Thursday, September 13, 2012

የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነገር …


የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነገር …
ቋንቋ የዕውቀት መቅሰሚያና የግኑኝነት ማጠናከሪያ መሣሪያ ለመሆኑ ዋቢ መጥቀስ አያሻም፡፡ ከዚህም ባለፈ በግለሰብ፣ በቡድንና በማህበረሰብ ደረጃ የባህልና የማንነት መገለጫ እንደሆነ ነው ዩኔስኮ በ2000 እ.ኤ.አ ያወጣው መረጃ የሰነዳው፡፡
ከላይ የተገለፀውን የቋንቋ እምቅነት፣ የአንድ ሀገር ባህላዊና ሁለንተናዊ ማንነት የማንፀባረቂያ ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ የመገኘት ገጽታ ወደ ራስ ቋንቋ በመመለስ ለእድገትና ለተለያዩ ፈጠራዎች ማዋል እንዳለብን ያለመላክተናል፡፡ ይህን በማድረጋቸው የትምህርት መሠረታቸውን፣ ባህላቸውን፣ ምጣኔ ሀብታቸውን፣ ማህበራዊ መስተጋብራቸውንና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምጥቀታቸውን በማይናጋ መሠረት ላይ አንፀው በተምሳሌትነት የምናነሳቸው ቻይና፣ ጃፓንና ጀርመን ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሀገራቱ ሁሉ ነገራቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲቀኝ ማድረግ በመቻላቸው በሁሉም መስክ የእድገት ቁንጮ ላይ መቀመጥ ችለዋል፡፡ ሀገራቱ ፡- ቀድሞ የተማሩትን፣ እንደ ተወላጅ የቋንቋ ተናጋሪነት በሌሎች በሚታወቁበት፣ በተፈለገው መጠንና ደረጃ የሚያውቁትና ብዙ ጊዜ በሚጠቀሙበት የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ዜጎቻቸውን አንፀዋል፡፡
ቀድሞውንም የአፍ መፍቻ ቋንቋ የማንነታቸው ውስጣዊና ውጫዊ መገለጫ መሆኑን ተቀብለው አጎልብተው የማንነታቸውና የስብዕናቸው መገለጫ እንዲሆንም ተቀብለውታል፡፡ ከዚህ ባለፈ አንድ ሰው ከተወሰነ ብሔረሰብ ወይም ከአንድ የቋንቋ ተናጋሪ ቡድን ጋር ተወግኖ የሚገለጽበትቋንቋ እንዳለውም በውስጣዊ መገለጫነት ይመድቡታል፡፡ የአንድ ብሔረሰብ ወይም የቋንቋ ተናጋሪ አባል ተደርጎ እንዲወሰድ ወይም ከዚያ ብሔረሰብ ጋር በተዛመደ መልኩ እንዲገለጽ የሚያደርገው ቋንቋ የአፍ መፍቻ ቋንቋ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተውት መደላድልን ፈጥረውለታል፡፡
መሠረታዊ መደላድሎችን በማጎልበት ይበልጥ ቋንቋቸው ከመናኘት ባለፈ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ምጥቀት፣ የጥናትና ምርምር መሸጋገሪያ ድልድይ መሆን እንዲችል ለትምህርት መስጫነት አውለውታል፡፡ በሌላ አገላለፅ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ለትምህርት መስጫነት ወይም ለማስተማሪያ ቋንቋነት አውለውት መምህራኑ  የሚያስተምሩበት ፣ ተማሪዎች ማዕቀፍ ተበጅቶለት ተግብረውታል፡፡ ውጤቱንም በምናየውና በምንሰማው መልኩ ምጥቀታቸውን አመላክቶናል፡፡
በርግጥም እ.አ.አ. በ1990 የወጣው  የትምህርት ፖሊሲ የአፍ መፍቻ ቋንቋን ለትምህርት ማስተማሪያነት ማዋል ጠቀሜታው ላቅ ያለ መሆኑን አመላክቶ የሥርዓተ ትምህርት አካል በማድረግ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ሆኖም ግን የአተገባበሩ ወጥ አለመሆን በስነ ትምህርት አመለካከት (pedagogical view) ‹‹የአፍ መፍቻ ቋንቋ ህፃኑ ከሌላ ቋንቋ እጅግ በተሻለ ሁኔታ  በፍጥነት የሚማርበትና እውቀት ሊገበይበት የሚችልበት ቋንቋ ነው›› የሚለው አካሄድ የተፈለገውን ያክል ግን ማስረፅ አለመቻሉን በትምህርት ተቋማቶቻችን የሚታዩት ጉራማይሌ ነፀብራቆች አፍ ሞልተን እንድንናገር አድርጎናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋን አዎንታዊ ገፅታን አንድ ህፃን አፉን በፈታበት ቋንቋ ትምህርት እንዲያገኝ ማድረጉ አፉን ባልፈታበትና አዲስ በሆነበት ቋንቋ ሲማር ሊያጋጥሙት ከሚችሉ ስነ- ትምህርታዊ (pedagogical) እና ሥነ-ልቦናዊ (psychological)  ችግሮች ማላቀቅ መሆኑን ያለመረዳት ተግዳሮት አተገባበሩን አንቀርፍፎታል (አዘግይቶታል) ፡፡ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር በUNESCO  ስምምነት መሠረት የህፃናት መብት መሆኑን ‹‹የእያንዳንዱ ህብረተሰብና ት/ቤትን በር ያንኳኳና ግንዛቤ የተጨበጠበት ነው›› ለማለት ግን የአተገባበሩ ክፍተት ትኩረት ሠጥተን መሥራት እንዳለብን የማስጠንቀቂያ ደወል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የህፃናቱን የአፍ መፍቻ ቋንቋ ፣ ባህል፣ አካባቢና አኗኗርን መነሻ ያደረገ ትምህርት አሠጣጥ የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ ተበጅቶለት ሊሠርፅ ይገባል፡፡ ይህን በመከተል በመጀመሪያ የትምህርት ዓመት የህፃናቱንየአፍ መፍቻ ቋንቋ በመጠቀም ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች 2ኛ ና 3ኛ ቋንቋዎች መሸጋገር የሚያስችል የመማሪያ ማስተማሪያ ቋንቋዎች አጠቃቀም ዘዴን ማስኬድ ይቻላል፡፡
በተቻለ መጠን ግን ህፃናት በትምህርት ቤት በሚቆዩበት የመጀመሪያዎቹ 4 እና 5 ዓመታት በራሳቸው ቋንቋ እንዲማሩና ሌሎች ቋንቋዎች በተጠቀሱት ጊዜያት ውስጥ ለመማሪያ ማስተማሪያነት አለመጠቀምና ሌሎችን ቋንቋዎች በንግግር በመጀመር ቀስ በቀስ ወደ ፅሑፍና ንባብ እንዲመጡ ማድረግ የተሻለ አካሄድ መሆኑን ልናሰምርበት ይገባል፡፡
ዘዴው በትምህርት ላይ የማይናጋ መሠረት ለመጣልና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ጠንካራ የትምህርት መሠረት (strong Foundation) እና ጠንካራ መሸጋገሪያ (Good bridges) በማድረግ ያፀናዋል፡፡
ጠንካራ የትምህርት መሠረት ለመሆኑ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትታቸውን የተማሩ ሕፃናት ለቀጣይ ትምህርታቸው መሠረት የመገንባት መገለጫ ሲሆን የመጀመሪያ ቋንቋ ማስተማር ጽንሰ ሀሳቦችን እንዲረዱ ይረዳል፡፡ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር ወደ ሌሎች የመማሪያ ማስተማሪያ ቋንቋዎች ለመሸጋገር፣ ማንበብና መጻፍ የተማሩ ህፃናት የሁለተኛና የሦስተኛውን ቋንቋ ማንበብና መጻፍ ለመማር የሚያስችላቸው ጠንካራ መሸጋገሪያ (ድልድይ) ነው፡፡
ከዚህ ሌላ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርና የአእምሮአዊ (ዕውቀታዊ) (cognitive Advantage) ጥቅም፣ ሥነ ትምህርታዊ (pedagogical Advantage)ና ሥነ ልቦናዊ ጥቅም (psychological Advantage) ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡
የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለመማሪያ ማስተማሪያነት መጠቀምን አንዳንድ ሰዎች የተሳሳቱ አመለካከቶችን ከፖለቲካዊ፣ በሥነ ትምህርታዊ፣ ከምጣኔ-ሀብታዊና ሥነ-ልቦናዊ አስተያየቶች አንፃር ያስቀምጣሉ፡፡
ከፖለቲካ አተያይ አንፃር ‹‹የአፍ መፍቻ ቋንቋን ለመማሪያ ማስተማሪያነት በመጠቀም አንድነታችንን ያናጋል›› የሚል የተሳሳተ አመለካከትን ያራምዳሉ፡፡ ከሥነ- ትምህርት እንድምታ አንፃር ደግሞ ያልዳበሩና ያላደጉ ቋንቋዎችን በትምህርት ቋንቋነት መጠቀም የተማሪዎችን ዕውቀት ያሳንሳል፣ ደካማ ውጤት ለማምጣት ምክንያት ይሆናል የሚል ስህተትን ይዘራሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ቋንቋዎች ለትምህርት መጠቀም የተማሪዎችን እንግሊዝኛ ችሎታ እንደሚያበላሽም ለማስረዳት ይሞክራል፡፡
ከምጣኔ ሀብት ጋር በተያያዘ ደግሞ እስካሁን ያላደጉም ሆነ ያልዳበሩ ቋንቋዎችን ወደ ትምህርት ለማምጣት ብዙ ወጪና ጉልበት ይጠይቃል፤ ቋንቋውን ከክልል ውጭ ስለ ማንጠቀምበት ሰፊ ጥቅም ለሌለው ነገር ጉልበትና ወጪን በከንቱ ማበከን እንደሆነ ያስቀምጣሉ፡፡

የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት የመማር ማስተማር ሂደት ምን መምሰል አለበት?
የአፍ መፍቻ ቋንቋን ትምህርት የመማር ማስተማር ሂደት ውጤታማ እንዲሆን በተለይም መምህራን የተለያዩ የማስተማር ስነ-ዘዴና ሥልቶችን ሊከተሉ ይገባል፡፡ መምህራኑ በተግባቦታዊ (Interactive communication) እና አሳታፊ (participatory)  የትምህርት አሰጣጥ ማሰልጠንና በአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቃታቸውን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ህፃናት በርካታ የንግግርና የፅሑፍ ልምምዶችን እንዲያደርጉና በራሳቸው ቋንቋ መተማመንን እንዲያዳብሩ የማድረግ ፣ የመጀመሪያቸውን አንድ ዓመት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቻ ንግግርና የፅሁፍ ክህሎቶችን እንዲማሩ ማድረግና በዚህ ደረጃ እያሉ የሌላውን የቋንቋ ትምህርት ማዘግየት ወይም የንግግር ክህሎትን (oral language) ብቻ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡
ሁለተኛውን የቋንቋ ትምህርት በዕለታዊ ቋንቋ አጠቃቀም ደረጃ (every day language/ Basic interpersonal communication) በንግግር ቋንቋነት የማስተማርና ቀስ በቀስ የህፃናቱን የመማሪያ ማስተማሪያ 2ኛ ቋንቋ ቃላቶችን (Academic Vocabulary of 2nd Language) በንግግር ክህሎት አማካይነት የማሳደግ ሂደትን መከተል ግድ ይላል፡፡
የአፍ መፍቻ ቋንቋውን ከዋናው የመማሪያ ማስተማሪያ ቋንቋ (official medium of instruction) ጋር ጎን ለጎን በማካሄድ መጠቀም፡፡ ከዚህ ባለፈ ዋነኛውን የመማሪያ ማስተማሪያ ቋንቋ ሙሉ በሙሉ መጠቀም በሚጀምሩበት ጊዜ የአፍ መፍቻ ቋንቋውን አንዳንዴ ግልፅ ያልሆኑ ፅንሰ ሀሳቦችን (Concept) በማስረዳት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለትምህርት መሣሪያነት በማዋል የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ልማትን ለማፋጠን ጠንካራ መሠረት መጣያ መንገድ ወይም ድልድይ በመሆኑ ከአዲስ አበባ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃርም አጠናክሮ መጓዝ የማይናጋ መሠረትን እንደመጣል ይቆጠራል፡፡     

No comments:

Post a Comment