዝምድና መርምረው በጥናታቸው ውጤቱን እንደገለፁት በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በወላጆችና በመማሪያ መፀሐፍ አማካኝነት
በሚገኙ የንባብ ዳራዎች መካከል ጉልህ ልዩነት የታየ ሲሆን፣ ለልዩነቱ ምክንያቱ በተማሪዎች የግል ንባብ የተገኘ የንባብ ዳራ እንደሆነ
ተጠቁሟል፡፡ በዚህም የአብዛኛዎቹ ተማሪዎች የንባብ ዳራ ማግኛ መንገድ ወደ ተማሪዎች ግለ ንባብ ያመዘነ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል፡፡
በጥናቱ ተሳታፊዎች የንባብ ዳራና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ተመስርቶ በተደረገው ንፅፅርም፣ የንባብ ዳራ ማግኛ መንገዶች ከዝቅተኛ
እስከ በጣም ከፍተኛ በደረጃ ከተመደቡት የአንብቦ መረዳት ችሎታ ውጤቶች ጋር ጉልህ ተዛምዶ እንዳላቸው ጥናቱ ያሳያል፡፡ ዘላለም
(2010) በበኩላቸው ባደረጉት ጥናት የተማሪዎች የማንበብ ልምድ፣ አመለካከትና ምርጫን ቃኝተዋል፡፡ በጥናቱ ውጤት ግኝት መሰረት
የተማሪዎቹ የማንበብ ልምድ ጥሩ ሆኖ አልተገኘም፣ የማንበብ አመለካከታቸው አዎንታዊ ነው፣ ከሴቶቹ ይልቅ የወንዶቹ የማንበብ አመለካከት
የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
መሐመድ (1992) የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች የአማርኛ ቋንቋ ለመማር ያላቸውን ዝንባሌ[ አመለካከት] በሚመለከት
ባደረጉት ጥናት የተማሪዎቹ ዝንባሌ [አመለካከት] አወንታዊ መሆኑን
አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሱት (በተማሪዎች የመማር አመለካከት ላይ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ ጉዳዬች) ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣
የመምህራን የማስተማር ዕውቀትና ዘዴ፣ የተማሪዎቹ ግላዊ ችሎታና የመማሪያ መፃህፍት ተፅዕኖ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ታዛሽ
(1992) የ11ኛ ክፍል ተማሪዎችን የአንብቦ መረዳት ችሎታ አጥንተዋል፡፡ በጥናቱም የተማሪዎች አንብቦ የመረዳት ችሎታ ምን ያህል
እንደሚመሳሰልና በአንድ የክፍል ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በደረጃቸው የሚጠበቅባቸው የአንብቦ መረዳት ችሎታ ያላቸው መሆንና አለመሆኑን
መርምረዋል፡፡ በትንተናው ውጤት መሰረትም ተማሪዎች መካከለኛ የሆነ አንብቦ የመረዳት ችሎታ ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በተጨማሪም
ተማሪዎቹ በደረጃቸው የሚጠበቅባቸውን የአንብቦ መረዳት ችሎታ አካብተው ያልተገኙ ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቱ ተማሪዎች አንብቦ የመረዳት
ችሎታቸውን ለማጎልበት የሚያግዝ በቂ የሆነ ትምህርት ስለማይሰጣቸው ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ በተለያዩ ተለዋዋጮች አማካኝነት የማንበብ አመለካከትን በሚመለከት ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር በማዛመድ
የተደረጉ ጥናቶችም አሉ (ደምሰው 1995፣ ገደፋው 1993)፡፡ ደምሰው (1995) የመማሪያ መፅሐፍ ምንባቦች የተማሪዎችን የማንበብ
ፍላጎት ለመያዝ ያላቸውን ብቃት በሚመለከት አጥንተዋል፡፡ በጥናቱ ውጤት መሰረት የማንበብ ፍላጎት ምንባብን ለማንበብ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ ተማሪዎች በመማሪያ መጽሐፍ ውስጥ ላሉት ምንባቦች
ፍላጎት አላቸው፡፡ የመማሪያ መፀሐፉ ምንባቦች የተማሪዎቹን ፍላጎት የመያዝ አቅም አላቸው፡፡ በተጨማሪም ምንባቦቹ በአብዛኛው በፍላጎት
ላይ ተፅእኖ ከሚያሳድሩ መስፈርቶች አንፃር በአመዛኙ ስኬታማ ለመሆን የቻሉ ናቸው፡፡
ከዚህ ጥናት ጋር በተያያዘ ገደፋው (1993) ተማሪዎች ቋንቋን ለመማር ያላቸውን ፍላጎትና የትምህርት ውጤት
ተዛምዶ አጥንተዋል፡፡ በጥናቱ እንደተመለከተው ፍላጎትና የትምህርት ውጤት ዝምድና አላቸው፡፡ ተማሪዎች አማርኛ ቋንቋን ለመማር ያላቸው
ፍላጎት ተነሳሽነት ከፍ ሲል የትምህርት ውጤታቸው ከፍተኛ ሆኗል፡፡ በተቃራኒው ፍላጎታቸው ሲቀንስ የትምህርት ውጤታቸውም ዝቅ ብሏል፡፡
ለዚህም ምክንያቱ በመማሪያ መፀሐፍ ውስጥ የተካተቱት ምንባቦች የተማሪዎቹን ፍላጎት መሰረት አለማድረጋቸው ነው ፡፡ በሌላ በኩል
ደግሞ የመማር ፍላጎት ከቀነሰ የትምህርት ውጤት እንደሚቀንስ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ
በዝርዝር እንደቀረበው በውጭ ሐገር በተደረጉት ጥናቶች በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ መካከል ልዩነቱን
ያመላከቱ የመኖራቸውን ያህል፣ ተዛምዶ አለመኖሩንም ያሳዩ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ተመራማሪዎች በጥናታቸው የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ
መረዳት ችሎታን ተዛምዶ ከተፈጥሮ፣ ከአካባቢ፣ ከፆታና ከትምህርት ደረጃ ጋር ለማዛመድ ሞክረዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ከማንበብ ውጤትና
ከማንበብ ብቃት ጋር እያገናኙ ዝምድናውን ፈትሸዋል፡፡ ለምሳሌ ዱቢንና ዞርካኢያ (2010)፣ ሊን (2010)፣ ያኮቭ (2010)፣
ኩሽና ዋትኪንስ (1996)፣ ዌብ (2009) መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በሐገር ውስጥ ጥናቶች የታየው ክፍተት የማንበብ አመለካከት ከሌሎች ተለዋዋጮች ጋር እየተመሳከረ አልተጠናም፣ አመለካከትን ብቻውን ወይም አንብቦ የመረዳት
ችሎታን በአንድ አቅጣጫ ብቻ በመመልከት የተሰሩ ጥናቶች ናቸው፣ አንዳንዶቹ ጥናቶች ደግሞ በማንበብ ፍላጎትና በመማሪያ መፀሐፍ የንባብ
ችሎታን ከተነሳሽነት ጋር እያዛመዱ አጥንተዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ከማንበብ ምርጫቸውና ከማንበብ ልምዳቸው
ጋር በማነፃፀር ብቻ ቃኝተዋል፡፡ ለዚህም የዘላለም (2010)፣ የመሐመድ (1992) እና የታፈረ
(2000) ጥናትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህም ይህ ጥናት የተስተዋሉትን ክፍተቶች
ለመሙላት በባሕር ዳር ከተማ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ
መረዳት ችሎታ ተዛምዶ ይመረምራል፡፡
የጥናቱ ዋና ትኩረት
በባሕር ዳር ከተማ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት
ችሎታ ተዛምዶ መመርመር ሲሆን፣ በዚህም የሚከተሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ይመልሳል፡-
1.
በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ አለ?
2.
የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታቸውን የመተንበይ ድርሻው ምን ያህል ነው?
3.
በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በፆታ ልዩነት ያሳያል?
1.3. የጥናቱ ዓላማ
የጥናቱ ትኩረት
በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ መፈተሽ
ነው፡፡ የጥናቱ ንዑስ ዓላማዎች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡-
1.
በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ መኖር አለመኖሩን ለማሳየት፣
2.
የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታቸውን የመተንበይ ድርሻው ምን ያህል እንደሆነ
ለማመላከት፣
3.
በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በፆታ ልዩነት እንዳለው
ለማሳየት፣
1.4. የጥናቱ አስፈላጊነት
ይህ ጥናት በተማሪዎች
የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለውን ተዛምዶ በማሳየት መምህራን የክፍል ውስጥ የትምህርት አሰጣጣቸውን
እንዲፈትሹና እንዲያስተካክሉ ያግዛል፡፡ ስለሆነም ጥናቱ ለመምህራንም ሆነ ለትምህርት ባለሙያዎችና ለተመራማሪዎች የሚከተሉት ጠቀሜታዎች
ይኖሩታል ተብሎ ይታሰባል፡-
- የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት
በአንብቦ የመረዳት ችሎታ ያለውን የትንበያ መጠን ለመገንዘብ ስለሚያስችል ይህንን መሠረት በማድረግ የመማሪያ ክፍል የትምህርት
አቀራረብ የማንበብ አመለካከትን እንዲሚያጎለብት መምህራኑ እንዲገነዘቡት ያደርጋል፡፡
- በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና
የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በፆታና በቤተሰብ ሁኔታ ልዩነት እንዳለውና እንደሌለው ስለሚያሳይ ወላጆች
የልጆቻቸውን የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ በመገንዘብ ለችግሮቻቸው ከመምህራን ጋር በመተባበር መፍትሄ እንዲፈልጉ
ያግዛል፡፡
3. የትምህርት ባለሙያዎች
በጥናቱ ግኝቶች መረጃ መሠረት የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ በመገንዘብ መምህራን የትምህርት ዕቅድ፣
መርሐ ትምህርትና የንባብ ትምህርት መርሐ ግብር ሲያዘጋጁ የተማሪዎቹን የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ከማጎልበት
አንፃር እንዲመለከቱት ይረዳቸዋል፡፡
4. በርዕሱ ዙሪያ
ጥናት ማድረግ ለሚፈልጉ ተመራማሪዎች እንደ መነሻ በማገልገል በሥራ ላይ እንዲያውሉት ያስችላቸዋል፡፡
1.5. የጥናቱ ወሰን
ይህ ጥናት በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከከል ያለውን ተዛምዶ በመመርመር
ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በጥናቱ የሚሳተፉት በባሕር ዳር ከተማ፣ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2004 ዓ.ም. ተመዝግበው
የሚማሩ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ የተማሪዎችን ቁጥር ለመወሰን ከ10ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በዕድል ሰጭ የንሞና ዘዴ
አማካኝነት አንድ የመማሪያ ክፍል ተመርጦ የክፍሉ ተማሪዎች የጥናቱ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ጥናቱ በ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ ብቻ እንዲካሄድ የተፈለገበት ምክንያት
ተማሪዎቹ የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በመሆናቸው የዕድሜያቸው ደረጃ፣ የቤተሰባቸው ሁኔታ፣ የአስተሳሰባቸው
መጠን፣ የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታቸውን ተዛምዶ ለመለካት ተገቢ ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡ በጥናቱ የሚፈተሸው በተማሪዎቹ
የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም በፆታና በቤተሰብ ሁኔታ ልዩነት መኖር፣
በማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለውን ተዛምዶ ብቻ እንጅ ሌሎች ተለዋዋጮችን ለምሳሌ እንደ ዕድሜ፣ የምጣኔ
ሐብት ገቢና የመኖሪያ አካባቢ ሁኔታን በመመርመር ውጤቱን አያሳይም፡፡
1.6. የጥናቱ
ውስንነት
ጥናቱ በሚካሄድበት
ወቅት የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታን ተዛምዶ ለመለካት
ሊወስኑት የሚችሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነሱም ጥናቱ የሚካሄደው
በከተማ ትምህርት ቤት ላይ በመሆኑ የተዛምዶውን ውጤት ከገጠር ትምህርት
ቤት ጋር አነፃፅሮ ለመመልከት አያስችልም፤ በተጨማሪም የጥናቱ ውጤት የተማሪዎችን የማንብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ
ብቻ ስለሚቃኝ ሌሎች ተዛምዶዎችን ለምሳሌ የማንበብ ልምድና የማንበብ ምርጫን ባለማካተቱ ጉድለት ሊኖርበት ይችላል፡፡
1.7. የቁልፍ
ቃላትና የፅንሰ ሐሳብ አጠቃቀም ብያኔ
የጥናቱ ቁልፍ
ቃላት የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ሲሆኑ፣
አጠቃቀማቸውም ቀጥሎ በቀረበው ብያኔ መሠረት ነው፡፡
1.
የማንበብ አመለካከት፡- ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸውን በሚለካ መጠይቅ ሞልተው
በሰጡት ምላሽ መሠረት የሚኖራቸውን አዎንታዊ ወይም አሉታዊ አመለካከት ይመለከታል፡፡
2.
