በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ
የመማር ማስተማር ን/የሥራ ሂደት
በተማሪዎች መማር ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ አዋኪ
ነገሮች እና መንስኤዎቻቸው
አዘጋጆች
1. ኃይሉ
ዲንቃ
2. አላምረው
ቁምላቸው
ግንቦት 2002 ዓ.ም.
አጠቃልሎ (Abstract)
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በትምህርት ቤቶች
ውስጥ ባለው ጤናማ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አዋኪ ነገሮችን በተለይም የተማሪዎችን መማር የሚያደናቅፉ
ወይም የሚያዘናጉ መዋያ ቦታዎች ስለመኖራቸው በማረጋገጥ እና አሳሳቢነታቸውን በማጥናት እንደዚሁም ተማሪዎችን ለተለያዩ ሱሶች በማጋለጥ
ወዳልተፈለገ ሁኔታ ውስጥ የሚያስገቡበትን ሁኔታ በመለየት ችግሩን ለመፍታት ወይም ለማቃለል የሚያስችል አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ
ለመውስድ በነበረው ፍላጎት መሠረት ችግሩ ይኖርባቸዋል ተብለው የተገመቱትን ት/ቤቶች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆንና ከአራት
ክ/ከተሞች 4 ት/ቤቶችን (እድገት በሕብረት የመጀመሪያ ደረጃት/ቤት ከልደታ፣ አፍሪካ አንድነት ቁጥር አንድ የሕዝብ
ት/ቤት ከአራዳ፣ ዶ/ር ሐዲስ ዓለማየሁ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ከቦሌ እና ከፍተኛ 12 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ከየካ)
በይሆነኝ (Purposive) የናሙና አመራረጥ ዘዴ ተጠቅሞ በመለየት እና ከየት/ቤቶቹ ትክክለኛ መረጃ ይገኝባቸዋል ተብለው የሚታመንባቸውን
ማለትም የየት/ቤቶችን ር/መምህራን፣የተማሪዎች ምክር አገልግሎት፣
የቀበሌ ት/ጽ/ቤት ኃላፊዎችን እና እንደዚሁም በትምህርት ቤቶች ከ6ኛ ክፍል በላይ ሆነው በልዩ ልዩ የተማሪዎች አደረጃጀት በመታቀፍ
ጉልህ እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን እና በሥነ ምግባራቸው የተሻሉትን ተማሪዎች በመምረጥ፤ ለተማሪዎች ለቡድን ውይይት የሚሆኑ ገዥ መጠይቆችን፣
ለሌሎች ደግሞ የቃል መጠይቆችን በማዘጋጀት በገጽ ለገጽ ውይይት (Subjective) የመረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴ በመጠቀም በጠቅላላ
ከ77 የጥናቱ አካል ከሆኑ ግለሰቦች መረጃው እንዲሰበሰብ ተደርጓል፡፡ የተሰበሰበው መረጃ ሲተነተን ለትምህርት ፍላጎት የሌላቸው፣
በሥነ ምግባራቸው የተበላሹ ተማሪዎች መኖራቸውን እና በሌሎች ተማሪዎች ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ መሆኑን ይህም በአብዛኛው በቤተሰብ
የአያያዝ ችግር እና ከቤሰቦቻቸው ጋር የተያያዘ የሥነ ምግባር ችግር እንደዚሁም የመጥፎ አራኣያነት ውጤት መኖሩን፤ በሌላ በኩል
የት/ቤቶች እና የመምህራን የተማሪዎች አያያዝ እና ለተማሪዎች ተገቢ ክብር ያለመስጠት፣ ድጋፍ ያለማድረግ፣ከዚህ በተጨማሪ የተወሰኑ
እና ልምድ የሌላቸው መምህራን መኖር እንደዚሁም በት/ቤቶች አካባቢ ያሉ “መዝናኛ” እና አዘናጊ ወይም አማላይ ቦታዎች እየተበራከቱ
መምጣት እና በተለይም የቀን ጨለማ ቤቶች (Day home Party) መኖር ተማሪዎች ጫት እና አልክሆል እንዲጠቀሙ አልፎ አልፈፎም
ሀሺሽ /ጋንጃ/ እንዲወስዱ እና በት/ቤትም ውስጥ ጭምር ይዘው እንዲገቡ ያደረጋቸው ሁኔታ መኖሩን እና ከት/ቤት እንዲቀሩ፣ እንዲያረፍዱ
እና አቋርጠው እንዲወጡ ተጽእኖ ያደረገባቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በት/ቤቶች አካባቢ ቋሚ እና ጊዜያዊ/ተማሪዎችን
ያነጣጠረ/ የንግድ ቦታዎች በመኖራቸው፣ በት/ቤቶች በር እና አጥር አካባቢ የንግድ እና የቤት መኪና በማምጣጥ እና በማቆም፣ ቁጭ
ብሎ ጫት በመቃም እና ተማሪዎች ሲወጡና ሲገቡ በተለይ ሴት ተማሪዎችን በማታለል እና በማማለል ላልተፈለገ ግብረ ሥጋ ግንኙነት፣
እርግዝናና ውርጃ እንደሚዳርጓቸው ለማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን ይህንን ችግር ለማቃለልም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ማለትም ተማሪዎች፣
መምህራን፣ ወላጆች፣ ት/ቤቶች የፀጥታ አካላት፣ እና ሕብረተሰቡ የየድርሻቸውን ኃላፊነት ቢወጡ እና ተቀናጅተው በጋራ መስራት ቢችሉ
ችግሩ ሊቃለል እና በት/ቤቶች ውስጥ በመካሔድ ላይ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ጤናማ እና ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
ማውጫ (Table of Contents)
አጠቃልሎ
(Abstract) _________________________________________________ i
ማውጫ
(Table of Contents) ___________________________________________ii
ክፍል
አንድ
1.
መግቢያ
_____________________________________________________________1
1.1.
የጥናቱ
ዳራ (Background of the Problem ____________________________1
1.2.
የጥናቱ
ችግር ምንነት (Statement of the Problem) _____________________4
1.3.
የጥናቱ
ዓላማ ___________________________________________________5
1.4.
የጥናቱ
አስፈላጊነት (Significance of the Study) ________________________5
1.5.
የጥናቱ
ወሰን ___________________________________________________6
1.6.
የጥናቱ
ውሱንነት ________________________________________________6
1.7.
አበይት
የጥናቱ ቃላት/ሐረጋት መፍቻ _________________________________7
ክፍል ሁለት
2.
የተዛማጅ ጽሑፍ ዳሰሳ
___________________________________________________8
2.1. የተማሪዎች የአደንዛዥ እጽ አጠቃቀም አጠቃላይ ሁኔታ
_____________________8
2.2. አደንዛዥ እጽ እና መጠጥ የሚጠቀሙ ተማሪዎች ልዩ ባሕሪያት
_______________10
2.3. የአደንዛዥ እጽ እና የአልኮል መጠጦች አሉታዊ ተጽእኖዎች
__________________11
2.4. የችግሩ መከላከያ ስልቶች
___________________________________________12
ክፍል ሦስት
3.
የጥናቱ ዘዴ
__________________________________________________________14
ክፍል አራት
4.
የመረጃ ትንተና
________________________________________________________15
4.1. በተማሪዎች የባሕሪ ችግሮች ስለመኖራቸው
______________________________17
4.2. የጓደኛ ጫና ስለመኖሩ
_____________________________________________19
4.3. የተማሪዎች የኋላ ጀርባ ____________________________________________21
4.4. አዋኪ ሁኔታዎች
_________________________________________________22
4.5. እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች
_________________________________________25
4.6. የተሰጡ ተጨማሪ አስተያየቶች
_______________________________________26
ክፍል አምስት
5.
ማጠቃለያ እና አስተያየት
________________________________________________28
5.1. ማጠቃለያ
______________________________________________________28
5.2. አስተያየት
______________________________________________________31
5.2.1. ተማሪዎችን በተመለከተ
______________________________________31
5.2.2. ወላጆች እና ሕብረተሰቡን በተመለከተ
____________________________32
5.2.3. ት/ቤቶችን በተመለከተ
_______________________________________32
5.2.4. መምህራንን በተመለከተ
______________________________________33
ማጣቀሻ
መጽሐፍት (References) _______________________________________34-35
አባሪዎች
(Appendices) _______________________________________________36-39
ii.
ክፍል አንድ
1.
መግቢያ፡-
1.1
የጥናቱ ዳራ (Background of the Problem)፡-
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የትምህርቱን ጥራት ለማስጠበቅ
የሚያስችል ስልት በመቀየስ፤ የጥራት ማስጠበቂያ ፓኬጁን በመጠቀም በየደረጃው ለሚገኙ የትምህርት ባለሙያዎች ተከታታይ ሥልጠና በመስጠት፤
የንቅናቄ መርሃ ግብር በማዘጋጀት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትምህርቱ ሥራ እንዲሣተፉ በማድረግ፤ በት/ቤት የተማሪዎችን ልዩ ልዩ
አደረጃጀቶች በመዘርጋትና በመጠቀም የትምህርቱን ጥራት በማስጠበቅ የተማሪዎችን የተሟላ ስብዕና እውን ለማድረግና የተጨበጠ ሁለንተናዊ
ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
በተለይ የትምህርቱን ጥራት ለማስጠበቅ በት/ቤት መሻሻያ መርሃ ግብር አማካይነት
በት/ቤቶች ውስጥ የሚካሄደውን የመማር ማስተማር ሒደት የተሣካ እንዲሆን ለማድረግ በተማሪዎችና በመምህራን መካከል ሊኖር ስለሚገባው
ጤናማ ግንኙነትና ከእያንዳንዳቸው ምን እንደሚጠበቅ በዝርዝር ተለይቶ የተቀመጠበትና በተግባር እየተገለፀ የሚገኝበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከመምህሩ ከሚጠበቀው ሙያዊ ሥነ ምግባር ባሻገር ተማሪው በስራ የሚያምን፣ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቡ የጐለበተ፣ መብትና