የአንብቦ መረዳት
ችሎታ፡- በጥናቱ የሚሳተፉት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ችሎታቸውን በሚለካ የአንብቦ
መረዳት ችሎታ ፈተና የሚያስመዘግቡትን ውጤት ይመለከታል፡፡
ምዕራፍ ሁለት፡- ክለሳ ድርሳን
2.1.አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ግንኙነት
አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ፡፡ ዴይና ባምፎርድ
(1982) በጥናታቸው እንደገለፁት አመለካከቶች ሰዎች አንድን ተግባር እንዲያከናውኑ ወይም እንዳያከናውኑ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ አዎንታዊ
አመለካከቶች አንድን ነገር ለማድረግ የሚያነሳሱ ሲሆኑ፣ በተቃራኒው አሉታዊ አመለካከቶች አንድን ተግባር በንቃት ለማከናወን ተነሳሽነትን ይቀንሳሉ፡፡ በተመሳሳይ የማንበብ ተግባርም ግለሰቦች ለማንበብ
ባላቸው አመለካከቶች አማካኝነት ተፅዕኖ ይደርስበታል፡፡ የማንበብ አመለካከታቸው አዎንታዊ የሆነ አንባቢያን ማንበብን መለማመድ ሲያፈቅሩ፣
ለማንበብ አሉታዊ አመለካከት ያላቸው ማንበብን ከመጥላታቸውም በላይ በማንበብ ተግባራት ለመሳተፍ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ይህ የሚያመለክተው
አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ጥናት ያደረጉት ኮንሊ (1992) እንዳብራሩት የማንበብ አመለካከት ተማሪዎች አንድን
ንባብ ለማንበብ ወይም ላለማንበብ ያላቸው ስሜት ሲሆን፣ ይህንን ተፅዕኖ የሚያሳድረው ደግሞ አመለካከት ነው፡፡ በተጨማሪም አዎንታዊ
የማንበብ አመለካከት ስኬታማ ማንበብን ሲያጎናፅፍ አሉታዊ የማንበብ አመለካከት አንባቢያን ደካማ ፍላጎት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡
አሌክሳንደርና ፊለር (1992) ጨምረው እንዳስረዱት ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከት አዎንታዊ ከሆነ የማንበብ ችሎታ ውጤታቸው
ስለሚጨምር ብዙ ያነባሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የማንበብ አመለካከታቸው አሉታዊ ከሆነ ውጤቱ የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡
ሮኢና ስሚዝ (2005) እንዳብራሩት ደግሞ ተማሪዎች ንባብን ለመማር ተግባራትን ሲያከናውኑ በሂደቱ ላይ ተፅዕኖ
ከሚያሳድሩት ነገሮች ዋነኞቹ የማንበብ አመለካከቶች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የቀረበላቸውን ምንባብ ለማንበብ በጐ አመለካከት ያላቸው
ተማሪዎች ንባብን ለመማር ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ፣ በጐ ያልሆነ አመለካከት ያላቸው ግን በሂደቱ ለመሳተፍ እንቅስቃሴያቸው ዝቅ ያለ
ነው፡፡
ተመሳሳይ ጥናት ያቀረቡት ኮንሊ (1992) እና ሜይ (1990) እንዳመለከቱት የተማሪዎችን የማንበብ አመለካት
አዎንታዊ ወይም አሉታዊ የሚያደርጉት መምህራን ናቸው፡፡ ለምሳሌ መምህራኑ በመማሪያ ክፍል ውስጥ አዎንታዊ የማንበብ አመለካከትን
የሚያጎለብቱ ልምዶችን ለተማሪዎች ካስተዋወቁ፣ ተማሪዎቻቸው ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ ያነበቡዋቸውን መፅሄት፣ መፀሐፍና መጣጥፍ
ወደ መማሪያ ክፍላቸው ይዘው እያመጡ ካነበቡላቸው የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከት አዎንታዊ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ ሙለር
(1973) የተባሉት ተመራማሪ በበኩላቸው የማንበብ አመለካከትን ለመለካት በ41 ተማሪዎች ላይ ቅኝት አድርገው ነበር፡፡ የጥናቱ
ውጤት እንደሚያመለክተው የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት በከፍተኛ
ሁኔታ ለተፅዕኖ የሚያጋልጠው የመምህራን የማንበብ አመለካከት ነው፡፡ በማንኛውም ክስተት መምህራን የተማሪዎቻቸውን የማንበብ አመለካከት
ከተረዱና ከተቀበሉት ለውጥ ያመጣሉ፡፡ ይህንን በሚመለከት ተመሳሳይ ጥናት ያደረጉት ሞዩር (1977) የማንበብ አመለካከትን ከመምህራን
የማንበብ ልምድ ጋር አያይዘውታል፡፡ በተጨማሪም መምህራን አዘውትረው የሚያነቡ ከሆነ ተማሪዎቻቸውም የማንበብ አመለካከታቸው አወንታዊ
እንዲሆን አርአያ ይሆናሉ፡፡ ይህንን በምርምር ለማረጋገጥ በተደረገው ጥናት አዘውትረው ከሚያነቡና ከማያነቡ መምህራን በመጠይቅ የተሰበሰበው
መረጃ ውጤት እንዳመለከተው አንባቢ መምህራን ከማያነቡት በተሻለ ለተማሪዎች የማንበብ አመለካከት አርዓያ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ከዚህ በተለየ ኢስቴስ (1971) የተባሉት ተመራማሪ ተማሪዎች የማንበብ
አመለካከታቸው የሚለወጥበትን ምክንያት ለማወቅ ጥናት አድርገዋል፡፡ ይህንንም ዕውን ለማድረግ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት መለኪያ
መጠይቅ አዘጋጅተው ነበር፡፡ በጥናቱ ከሶስተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከሚማሩ ተማሪዎች መካከል ናሙና በመውሰድ የማንበብ አመለካከታቸውን
ለክተዋል፡፡ ከትንተናው የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው ማንበብን በተመለከተ የወጣት ተማሪዎች አመለካከት አወንታዊ ነው፡፡
ከዚህ ምርምር ጋር የሚቃረን ጥናት ያቀረቡት ተመራማሪ ራንስበሪ
(1973) ናቸው፡፡ ተመራማሪው በጥናታቸው 65 የጥናት ተሳታፊ ተማሪዎችን፣ መምህራንና ወላጆችን በመምረጥ ለማንበብ የሚያስደስታቸውንና
የማያስደስታቸውን ንባብ እንዲገልፁ አድርገዋል፡፡ ተማሪዎቹ አንድን
ንባብ እንዲያነቡና እንዳያነቡ የሚገፋፉት በንባብ መማሪያ መፃህፍት
አማካኝነት መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ወላጆች ንባብን እንዲጠሉት ያደረጋቸው ምክንያት አዘውትረው አለማንበባቸው ነው፡፡ መምህራን በበኩላቸው