ግዴታውን የተገነዘበና በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ስብዕናው የተሟላ በሥነ ምግባር የታነፀ፣ ሃላፊነት የሚሰማው ሃገር ተረካቢ ትውልድ/ዜጋ
እንዲሆን ለማድረግ በጥራት ማረጋገጫ ፓኬጁ ወሣኝ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ማሻሻያ መርሃ ግብር በመቅረፅና በስራ ላይ እንዲውል
በመደረጉ በመደበኛው ትምህርት በክፍል ውስጥ ከሚሰጠው የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት በተጨማሪ ተማሪዎች በሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር
ክበብ እንዲታቀፉ በማድረግ በአመለካከታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተሻሉ ዜጐች ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ በመሠራት ላይ
ይገኛል፡፡
ሆኖም ግን ከዚህ እንቅስቃሴ በተፃራሪ ከሚጠበቀው ባሕሪ ያፈነገጡ
(Abnormality) ተማሪዎች እዚህም እዚያም መከሰታቸው አልቀረም፡፡
ከሚጠበቀው ትክክለኛ ሥነ ምግባር ያፈነገጡ ሲባል ለትምህርታቸው ትኩረት
በመስጠት ፈንታ ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታና ሁኔታ የሚያሣልፉ ማለትም ከት/ቤት የሚቀሩ ወደ ቡና ቤቶች ወይም መጠጥ ቤቶች በመሔድ
መጥፎ ባሕሪያትን የሚላመዱ፣ በጫት ማስቃሚያ ቤቶች በመገኘት የጫትና የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ በመሆን ለደባል ሱሶች ተጠቂ የሚሆኑ፤
ከዚህ ሲከፋ ደግሞ ለዚህ ችግር የተጋለጡ ሴት ተማሪዎች በግዴታና በቅፅበታዊ ስሜት በመገፋፋት አላስፈላጊ ለሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት
በመጋለጥ በለጋ እድሜያቸው ለተጨማሪ ልዩ ልዩ ችግሮች ማለትም ላልተፈለገ እርግዝና፤ ኤች አይ ቪን ጨምሮ ለአባላዘርና ሌሎች ተያያዥ
በሽታዎች ከመጋለጥ ባሻገር ለአካል፤ ለሥነ ልቦናና ለማኀበራዊ ችግሮች የሚዳረጉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህ ደግሞ ተማሪው ከራሱ
አልፎ ለቤተሰቡ ሸክም፤ ለሐገርም ማኀበራዊ ጠንቅ ይሆናል፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ ለዚህ ችግር የተጋለጡና ከባድ ፈተና ውስጥ የሚገኙ
እንዳሉ ይገመታል፡፡ አሁንም ወደ ችግሩ እየገቡ ያሉ ተማሪዎች እንዳሉ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ችግሩ በእነዚህ ተማሪዎች ላይ የሚያቆም
ሣይሆን በእድሜያቸው ተፈጥሯዊ ባሕሪና በጓደኛ ግፊት ወደ ሌሎች ተማሪዎችና ት/ቤቶች በፍጥነት የሚስፋፋበትና በመጨረሻም ትም/ቢሮውም
ሆነ የከተማው አስተዳደር ሁኔታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሥር ከመስደዱ እና
እየተካሔደ ባለው ሁለገብ እንቅሰቃሴ ላይ ሣንካ ከመፍጠሩ በፊት በፍጥነት ለመከላከል ብሎም አፋጣኝና ተመጣጣኝ የማስተካከያ እርምጃ
ለመውሰድ እንዲቻል ችግሩ ያለበትን ደረጃ የስርጭትና የአሣሣቢነቱ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለማየት በጥናት ላይ መመስረት አስፈልጓል፡፡
ስለዚህ በተማሪዎች
የመማር ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ውስጣዊ እና ውጫዊ የሆኑ አዋኪ ነገሮች ምንነት እና መንስኤዎቻቸው በሚል ርእስ
በት/ቢሮ ጥናት እንዲካሔድ ተደርጓል፡፡ ውስጣዊ ተፅዕኖ ማለት በዚህ ጥናት የተማሪዎች የእርስ በርስ ተፅዕኖ ወይም የጓደኛን ግፊት
የሚመለከት ሲሆን በተለይ ለትምህርት አደናቃፊ ወደሆኑ አልባሌ ቦታዎች
በመውሰድ በኩል የጓደኛ ተፅዕኖው ከፍተኛ ይሆናል ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ በሌላ በኩል በዚህ ጥናት ውጫዊ ተጽዕኖ ማለት ደግሞ
በጓደኛም ሆነ በሌላ ተፅዕኖ በተማሪዎች መማር ላይ የመጠጥ፤ የዝሙት፣ የጫትና የአደንዛዥ ዕፅ በትምህርታቸው ላይ እያሣደረ ያለውን
ተፅዕኖ የሚመለከት ነው፡፡
ትምህርት ቢሮው ይህንን ጥናት ለማጥናት እንዲነሣሣ ያደረጉት ምክንያቶች በቀጥታም
ሆነ በተዘዋዋሪ፤ በትምህርት ዘርፉም ሆነ በሌላው የሕብረተሰብ ክፍል በዚህ ችግር ዙሪያ እየሰጡ ያለው መረጃ አንዱ ሲሆን ከዚህ
በተጨማሪ ተማሪዎች ራሣቸው በችግሩ ውስጥ አልፈው ስለ ሁኔታው በሬዲዮ በቀጥታ እየተናገሩ ያሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ በመሆኑ ነው፡፡
ይህ ጥናት ትኩረት ያደረገው በአካባቢው መጠጥ ቤቶች፤ የምሽት ቤቶች፤ የጫትና የአደንዛዥ ዕፅ መጠቀሚያ ቤቶች ያሉባቸውንና የውጭ
ሃገር ዜጐች የሚንቀሣሱባቸው ወይም እንደመዝናኛ የሚጠቀሙባቸው ቦታዎች ባሉ ት/ቤቶች ነው፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ አካባቢ ባሉ ት/ቤቶች
ትኩረት ያደረጉ መረጃዎች በተደጋጋሚ እየደረሱ ያሉ በመሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች የሚፈጸሙት ከት/ቤት ውጭ በመሆኑና
በድብቅ የሚከናወን በመሆኑ መረጃውን በቀጥታ ለማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም በተዘዋዋሪ ከሌሎች ተማሪዎችና ከት/ቤቱ አስተዳደር በማሰባሰብ
ችግሩ በስፋት ይታይባቸዋል የሚባሉትን 4 ት/ቤቶችን ከተለያዩ 4 ክፍለ ከተሞች በመምረጥ ጥናቱን ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
1.2. የጥናቱ ችግር ምንነት (Statement of the
Problem)
በት/ቤቶች ውስጥ የሚካሔደውን የመማር ማስተማር ሂደት ጤናማ
ለማድረግ እንዲቻል ተገቢ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ እና ችግሮች ሲፈጠሩም በችግሩ ዙሪያ ጥናት በማካሔድና በተጨባጭ መረጃ የተደገፈ
የመፍትሔ ሐሳብ በማቅረብ ችግሮች ሥር ሳይሰዱ እንዲፈቱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በዚህ መሰረት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ተማሪዎች ለትምህርታቸው
ትኩረት በመስጠት ፋንታ በአልባሌ ቦታ ማለትም የቀን ²መዝናኛ²
ቦታዎች/የቀን ጨለማ ቤቶች ²Day
Home Party² የሚውሉበት ሁኔታ መኖሩን፤ አልኮል፣ ሲጋራ፣ ጫት እና ሐሺሽ
በመጠቀም ለነዚህ ነገሮች ተገዥ እየሆኑ ያሉበት ሁኔታ መኖሩን፤ ሴት ተማሪዎች በጓደኞቻቸው እና በሌሎች ሰዎች አማካኝነት እየተወሰዱ
ለአላስፈላጊ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ እርግዝና፣ መውለድ እና ማስወረድ ምክንያት ለተለያዩ የጤና፣ የማሕበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች
እየተዳረጉ መሆኑንና በአጠቃላይ ከትምህርት ገበታቸው የሚቀሩበት ፣የሚያረፍዱበት፣ አቋርጠው የሚወጡበት እና ችግሩ ሲጠንም ትምህርቱን
ከነአካቴው የሚተውበት ሁኔታ መኖሩን ከተለያዩ ምንጮች ማለትም ከመገናኛ ብዙሐን፣ ከትምህርት ባለሙያዎች፣ ከተማሪዎች፣ ከት/ቤቶች እና ከሕብረተሰቡ
በተለያየ ጊዜ የሚገለጽበት ሁኔታ ይበዛል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በተወሰኑ ት/ቤቶች ችግሩ ጎልቶ በመውጣቱ ተማሪዎች በት/ቤት
ውስጥ አደንዛዥ እጽ ሲያዘዋውሩ እጅ ከፍንጅ እስከመያዝ የደረሱበት ሁኔታ መታየቱ እና በትምህርት ሰዓት በቀን ጨለማ ቤቶች
(Day Home Party) የሚገኙበት ሁኔታ በስፋት እየታየ መጥቷል፡፡
ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ በሌሎች ሀገሮች እንደሚታየው ችግሩ
ሀገራዊና እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ሊሔድ ይችላል፡፡
ስለዚህ ችግሩን ለመከላከል እንዲቻል ት/ቢሮው ይህንን ጥናት
ለማካሔድ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው ሲሆን ጥናቱም ከዚህ በታች የተነሱትን ጥያቄዎች ይመልሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
1.
ተማሪዎች
በማይፈለጉ መዝናኛ ቦታዎች (²Day
Home Party²) እንዲዉሉ የሚደርጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
2.
ተማሪዎችን
መጠጥ፣ ጫት፣ ሐሺሽ እና ሲጋራ እንዲጠቀሙ የሚገፋፏቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
3.
ከላይ
የተጠቀሱት ችግሮች አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በት/ቤቶች ስፋት እና ጥልቀቱ ምን ያህል ነው?
4.
ችግሩን ለመቅረፍ ምን ዓይነት መፍትሔ
ቢወሰድ ይመረጣል?
1.4. የጥናቱ
ዓላማ
የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ፡-
Ø የተማሪዎችን መማር የሚያውኩትን ዋና ዋና ምክንያቶች ለመለየት፤
Ø ት/ቤቶች ከአዋኪ ነገሮች እንዲጸዱ ለማድረግ የሚያስችል የመፍትሔ ሐሣብ ለማቅረብ፤
1.3. የጥናቱ አስፈላጊነት
ይህን ጥናት ለማካሔድ የተፈለገበት ዋናው
ምክንያት የተማሪዎችን መማር የሚያውኩ ነገሮችን በመለየት እና መንስኤዎቻቸውን
በማጥናት ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል የመፍትሔ ሐሳብ ለማመንጨት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ጥናት ለሚያካሒዱ
አጥኝዎች ወይም ባለሙያዎች የጥናታቸው መነሻ በመሆን ሊያገለግል ይችላል፡፡
1.5. የጥናቱ ወሰን ፡-
ጥናቱ ከ1ዐ ክፍለ ከተሞች መካከል ችግሩ ይጐላባቸዋል ተብለው በተመረጡት
4 ክፍለ ከተሞች ውስጥ ባሉ 4 ት/ቤቶች ውስጥ ተካሔዷል፡፡
1.6.