የማንበብ አመለካከት አወንታዊና አሉታዊ እንዲሆን የሚያደርገው የተማሪዎች አዕምሯዊ ችሎታ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ በጥናቱ ማጠቃለያ
ላይ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ተፅዕኖ የሚያሳድርበት ዋነኛ ምክንያት የንባብ ችሎታ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ሒዚግነቶንና አሌክሳንደር (1984) ባካሔዱት ጥናት ደግሞ አወንታዊ የማንበብ
አመለካከትን ለማዳበር የመምህራንና የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ገምግመዋል፡፡ በጥናቱ 100 መምህራን በማስተማር ልምዳቸው
መሰረት ተመርጠው ንባብን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ሲያስተምሩ ምን፣ ምን ተግባራትን እንደሚያከናውኑ አጠቃላይ መጠይቅ ቀርቦላቸዋል፡፡
በመጠይቁ ላይ ትኩረት በመስጠት የሚጠቀሙባቸውን 9 የማስተማር ልምዶችን በቅደም ተከተል እንዲዘረዝሩ ተጠይቀዋል፡፡ በመጠይቁ የቀረቡላቸው
ዝርዝሮችም አንብቦ መረዳት፣ ቃላዊ ንባብ፣ የዝምታ ንባብ፣ ቃላዊ ትርጉም፣ ቃላትን መምረጥ፣ መዋቅራዊ ትንተና፣ የማንበብ አመለካከቶችና
የክህሎት ጥናት የሚሉ ነበሩ፡፡ ከመጠይቁ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው በርካታዎቹ መምህራን የማስተማሪያ ክፍለ ጊዚያቸውን ለማንበብ
አመለካከት ማጎልበቻነት አይመድቡም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ መምህራኑ ክህሎትን በማስጨበጥ ላይ ስለሚያተኩሩና የክህሎት እድገት የማንበብ
አመለካከትን አዎንታዊና አሉታዊነት ለመጨመርና ለመቀነስ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡
ማና እና ማይሽፍ (1987) ከላይ ያለውን ጥናት በመቃረን ባደረጉት ጥናት
በዩኒቨርስቲ የስነ-ፅሁፍ ተማሪዎች ለምን ለአሉታዊ የማንበብ አመለካከት እንደተጋለጡ መርምረዋል፡፡ ምክንያቱንም ለመገንዘብ ጥረት
አድርገዋል፡፡ ጥናቱን ተግባራዊ ለማድረግ በጥቅም ላይ የዋለው የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያ ተማሪዎቹ ግለ ታሪካቸውን እንዲሞሉ በማድረግ
ነበር፡፡ ከተማሪዎቹ ግለ ታሪክ በዳግም ግምገማ ከተገኘው ውጤት ለመረዳት እንደተቻለው በተማሪዎቹ ላይ አሉታዊ የማንበብ ተፅዕኖ
ያሳደረው የተማሪዎቹ ወላጆችና መምህራን አርዓያ በመሆን የማንበብ አመለካከታቸው እንዲጎለብት ድጋፍ ስላላደረጉላቸው ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሞሪሰን፣ ጃኮብስና ስዊንያርድ (1999) መምህራን በመማሪያ
ክፍል ውስጥ ለተማሪዎቻቸው የሚያነቡላቸው ግላዊ የመዝናኛ ንባብ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ለመለወጥ ያለውን ፋይዳ በሚመለከት
አጥንተዋል፡፡ በመጠይቅ ከተሰበሰበው የማስተማርና ግላዊ የንባብ ልምድ መረጃ ከተገኘው ውጤት ለመረዳት እንደተቻለው መምህራን በአብዛኛው
የሚያነቡት የሚያስተምሩትን ትምህርት መፃሕፍት ንባቦችን ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ተማሪዎቹ ማንበብን መሰረት በማድረግ እየተዝናኑ
ስለማይማሩ ለማንበብ ያላቸው አመለካከት ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ ወደ መሆን አዘንብሏል፡፡
አፕሊጌትና አፕሊጌት (2004) ያደረጉት ጥናት የመምህራንን የማንበብ ልምዶችና
አመለካከቶች የሚመርምር ነው፡፡ በልቅ መጠይቅ አማካኝነት በመምህራን ላይ በተደረገው ቅኝት 54% የሚሆኑት መምህራን የማንበብ ጉጉት
የሌላቸው መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ለዚህም ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የተገመተው መምህራኑ በቀድሞ የትምህርት ዘመናቸው
ወቅት የማንበብ አመለካከታቸው አሉታዊ ተፅዕኖ አድሮበት ስለነበር ነው፡፡ በጥናቱ ማጠቃለያ ላይ እንደሰፈረው የመምህራን ማንበብን ያለመውደድ ልምድና የአመለካከት አለመዳበር
የተማሪዎቻቸውን የማንበብ አመለካከት በዕጅጉ እንደሚጎዳ ተገልጧል፡፡
የብላክቢ (2006) ጥናት ከአፕሊጌትና አፕሊጌት (2004) የተለየ ነው፡፡
ተማሪዎች እንደሚኖሩበትና እንደተማሩት አግባብ የማንበብ ክሕሎታቸው ዕድገት ለተፅዕኖ ይጋለጣል፡፡ በማንበብ አመለካከቶች ላይ አወንታዊና
ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ ለማድረስ ምክንያት የሚሆኑት ጉዳዬች ተፈጥሮ (innate) ፣ ቤተሰብና
ትምህርት ቤት ናቸው፡፡ እነዚህ የተፅዕኖ ምክንያቶች ተማሪዎች ለማንበብ በሚነሳሱበት ወቅትና ራሳቸውን እንደ አንባቢ መቁጥር በሚጀምሩበት
ጊዜ ማንበብን እንዲወዱ ወይም እንዲጠሉ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ብላክቢ (2006) ጨምረው እንደገለፁት፣ ቤተሰብ በማንበብ ላይ አንዳንድ
ተፅዕኖዎች ያሳድራል፡፡ ማህበራዊ መደቦችና የቤተሰብ ባሕል የተማሪዎች ማንነት ላይ ጫና በመፍጠር ተፅዕኖ የሚያሳድረው አመለካከታቸውና
የንባብ ተግባራቶች ላይ ነው፡፡ ተማሪዎች በቤተሰባቸው አማካኝነት የማንበብና የመፃፍ ችሎታቸው ሲያድግ አመለካከታቸውም አብሮ ያድጋል፡፡
ሞሮውና ያንግ (1997) በተመሳሰይ እንዳጠኑት ወላጆች በመኖሪያ ቤት ልምዶቻቸው
በልጆቻቸው ላይ ተፅዕኖ እንዲሚያሳድሩ ያምናሉ፡፡ የቀን ተቀን የቤተሰብ ተግባራት በልጆች የማንበብ ዕድገት፣ በአመለካከቶቻቸውና
በማንበብ ተግባራት የተሳትፎ ፍላጎታቸው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ወላጆች ወይም ልጆችን ተንከባካቢዎች መልካም
አርዓያ በመሆን ተፅዕኖ ለማሳደር የሚችሉበት ምክንያት ልጆቻቸው በማንበብ ልምምድ ወቅት ምን፣ እንዴት፣ መቼና ለምን እንደሚያነቡ
ስለማያስረዷቸው ነው፡፡
ይሁን እንጁ ማዩንግሱንና ሒኪዩንግ (2002) ባደረጉት ጥናት የማንበብና