የጥናቱ
ውሱንነት
ይህንን
ጥናት ለማካሔድ ሥራው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች ነበሩ፡፡
ü መረጃው
በሚሰበሰብበት ውቅት በተጨማሪ ደራሽ ስራዎች ምክንያት በሚፈለገው ፍጥነት ለመሄድ ያልተቻለ መሆኑ፡፡
ü መረጃውን
ለመሰብሰብ የትራንስፖርት እጥረት በመኖሩ በግል ትራንስፖርት በሚሰበሰብበት ወቅት በባለሙያዎች ጊዜ፣ ገንዘብ፣ እና ጉልበት ላይ
ቀጥተኛ ተጽእኖ ማሳደሩ፤
ü መረጃው
በመሰበሰበበት ቦታ ተደራራቢ ሥራዎች በመኖራቸው የት/ቤት አመራሮችን በሚፈለገው ጊዜ /በቀጠሮ ጊዜ ጭምር/ ለማግኘት አስቸጋሪ ሁኔታ
መፈጠሩ፡፡
ሆኖም ግን ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ቢኖሩም በጥናቱ ውጤት ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር ጥንቃቄ እና ጥረት ተደርጓል፡፡
1.6.
የጥናቱ አበይት ቃላት/ሐረጋት መፍቻ
አዋኪ፡- የተማሪዎችን
መማር የሚያደናቅፍ ወይም በየእለቱ የትምህርት ሥራቸው ላይ ጣልቃ በመግባት በመማራቸው ፋንታ ዓላማቸውን እንዲስቱ እና እንዲዘናጉ
በማድረግ፣ አእምሯቸውን በመስረቅ፣ በመያዝ እና በማማለል ወይም በመማረክ ባልተፈለገ እና ባልተጠበቀ ቦታ እንዲውሉ የሚያደርግ ጉዳይ
ነው፡፡
የቀን
ጨለማ ቤቶች (Day Home Party) ፡- ተማሪዎች ትምህርታቸውን ትተው የሚሔዱበት በውስጡም ለትምህርት
ከሚቀርቡ ነገሮች በተቃራኒ ጫት፣ ሐሺሽ፣ መጠጥ እና ሲጋራ በማቅረብ ተማሪዎች በሱስ እንዲጠመዱ፣ የትምህርት ጊዚያቸውን እንዲያባክኑ
እና በተለይም ሴት ተማሪዎች እንዲደፈሩ ምክንያት የሚሆን ሰዋራ፣ ዝግ እና ጨለማ የሆነ ቤት ነው፡፡
ክፍል ሁለት
2. የተዛማጅ ጽሑፍ ዳሰሳ
ስብእናቸው የተሟላ ብቁ ዚጎችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ከመማር ማስተማሩ
ጎን ለጎን በችግሮች ዙሪያ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሁለገብ ርብርብ ማድረግ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ በት/ቤት ውስጥ
እና ከት/ቤት ውጭ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ እና ችግሮችን በመለየት አፋጣኝ መፍትሔ መውሰድ ከተቻለ ደግሞ ጤናማ የመማር
ማስተማር ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ መሠረት ይህ ጥናት ትኩረት የሚያደርገው በት/ቤቶች አካባቢ ያሉትን አዋኪ ነገሮች
ማለትም የተማሪዎችን መማር የሚያዘናጉ ወይም እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን እና የችግሮችን ምንጭ በመለየት የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ
የሚያስችል ጥናት ለማካሔድ ነው፡፡
ከዚህ ጥናት ጋር በተያያዘ ሌሎች ጥናታዊ ጽሑፎች እና ዘገባዎች
ምን እንደሚሉ በዚህ ንኡስ ርእስ ለመዳሰስ የተሞከረ ሲሆን በተለይ የተማሪዎች የአደንዛዥ እጽ አጠቃቀም አጠቃላይ ሁኔታን በተመለከተ፣
ከአደንዛዥ እፅ፣ ከሲጋራ እና ከመጠጥ ተጠቃሚዎች ልዩ ባሕሪያት ምን ምን እንደሚመስል፣ የአደንዛዥ እጽ እና መጠጥ አሉታዊ ተጽእኖዎችን
እና የችግሩን መከላከያ ስልቶች በተመለከተ በርእስ በመከፋፈል ለማየት ተሞክሯል፡፡
2.1. የተማሪዎች የአደንዛዥ እጽ አጠቃቀም አጠቃላይ ሁኔታ
በት/ቤት ደረጃ ያሉ ወጣቶች ሁሉን ነገር ለማወቅ ካላቸው ጉጉት
የተነሳ ለተለያዩ ሱሶች የሚጋለጡበት ሁኔታ ይበዛል፡፣ ለምሳሌ በአሜሪካን ሀገር ከጠቅላላው የተማሪዎች ቁጥር ግማሽ የሚሆኑት ተማሪዎች
የመጠጥ እና የተለያዩ አደንዛዥ እፆች ተጠቃሚዎች ናቸው (Jan, Nssi, RN.BS, 2008) ፡፡ አደንዛዥ እጽ የሚወስዱበትን
ምክንያት ይኸው ፀሐፊ አያይዞ ሲገልጽ አንድም ለመነቃቃት በሌላ በኩል ጭንቀትን ለማስወገድ እና ለመዝናናት ነው፡፡
ይህንን አደንዛዥ እጽ በአብዛኛው የሚጠቀሙት የትኞቹ ተማሪዎች ናቸው?
ለሚለው ደግሞ እድሚያቸው ከ12 እስከ 17 የሆኑት ታዳጊዎች ሲሆኑ በተለይ በአሜሪካ እና በካናዳ በአመት በጠቅላላው በመጠጥ ምክንያት
ከ100,000 በላይ ሰዎች እንደሚሞቱ ተረጋግጧል
(Professional Guide to Starting a Day Care)፡፡ ከላይ ያሉትን ነገሮች ስንመለከት አለም አንድ መንደር
እየሆነች ባለችበት ሁኔታ በአሜሪካ እና በሌሎች ያደጉት ሀገራት እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች የሚታዩ ከሆነ ችግሩ በኛም ሀገር በፍጥነት
አሳሳቢ ወደሆነ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል አሁን ካሉት ምልክቶች መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ከላይ በተገለጸው እድሜ ክልል
ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ለችግሩ ተጋላጭ መሆናቸው ችግሩን የከፋ ሊያደርገው እንደሚችል ይታመናል፡፡ ምክንያቱም እድሚያቸው በዚህ ደረጃ
ያሉ ልጆች በባህሪያቸው ፈጣንና ሁሉን ነገር ለማወቅ የሚፈልጉ በመሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ Lopez Gatcia KS, Costa Junior ML.(2008) ሲገልጹ የታዳጊ
ወጣትነት እድሜ ለሕይወት አደገኛ የሆኑ ባህሪያትን ለምሳሌ እንደ አደንዛዝ እጽ ያሉትን ነገሮች ለመጀመር ምቹ እና ተጋላጭ የሆነ
የእድሜ ክልል ነው ይላሉ፡፡
በሀገራችን ሁኔታ ስንመለከትም በተማሪዎች ደረጃ አደንንዘዥ እጽ እና
መጠጥ የመጠቀም አዝማሚያ/ምልክቶች እንዳሉ የሚጠቁሙ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ከተካሔዱት ጥናቶች ባሻገር በተለይ በአዲስ አበባ ተጨባጭ
ሁኔታ ተማሪዎች በብዙዎች ዘንድ ከተለመዱት ጫት እና መጠጥ ጀምሮ አደገኛ የአደንዛዥ እፆችን እስክ መጠቀም እና በት/ቤቶች ውስጥ
እስከማዘዋወር የደረሱበት ሁኔታ መኖሩን ስንመለከት ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በውጭ ሀገር እንደምናየው አሳሳቢ ወደሆነ ደረጃ ሊሸጋገር
ይችላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ መስፍን ካሣዬ፣ 1998 በአዲስ አበባ ከተማ እና በቡታጅራ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ላይ ባካሔደው
ጥናት በግል እና በመንግስት ት/ቤቶች አልኮል መጠጦች እና ጫት የሚጠቀሙበት ሁኔታ መኖሩን ለማረጋገጥ የቻለ ሲሆን በሌላ በኩል
በአዲስ አበባ ከግል ት/ቤቶች ውስጥ 48% ሲጋራ እንደሚጠቀሙ፣ 31% ደግሞ ካናቢስ የሚባለውን
አደንዛዥ እጽ እንደሚጠቀሙ በጥናቱ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡
2.2. አደንዛዥ እጽ እና መጠጥ የሚጠቀሙ ተማሪዎች ልዩ ባሕሪያት
አደንዛዥ እጽ የሚጠቀሙ ሰዎች ከዚያ በፊት በተፈጥሮ እና በሂደት
ካዳበሩት አንፃራዊ የሆነ ጤነኛ ባሕሪ ለየት ባለ ሁኔታ እነርሱነታቸውን በመቀየር እጹ በሚያሳድርባቸው ተጽእኖ ምክንያት በሕብረተሰቡ
የማይፈለጉ ወይም ነውር የሆኑ ባሕሪያትን እንዲፈጽሙ እና የወሰዱት ባእድ ነገር በመራቸው እና ባዘዛቸው ሁኔታ እና ቦታ ላይ ሊያውላቸው
ይችላል፡፡
በተለይ መጠጥ የሚጠቀሙ ተማሪዎች የሚታይባቸውን ባህሪ በተመለከተ
The Higher Education Center for Alcohol and other Drug Abuse and Violence
Prevention (2010) ሲገልጽ ዱለኞች/ተደባዳቢዎች፣ አጉራ ዘላሎች፣አስገድዶ ደፋሪዎች፣ ልቅ የግብረ ሥጋ ፈፃሚዎች፣ እና
በት/ቤት ግቢ ውስጥ በመጠጣት የመማር ማስተማሩን ሂደት አዋኪዎች ናቸው በማለት ይገልፃቸዋል፡፡
የአደንዛዥ እጽን ችግር ለመከላከል እና በተማሪዎች መማር ላይ የሚሳድረውን
ተጽእኖ ለመቀነስ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮች (Barriers) እንዳሉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህን እንቅፋቶች በሁለት ዋና ዋና
ክፍሎች ይመድቧቸዋል (Working with Schools to Prevent Substance Abuse) ፡፡ እነዚህም፡-
A. አካባቢያዊ (Environmental) _ ከትም/ ሂደቱ ውጪ ያሉ ነገሮች
በዚህ ውስጥ የሚጠቀሱት
Ø
በሌሎች ሰዎች መገለልና
²የማይረባ² ሰው ተደርጎ መወሰድ፤
Ø
በሚፈጠር የኢኮኖሚ
አቅም የመግዛት ወይም የማድረግ አቅም ማደግ፤
Ø
በቤተሰብ መፍረስ