የአመለካከት ዕድገት የሚመጣው በትምህርት ቤት ብቻ የሚመስላቸው በርካታ ወላጆች እንዳሉ አረጋግጠዋል፡፡ በእርግጥ በቤተሰብ ብቻ
ሳይሆን፣ በትምህርት ቤት አማካኝነትም በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አዩናላና ሌሎች (2002)
በትምህርት ቤት ውስጥ የማንበብ አመለካከትን ለተፅዕኖ የሚያጋልጡ ናቸው በማለት የዘረዘሯቸው፡- ተማሪዎችን በመማሪያ ክፍል ውስጥ
ለመዝናናት ማስነበብ፣ በራሳቸው ምርጫ ፅሁፎችን እንዲያነቡ ማድረግና በክፍል ውስጥ ለጓደኞቻቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማስነበብ
ናቸው፡፡
ጋምብሪል (2004)፣ በጥናታቸው ግኝት እንደደረሱበት መምህራን ተማሪዎችን
አዝናኝ ንባቦች መርጠውላቸው ማስነበብ የማንበብ አመለካከታቸው አወንታዊ ቅርፅ እንዲይዝና የራስ ግላዊ ውጤታማነታቸው እንዲጨምር
ያደርጋል፡፡ ተማሪዎቹ በመደበኛነት የመዝናኛ ንባብ የሚያነቡ ከሆነ በስፋትና በጥልቀት ማንበብ እንዲለምዱ፣ የማንበብ ክህሎት ብቃታቸው
እንዲያድግ፣ የአንብቦ መረዳትና የቃላት ችሎታቸው እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ምናባቸውን ለማስፋት፣ የፈጠራና የክህሎት ዕድገታቸውን
ከፍ ለማድረግ ይረዳል፡፡ የጉዝሪ (1999) የጥናት ውጤት ከጋምብሪል (2004) ጋር ይቃረናል፡፡ ተማሪዎች በራሳቸው ምርጫ ብቻ የመዝናኛ ፅሁፎች ወይም ድርሳናትን መርጠው ማንበባቸው ከራሳቸው ፍላጎትና
አመለካከት ጋር የሚገጣጠም ርዕስ እንዲያነቡ ስለሚያደርጋቸው በራሳቸው ሙከራዎች ስሌት ዕውቀትና ልምዶቻቸውን በማስፋት ግላዊ ዓላማቸውን
ለማሳካት ያገለግላቸዋል፡፡
ከዚህ ጥናት በተለየ ድሪኸር (2003) እንደገለፁት ተማሪዎች ድምፃቸውን
በመማሪያ ክፍል ውስጥ ከፍ አድርገው እንዲያነቡ ማድረግ አወንታዊ የማንበብ አመለካከታቸው እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ ተማሪዎቹን ከንባብ
በኃላ በቁልፍ ሐሳቦች ላይ ማወያዬት ፍላጎታቸውን ያጠናክራል፡፡ አወንታዊ የማንበብ አመለካከታቸውን ያሳድጋል፡፡ ብራስል
(2003) እንደጠቀሱት ደግሞ የመዝናኛ ምንጭ ይሆናቸዋል፣ የቃላት ክምችታቸው መሰረት ይይዛል፣ ውጤታማ የንባብ ብልሐቶችን ይማራሉ፡፡
በመጨረሻም ስችማይት (2009) እንደሚገልፁት የማንበብ አመለካከትን በሚመለከት ተመሳሳይና ተቃራኒ ጥናቶች አሉ፡፡ የጥናቶቹ ግኝቶች የማንበብ አመለካከት
በወላጆችና በመኖሪያ ቤት አካባቢ፣ በመማሪያ ክፍል እንዲሁም በተማሪዎችና በመምህራን አመለካከትና ባሕሪ ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ አመለካከትና
የማንበብ አመለካከት ያላቸውን ግንኙነት የሚጠቁሙ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ከተደረጉት ጥናቶች ቅኝት ለመገንዘብ እንደሚቻለው ማንበብና የማንበብ
አመለካከት ጥብቅ ግንኙነት አላቸው፡፡ አመለካከት በማንበብ ላይ የሚያሳድረው የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ የማንበብ አመለካከት
ተለዋዋጭ ሲሆን፣ ምክንያቶቹም ወላጆች፣ ቤተሰብ፣ መምህራንና አካባቢ የሚያሳድሩት አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም
አመለካከትና የማንበብ አመለካከትን ግንኙነት ጠንቅቆ በመረዳት በትምህርት ቤት ውስጥ በተማሪዎች የማንበብ አመለካከት ላይ ለሚፈጠሩ
ችግሮች መፍትሄ መፈለግ ያሻል፡፡
2.2. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች
የማንበብ አመለካከት
ኩሊክና ኩሊክ (1982) በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በችሎታ አቅም የተደራጀ ቡድን ለአመለካከት ለውጥ
ያለውን አስተዋፅኦ በሚመለከት ጥናት አድርገዋል፡፡ ጥናቱ የተካሄደው 52 ተማሪዎችን በከፍተኛ፣ በመካከለኛና በዝቅተኛ ችሎታ ቡድኖች
በማደራጀት ነበር፡፡ የጥናቱ ውጤት እንዳመለከተው ተማሪዎችን በቡድን ማደራጀት ለአመለካከት ለውጥ ጠቀሜታ አለው፡፡ በጥናቱ በቡድን
የተደራጁት ተሳታፊዎች ለሚማሩት የትምህርት ዓይነት በርካታ አዎንታዊ አመለካከቶችን ሲያሳድጉ፣ በቡድን ያልተደራጁት ግን አመለካከታቸው
አሉታዊ ሆኗል፡፡ በቡድን ከተደራጁት መካከልም ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች አመለካከታቸው ከፍተኛ ሲሆን፣ መካከለኛና ዝቅተኛ
ችሎታ ያላቸው የአመለካከታቸው ደረጃ መካከለኛዎቹ መካከለኛ፤ ዝቅተኛዎቹ ደግሞ ወደ ዜሮ የሚጠጋ አመለካከት አስመዝግበዋል፡፡
በተመሳሳይ ሊናና ካሪም (2007) የማንበብ አመለካከት፣ ቤተሰባዊ ቅድመ ሁኔታና በራስ ጥረት መማር በማንበብ
ችሎታ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በሚመለከት ጥናት አድርገዋል፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በ4018 የጥናቱ ተሳታፊ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ መጠይቅና አንብቦ የመረዳት ፈተና በማቅረብ ነው፡፡ ከጥናቱ የተገኘው ውጤት እንደጠቆመው
የቃላዊ/የአጠቃላይ ትምህርት በራስ ጥረት መረዳት (Verbal/General academic
self-concept) የማንበብ ችሎታ ከፍተኛ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም የፆታ ልዩነት በማንበብ አመለካከት
ላይ ተፅዕኖ እንዳለውና እንደሌለው ተፈትሿል፡፡ በጥናቱ ውጤት እንገተገለፀው ሴቶቹ ተማሪዎች ከወንድ ተማሪዎች በተሻለ አዎንታዊ
የማንበብ አመለካከት አላቸው፡፡ ወንዶቹ ተማሪዎች የተሻሉ ሆነው የተገኙት ትምህርትን በራስ ጥረት በመረዳት፣ በራስ ውጤታማነት፣
በማስታዎስ፣ በማብራራትና በመነሳሳት ናቸው፡፡
በተጨማሪም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አስቸጋሪ አጫጭር ታሪኮችን(ንባቦችን) የማንበብ አመለካከት፣