በሚፈጠር የጤና መታወክ፤
Ø
የቤተሰብ ክትትል
ያለማድረግ እና ለልጆች ተገቢ የሆነ የመዝናኛ ጊዜ እና ቦታ የመምረጥ ችግር፤
Ø
በተማሪዎች ሕይወት
እና የአኗኗር ዘይቤ በአፍራሽነቱም ሆነ በገንቢነቱ አራአያ ሊሆኗቸው የሚችሉ ሰዎች ከቴሌቪዥን፣ ከተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ከጓደኞቻቸው
ሊያገኙበት የሚችሉበት ሁኔታ መኖራቸው፤
B. ውስጣዊ (Systemic)
ከመማር ማስተማር ሂደቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሲሆኑ፤
Ø
የጤና ትምህርት
በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ያለመካተት እና ሥለ አደንዛዥ እጽ ትኩረት ያለመስጠት ችግር፤
Ø
የተወሰኑ መምህራን
የአደንዛዥ እጽ አጠቃቀምን ለመከላከል አርአያ ያለመሆን፣ ጠንካራ እምነት ያለመያዝ እና በቂ ስልጠና ያለማግኘት ችግር፤
Ø
መንግሥታዊ የሆኑ
ቢሮዎች እና የባለስልጣን መ/ቤቶች ውጫዊ እና ውስጣዊ ትስስር ማነስ እና የመናበብ ችግር፤
Ø
ገዢ የማስፈጸሚያ
ስልቱን ከመፈጸም አኳያ የዝግጁነት/የተነሳሽነት እና የአቅም ውሱንነት ችግር፤
Ø
በችግሩ ዙሪያ ወላጆችን
ከማሳተፍና ድጋፍ ከመስጠት ወጣገባነት የመኖር ችግር፤
Ø
የባለብዙ ባሕል
ፍላጎቶችን እና የልዩነት ጉዳዮችን በብቃት የማስተናገድ ውሱንነት መኖር፤
Ø
በት/ቤቶች እና
በሌሎች መ/ቤቶች መካከል የግንኙነት መላላት ችግር፡፡
2.3. የአደንዛዥ
እጽ እና የአልኮል መጠጦች አሉታዊ ተጽእኖዎች
አልኮል መጠጥ እና አደንዛዥ እጽ የሚጠቀሙ ተማሪዎች በትምህርት ውጤታቸው፣
በጤናቸው፣ በማሕበራዊ ግንኙነታቸው እና በኢኮኖሚያቸው ላይ ቀጥተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖዎች ያሳድራሉ (Lopez Gatcia KS, Costa Junior ML.፣
2008፣ The Higher Education Center for Alcohol and other Drug Abuse and Violence
Prevention 2010; Brook David 1994; Dereje Kebede et.al. 2005)፡፡
የአልኮል መጠጥ አጠቃቀም ከማሕበራዊ ጠንቀነቱ አንፃር ሲታይ
በ Spearman’s Correlation Co-efficient ቀመር መሠረት የከልኮል መጠጥ እና የማሕበራዊ አፍራሽ ባሕሪ ቀጥተኛ
ግንኙነት አላቸው(Lopez Gatcia KS, Costa Junior ML.፣ 2008)፡፡
በሌላ በኩል በ
Jill Grove (2002) ግኝት መሠረት አደንዘዥ እጽ የሚጠቀሙ ወጣቶች ዝቅተኛ በራስ የመተማመን ባሕሪ ስለሚኖራቸው ደካማ ተግባቦት
እና ራስን የመግለጽ ችግር ያጋጥማቸዋል ይላል፡፡
አልኮል መጠጥ እና አደንዛዥ እጽ የሚጠቀሙ ተማሪዎች ልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት
የመፈፀም፣ አስገድዶ የመድፈር እና ያልተፈለገ እርግዝና የሚያስከትልበት ሁኔታ እንዳለ የጥናት ውጤቶች ያሳያሉ፡፡
ከተማሪዎች
ውጤት ጋር በተያያዘም አደንዛዥ እጽ እና የአልኮል መጠጥ ምን አይነት ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል? በሚለው ዙሪያ በርካታ መፅሐፍት በተማሪዎች ውጤት ላይ ቀጥተኛ የሆነ አሉታዊ
ተጽእኖ እንደሚኖራቸው አረጋግጠዋል፡፡ በተለይ Brandon, 2002 እንደጠቀሰው በ10,000 የአሜሪካን የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ ባካሔደው ጥናት
አደንዛዥ እጽ ከሚጠቀሙት ይልቅ የማይጠቀሙት የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል/በሒሳብ ስሌት፣ በምንባብ እና በጽሑፍ ውጤታቸው አደንዛዥ
እጽ የማይጠቀሙት ከሚጠቀሙት በላይ ውጤታቸው 53፣ 24 እና 53 በቅደም ተከተል ያስመዘገቡበትን ሁኔታ እናያለን/፡፡ በዚሁ ጥናት
ላይ በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ በተካሔደው ጥናት አደንዛዥ እጽ የማይጠቀሙ እና በሕገወጥነት/በወጣት ጥፋተኝነት መዝገብ
ውስጥ የሌሉ ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
በሌላ በኩል በሌላ የጥናት በ14,000 ተማሪዎች ላይ በተካሔደው ጥናት 21.6% የሚሆኑት ጠጥተው ወደ ትምህርት ቤት በመግባታቸው በትምህርታቸው
የደገሙ ሲሆን 29.5% የሚሆኑት ደግሞ በመጠጥ ምክንያት ከትምህርት ቤት የሚቀሩ ሆነው
ተገኝተዋል (The Higher Education Center for Alcohol and other Drug Abuse and