አንብቦ የመረዳትና የማስታዎስ ችሎታ ለመመርመር ግራቪስ፣ ላበርግና ኩኪ (1983) ጥናት አድርገው ነበር፡፡ ለጥናቱ ተሳታፊ
72 ተማሪዎች በደረጃቸው አንብቦ ለመረደት ቀላልና አስቸጋሪ አጫጭር የንባብ ታሪኮችን በማቅረብ ጥናቱ ተካሂዷል፡፡ የጥናቱ ውጤት
እንዳመለከተው አንብቦ ለመረደት ቀላል ለሆኑት ታሪኮች የተማሪዎቹ አመለከካት አዎንታዊ ሲሆን፣ የመረዳትና የማስታዎስ ችሎታቸውም
ከ13% እስከ 38% ጨምሯል፡፡
በሌላም በኩል ክሪስቲናና ጆናታን (2011) የታላቋ እንግሊዝ ወጣት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸው ለምን
እንደቀነሰ ለማወቅ ጥናት አድርገዋል፡፡ በጥናቱ በ17,000 ተማሪዎች ላይ ለማንበብ አመለካከታቸው መቀነስ የትምህርት ቤት የማንበብ
ብቃት፣ የፆታ ወይም የጎሳ ልዩነት ምክንያት እንደሆን ቅኝት በማድረግ ባህሪያቸውን ለመመርመር ጥረት ተደርጓል፡፡ በጥናቱ የተገኘው
ውጤት እንዳመለከተው የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከት ከ2005 እስከ 2009 ባሉት አምስት ዓመታት ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ ምክንያቱ ደገሞ ወጣቶቹ በማንበብ ስለማይደሰቱ ማንበብን ማቆማቸው ነው፡፡
በመጨረሻም በትምህርት ውጤታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸውን አመለካከት፣ የማንበብ ችሎታ ውጤታቸውንና
በራስ ጥረት ማንበብን በማጐልበት የትምህርት ብቃታቸውን ማሳደግ ይቻልና አይቻል እንደሆን ለመመርመር ቲዎዶር (2010) ጥናት አድርገው
ነበር፡፡ ጥናቱን ለማካሄድ በትምህርታቸው ውጤታማ የሆኑ ተማሪዎችን በሁለት ቡድን በማደራጀት አንደኛው ቡድን በንባብ ማሻሻያ መርሐ
ግብር (Remedial Reading Program) እንዲሳተፍ ሲደረግ ሌላው ቡድን ግን አልተሳተፈም፡፡ በተጨማሪም ሁለቱም ቡድኖች የማንበብ አመለካከት መጠይቅ
እንዲሞሉ ተደርጓል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደጠቆመው በንባብ መፍትሄ መርሐ ግብር የተሳተፉት ተማሪዎች ካልተሳተፉት
ጋር ሲነፃፀሩ የማንበብ አመለካከታቸው ተሻሽሏል፣ በራስ ጥረት የማንበብ ውጤታማነታቸው ደረጃው ከፍተኛ ሆኗል፡፡
ለማጠቃለል ያህል ከጥናቶቹ ውጤት ለመገንዘብ እንደሚቻለው የሁለተኛ ደረጃ ትህርት ቤት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከት
በተለያዩ ምክንያቶች ለተፅኖ ይጋለጣል፡፡ ተማሪዎችን በቡድን ማደራጀት ለአመለካከት ለውጥ
ጠቀሜታ አለው፡፡ የማንበብ አመለካከት፣ ቤተሰባዊ ቅድመ ሁኔታና በራስ ጥረት መማር በማንበብ ችሎታ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ አንብቦ
ለመረደት ቀላል የሆኑ ታሪኮች(ንባቦች) የተማሪዎቹን የማንበብ አመለከካት አዎንታዊ ያደርጋሉ፤ የመረዳትና የማስታዎስ ችሎታን በእጅጉ ይጨምራሉ፡፡ በማንበብ የማይደሰቱ ተማሪዎች ለማንበብ
ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ ቢሆንም አመለካከታቸውን በተለያዩ ዘዴዎች በማሳደግ ማሻሻል ይቻላል፡፡
2.3. የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት
ችሎታ ተዛምዶ
ሳላበስ (2008) በ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ መኖርና
አለመኖሩን በሚመለከት ባደረጉት ጥናት የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ ደረጃው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በተጨማሪም ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከትና የትምህርት ውጤታቸው ተዛምዶ እንዳለው ተጠንቶ ተዛምዶው ዝቅተኛ ደረጃ እንዳለው
ተረጋግጧል፡፡ በጥናቱ በፆታ ምክንያት የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ልዩነት እንዳለው ታውቋል፡፡ ለዚህም በጥናቱ እንደ ምክንያት የተጠቀሱት ተማሪዎቹ የቀረበላቸውን ንባብ በግልፅና በትክክል
አለመረዳታቸው፣ የንባቡን መዋቅር፣ ይዘትና ቴክስት ለመተቸት አለመቻላቸው ናቸው፡፡
ፒትስቸር (2010) በተመሳሳይ ባደረጉት ጥናት በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የማንበብ ችሎታ ውጤት መካከል
ያለውን ተዛምዶ ቃኝተዋል፡፡ በ32 ተማሪዎች ላይ በተደረገው ጥናት የተገኘው ውጤት እንደጠቆመው የተዛምዶው መጠን ዝቅተኛ ነው፡፡
በጥናቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የማንበብ ውጤታማነት መካከለኛ ተዛምዶ ሲኖረው፣ በመካከለኛ
ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩት ዝቅተኛ ተዛምዶ አስመዝግበዋል፡፡
ከዚህ ጥናት ጋር በተያያዘ ናንሲ (1989) ከ 1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎችን ለማንበብ ያላቸውን
አመለካከትና የማንብ ችሎታ ውጤት ተዛምዶ አጥንተዋል፡፡ በጥናቱ የተሳተፉ 876 ተማሪዎች ከሞሉት የማንበብ አመለካከት መለኪያ መጠይቅና
የአንብቦ መረዳት ችሎታ ፈተና የተገኘው ውጤት እንደሚያስረዳው
(1) በተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከትና የንባብ ውጤታማነት መካከል ተዛምዶው
ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፤ (2) የማንብቦ ችሎታ ውጤታቸው ደረጃው መካከለኛ ሆኗል፤ (3) እስከ ስምንተኛ ክፍል ባሉት
የትምህርት ደረጃዎች የማንበብ አመለካከታቸው ቀንሷል፤ (4) ከወንዶቹ ተማሪዎች በተሻለ የሴት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የንባብ
ውጤታማነት ተዛምዶ ከፍተኛ ሆኗል፤ (5) የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች የማንበብ አመለካከት አዎንታዊ እንደነበር ተጠቁሟል፤
(6) በሴትና በወንድ ታሪዎች መካከል የማንበብ ብቃትን በሚመለከት ጉልህ ልዩነት አልታየም፤ (7) ዝቅተኛ የማንበብ ችሎታ ውጤት
(achievement) ያላቸው ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸውም ቀንሷል::
በተጨማሪም ባስ (2012) የተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የመፃፍ ዝንባሌ ተዛምዶ እንዳላቸውና እንደሌላቸው
አጥንተዋል፡፡ ተመራማሪው በቱርክ ሐገር ኒጋዳ ትምህርት ቤት በ450 ተማሪዎች ላይ ባደረጉት ጥናት በመጠይቅ የተሰበሰበው መረጃ
ውጤት እንዳመለከተው በማንበብ አመለካከትና በመፃፍ ዝንባሌ መካከል አዎንታዊ ተዛምዶ አለ ፡፡ እንዲሁም የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት
የመፃፍ ዝንባሌያቸውን የመተንበይ ድርሻው የጎላ ነው፡፡
በተመሳሳይ ተራቪስ (2010) የተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና ስነፅሁፍ የማንበብ ልምዳቸው ተዛምዶ መኖርና
አለመኖሩን መርምረዋል፡፡ ለ18 ወራት በተደረገው ጥናት የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከት፣ የንባብ ልምድና በተጓዳኝም ሥነ ፅሁፍን
የማንበብ ተነሳሽነታቸው በመጠይቅ መጠናዊና ዓይነታዊ መረጃ ተሰብስቦ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸው
በጐለበተ መጠን ልምዳቸው በመዳበሩ የማንበብ ተነሳሽነታቸው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊለወጥ ችሏል፡፡ በጥናቱ ተማሪዎች ለረጅም ጊዜ እያነበቡ
የመቆየት ልምዳቸው በአመለካከታቸው ላይ ለውጥ አልታየበትም፡፡
ከዚህም ሌላ የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ በፆታ ልዩነት ተዛምዶ እንዳለውና እንደሌለው ለመመርመር
የተደረጉ ጥናቶች አሉ፡፡ ዊዊ (2009) በቻይና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የፆታ ልዩነት ከአንብቦ በመረዳት ችሎታ ጋር ያለውን
ተዛምዶ መርምረዋል፡፡ በመጠይቅና በክለሳ ድርሳን ሪፖርት የተሰበሰቡት መረጃዎች እንዳመለከቱት ሴት ተማሪዎች ከወንድ ተማሪዎች በተሻለ
ሁኔታ ብልሐቶችን በመጠቀም፣ የንባብ ጭንቀትን በመቋቋም እንዲሁም አንብቦ በመረዳት ችሎታ የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሮዊል (1972) የማንበብ አመለካከትን የሚለውጡ ምክንያቶችን ለመመርመር ጥናት አድርገዋል፡፡ በጥናታቸውም
የማንበብ አመለካከት አንብቦ ከመረዳት ችሎታ፣ ቃላትን ከመለየት፣ ከፆታ፣ ከዕድሜና ከማሕበራዊ ደረጃ ጋር ያለውን ተዛምዶ አጥንተዋል፡፡
ተመራማሪው የጥናቱን ተሳታፊዎች በሙከራ ቡድንና በቁጥጥር ቡድን በመከፋፈል ከሰበሰቡት መረጃ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው የማንበብ
አመለካከት በፆታ፣ በዕድሜና በማህበራዊ ደረጃ ተዛምዶው በስታስቲክስ ጉልህ ልዩነት አልተገኘበትም፡፡ ልዩነት የታየው ቃላትን ተገንዝቦ
በመለየት ላይ ነው፡፡
በጥናቶቹ እንደተጠቆመው የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ እንዳይጎለብት የሚያደርጉት ምክንያቶች
አዎንታዊ የማንበብ አመለካከት እንዲዳብር ትኩረት ባለመሰጠቱ፣ መምህራን የበርካታ ተማሪዎቻቸውን የማንበብ አመለካከት ዝንባሌ ግምት
ውስጥ ሳያስገቡ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ማከናዎናቸው እንዲሁም ወላጆች ማንበብን የትርፍ ጊዜ ተግባር አድርገው መቁጠራቸው ናቸው
(ሮዊል 1972፣ ዊዊ 2009)፡፡
ከዚህ በተለየ አቡ-ራቢያ (1996) አመለካከቶችና ባሕላዊ ዳራ በሁለተኛ ቋንቋ አንብቦ ከመረዳት ችሎታ ጋር
ያላቸውን ተዛምዶ ከሶስት ማሕበራዊ አውዶች ጋር በማነፃፀር ጥናት አድርገዋል፡፡ በጥናቱ ከተሳተፉት እስራኤላዊ አረብ፣ እስራኤላዊ
አይሁድና ካናዳዊ አረብ ተማሪዎች የተገኘው ውጤት እንደሚያስረዳው በራሳቸው ባሕል የቀረበላቸውን ፅሁፍ የተፈተኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች
የማንበብ አመለካከትና ፍላጎታቸው እንዲሁም አንብቦ የመረዳት ችሎታቸው የተሻለ ሆኖ ተገኝተል፡፡ የካናዳዊ አረቦቹ ቡድን ውጤት ከእስራኤል
አረቦቹና ከአይሁድ አረቦቹ ጋር ሲነፃፀር የቴክስቱ ይዘት ሳይሆን የቴክስቱ ቋንቋ አንብቦ ለመረዳት ተፅዕኖ አሳድሮባቸዋል፡፡
በተጨማሪም ግሪአኒ (1987) የማንበብ አመለካከት፣ የመኖሪያ አካባቢና የማንበብ ፍላጎት ከማንበቢያ ትርፍ
ጊዜ (leisure-time reading) ጋር ያላቸውን ተዛምዶ በሚመለከት
በጥናታቸው ቃኝተዋል፡፡ ከጥናቱ የተገኘው ውጤት እንደሚያስረዳው የመኖሪያ አካባቢና የማንበቢያ ትርፍ ጊዜ ተዛምዶ አላቸው፡፡ ከሌሎቹ
ተለዋዋጮች በላቀ ሁኔታ የማንበብ አመለካከት ከማንበቢያ ትርፍ ጊዜ ጋር በጥብቅ ይዛመዳል፡፡ የማንበብ ፍላጎትና የማንበቢያ ትርፍ
ጊዜ ያላቸውን ተዛምዶ በሚመለከት ጥናቱ እንዳመለከተው ለመዝናኛ ንባብ ካልሆነ በስተቀር ትርፍ የማንበቢያ ጊዜ ለትምህርታዊ ንባብ
ብዙም ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡
ቡክሆረስት-ሄንግና ፔሪራ (2008) በአንድ የሲንጋፖር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዓመቱ የትምህርት ማብቂያ
ተማሪዎች አሉታዊ የማንበብ አመለካከት ሊያድርባቸው የቻለበትን ምክንያት አጥንተዋል፡፡ ለዚህም ትርፍ ጊዜን በንባብ ተግባር ላይ
አለማዋል በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ታውቋል፡፡ በጥናቱ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው በማንበብ አመለካከት በሴቶችና
በወንድ ተማሪዎች መካከል የጎላ ልዩነት አልታየም፤ ሁሉም የጥናቱ ተሳታፊዎች የማንበብ ውስጣዊ ፍላጎታቸው ግን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡
በአጠቃላይ ከጥናቶቹ ውጤት ለመረዳት እንደሚቻለው የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ተዛምዶ አላቸው
የሚሉ ተመራማሪዎች አሉ ለምሳሌ ሳላበስ (2008)፣ አቡ-ራቢያ (1996)ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሌላም በኩል ተዛምዶው ቢኖርም
በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙ ተመራማሪዎች አሉ (ግሪአኒ 1987፣ ቡክሆረስት-ሄንግና ፔሪራ 2008)ን
መጥቀስ ይቻላል፡፡
2.3. የማንበብ አመለካከት አንብቦ ለመረዳት ያለው ሚና
ወላጆች የማንበብ አመለካከትን ለማሳደግና ለማጠናከር በመኖሪያ ቤት ውስጥ ሁለት ሚናዎችን
ይጫወታሉ፡፡ የመጀመሪያው ሚና ማንበብን ባህላቸው አድርገው የሚነበቡ ነገሮችን በመኖሪያ ቤት ውስጥ ማስቀመጣቸው ሲሆን፣
ሁለተኛው ሚና በማንበብ ልምዳቸው አማካኝነት ለልጆቻቸው አዝናኝና
አስተማሪ ድርሳናትን እያነበቡላቸው ተፅዕኖ ማሳደራቸው ናቸው፡፡ ወላጆች የማንበብ ልምዳቸውን በማዳበር ለልጆቻቸውም አርአያ ከሆኑ
ልጆቻቸው በመኖሪያ ቤት ውስጥ እንዲያነቡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ (ስፓይገል 1994)፡፡ ወላጆችና የመኖሪያ ቤት አካባቢ በአመለካከት
ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በጎ ከሆነ በትምህርት ቤት አወንታዊ አመለካከትን ለማጠናከር ለሚደረገው ጥረት በቅርበት አብሮ ለመስራት
ያግዛቸዋል (አሌክሳንደርና ፊለር 1976)፡፡
በተጨማሪም ስችማይት (2009) የተማሪዎችን አወንታዊ የማንበብ አመለካከቶች
ማሳደጊያና ማጠናከሪያ ናቸው በማለት የሚዘርዝሯቸው 5 መንገዶች አሉ፡፡ እነሱም በመኖሪያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ወላጆች፣ በትምህርት
ቤት አካባቢ ያሉ የመማሪያ ክፍሎች፣ በተለያዩ መሳሪያዎች የሚሰበሰቡ የአመለካከት ግምገማዎች፣ የማስተማር ልምዶች፣ የተማሪዎችና
የመምህራን አመለካከትና ባህሪያት ናቸው፡፡
ይህንን ሀሳብ በመቃረን ክራመር (1994)፣ ዊየርና ዊየር (1994)ና
ብሮፊ (2004) የማንበብ አመለካከትን ለማሳደግና ለማጠናከር የሚቻለው በመኖሪያ ቤት ሳይሆን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ብቻ ነው በማለት
ይከራከራሉ፡፡ ለዚህ አባባላቸው በምክንያትነት የሚጠቅሱት የመምህራንና የተማሪዎች የመማሪያ ክፍል ውስጥ ተራክቦ፣ ንቁ የሆነ የመማር
መነሳሳት ካለ፣ የመማሪያ መፃሕፍት በተማሪዎች ፍላጎት መሰረት ከተመረጡ፣
መምህራን በተማሪዎች የመማሪያ ክፍል ውስጥ ቤተ- መፃህፍት ካዘጋጁ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ብቻ የማንበብ አመለካከትን ማሳደግና ማጠናከር
ይቻላል፡፡
በዚህ ሀሳብ የማይስማሙት ማክኪና፣ ኪአርና ኢልስዋርዝ (1995) የመምህራንና
የተማሪዎችን አመለካከቶችና ባህሪያት ጠንቅቆ በማወቅ የማንበብ አመለካከትን ማሳደግና ማጠናከር ይቻላል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች
ለማንበብ ያላቸውን አዎንታዊና አሉታዊ ምክንያት በመገንዘብ ለችግሮቹ መፍትሔ ፈልጎ ያላቸውን ማጠናከር፣ የሌላቸውን መፍጠር ይቻላል፡፡
ልጆች በመኖሪያ ቤትም ሆነ በትምህርት ቤት በትርፍ ጊዜያቸው እንዲያነቡ ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸው፣ ወላጆችና መምህራን ደካማና ጎበዝ
እያሉ በአንባቢያን መካከል ልዩነት ካልፈጠሩ፣ መምህራን በትምህርት ቤት ውስጥ ጎበዝ ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸው አዎንታዊ ሲሆን፣ የሰነፍ ተማሪዎች
ግን አሉታዊ ነው በማለት ተማሪዎችን ካልከፋፈሉ፤ በፃታ ፣በዕድሜና በጎሳ አማካኝነት የማንበብ ተፅዕኖን አጥንቶ መፍትሔ ከተፈለገ የማንበብ አመለካከትን የትም ቢሆን ማሳደግና
ማጠናከር ይቻላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ራሲኒስኪና ፓዳክ (2000) እንዳመለከቱት የተማሪዎች ንባብ
ስኬታማ እንዲሆን መምህራን መፃሕፍትን ማንበብ በመውደድ አርዓያ ሊሆኗቸው ይገባል፡፡ መምህራኑ ለተማሪዎቻቸው የማንበብ አርአያ ከሆኑ፣
በመማሪያ ክፍል ውስጥ የማንበብ ፍላጎትን ለማነሳሳት ተቀባይነት ያገኛሉ፡፡ አርአያ በሚሆኑበት ወቅት ከመምህራኑ የሚጠበቀው ክንውን
ተማሪዎቻቸው በዝምታ ንባብን ሲያነቡ እንዲመለከቷቸው ማድረግ ሳይሆን፣ ካነበቡት ምንጭ እየጠቀሱ ማንበብ ሕይወታቸውን እንዴት እንደለወጠው
ለተማሪዎቻቸው ቢነግሯቸው ተማሪዎችም ከማንበብ የሚገኘውን ጥቅም በመረዳት አንባቢ የመሆን አመለካከታቸው ሊያድግና ሊጠናከር ይችላል፡፡
ጋምብሪል (1996) እንዲሚገልፁት፣ ተማሪዎቻቸው ፈላስፋ፣ ተማራማሪ፣ ደራሲና ሐያሲ እንደሚሆኑላቸው የሚመኙ መምህራን እነሱም ተፈላሳፊ፣
ተመራማሪ፣ ተባባሪ፣ አንባቢ፣ ፀሐፊና ገምጋሚ መሆን አለባቸው፡፡
በተመሳሳይ ራስኒስኪና ፓዳክ (2000) እንዳመለከቱት ተማሪዎች ለማንበብ
ያላቸው አመለካከት አዎንታዊ እንዲሆን የሚፈልጉ መምህራን እነዚህን አራት ጠቃሚ ዕምነቶች አዋህደው መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነሱም(1)
ሁሉም ተማሪዎቻቸው ለመማር እንደሚፈልጉ ተስፋ ማድረግ፤(2) ተማሪዎች ወደ መማሪያ ክፍል ይዘዋቸው የሚመጡትን ከማንበብ ጋር የተያያዙ
ነገሮች ትኩረት መስጠት፤(3) ተማሪዎች በንባብ ትምህርት ተግባራት ከማይተገብሩት ይልቅ የሚተገብሩትን ተግባር በትኩረት መቃኘት፤(4)
በተማሪዎች ፍላጎትና ጠቀሜታ ላይ ተመስርቶ የተቃኘ ማስተማር፣ መማርን ቀላል
እንደሚያደርገው ማመን ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በምርምሮቹ እንደተገለፀው የማንበብ አመለካከት ለተማሪዎች የማንበብ
አመለካከት ሚናው የጎላ ነው፡፡ መምህራንና ወላጆች አዘውትረው ለማንበብ ያላቸው አመለካከት አሉታዊ ከሆነ ተማሪዎችም ለማንበብ ያላቸው
አመለካከት እየቀነሰ ይሄዳል፡፡
No comments:
Post a Comment