Violence PreveNtion፣ 2010) ፡፡
2.4. የችግሩ መከላከያ ስልቶች
ይህንን ዓይነት አሳሳቢ ማሕበራዊ ችግር ለመከላከል ወይም የአደገኛነቱን
ደረጃ ለመቀነስ እና በተለይም በት/ቤቶች ውስጥ ጤናማ የመማር ማስተማር ሁኔታ ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡ እንዚህ የመከላከያ
ስልቶችን ነበጥንቃቄ በማየት እና በትክክል ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መስራት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ከተመለከቱት
የተወሰኑትን መራርጦ ማየት ችግሩን ለማቃለል የሚያስችል የመፍትሔ ሐሣብ ለማፈላለግ እንደ መነሻ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡
Office of Mental Health and Addiction
Services በሚለው ውስጥ አልኮል፣ ሲጋራ እና ሌሎች አደንዛዥ እፆችን አጠቃቀም ለመከላከል የተሻለው አማራጭ ስልት በተማሪዎች
ላይ አዎንታዊ የባሕሪ ለውጥ (Positive Behavior Change) በማምጣት መሆን አለበት ይላል፡፡ እነዚህም በዝርዝር ሲገለጹ፡-
v የውስጣዊ ግፊት ምንነትን እንዲገነዘቡ መርዳት ለምሳሌ ከአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚዎች
ጋር የመቀራረብ ውስጣዊ ፍላጎትን ውጫዊ ግፊት ማለትም የጓደኛ የመገፋፋት እና ወደ ሱስ እንዲገቡ የማግባባት አመለካከት ቀድሞ የመገንዘብ
ክህሎት እንዲያዳብሩ ማገዝ፤
v አነዚህን ግፊቶች ለመቋቋም እና ለመቃወም የሚያስችል ውስጣዊ ስብእና እንዲያጎለብቱ
እና ማሕበራዊ ክህሎታቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያስችላቸውን ሁታዎች ማመቻቸት፤
v በመልካም አርዓያነታቸው የሚታወቁትን ተማሪዎች በመጠቀም "ማንም የሚያደርገው ነው” የሚለውን መልካም ያልሆኑ የጓደኛ እና የአቻዎቻቸውን
አደገኛ የማዘናጊያ ምክሮች እንዳይከተሉ ስልት መቀየስ፤
v ተገቢ
የሆነ፣ ደረጃውን የጠበቀና ከሁኔታዎች ጋር የሚሔድ ጽሑፎችን በማዘጋጀት የአልኮል መጠጠን፣ የሲጋራን እና አደንዛዥ እጽን የአጭር
ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ጉዳቶች የማሳወቅ ሥራ መስራት፤
v አሳታፊ የማስተማር ዘዴ በመጠቀም ማለትም Role Play,
Discussions, brainstorming and cooperative learning የተማሪዎችን ግንዛቤ ማዳበር፤
v በአመት ውስጥ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን በመለየት እና
በማዘጋጀት በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ ማድረግ፤
v ወላጆችን እና ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የተቀየሱትን የመከላከል ስልቶች ውጤታማ ማድረግ ያስችላል፤
v መምህራን በስርዓተ ትምህርቱ ውስጥ በማስገባት ለማስተማር እንዲችሉ
ተገቢ ስልጠና መስጠት፤
v የምናዘጋጀው የማስተማሪያ ማቴሪያል ለተማሪዎች ባሕላዊ እሴት
የጠበቀ እና መምህራን በቀለላሉ እንዲያስተምሩበት ሆኖ መዘጋጀት አለበት፡፡
ክፍል
ሦስት
3. የጥናቱ ዘዴ
የተማሪዎችን የመማር ሁኔታ
ሊያውኩ የሚችሉ ተፅዕኖዎች በሁሉም ት/ቤቶች በእኩል ደረጃ ይኖራሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ስለዚህ ችግሩ ይበልጥ የሚታይባቸውን ት/ቤቶች
በውል ለይቶ በማጥናት አስቀድሞ ከአስሩም ክፍለ ከተሞች መረጃ ማግኘት አስፈላጊ ነበር፡፡ በመሆኑም ለአሥሩም ክፍለ ከተሞች ስልክ
ተደውሎ የጉዳዩን አሳሳቢነት ደረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከክፍለ ከተሞች በተገኘው መረጃ መሠረት ከየካ ክፍለ ከተማ የከፍተኛ 12
2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ከቦሌ ክፍለ ከተማ የዶክተር ሐዲስ አለማየሁ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ የእድገት በሕብረት
የመጀመሪያ ደረጃና ከአራዳ ክፍለ ከተማ የአፍሪካ አንድነት ቁጥር አንድ የመጀመሪያና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የችግሩ ሰለባ እንደሆኑ
ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለዚህ እነዚህ አራት ት/ቤቶች የጥናቱ ትኩረት ሆነው ተወስደዋል፡፡ በመሆኑም በነዚህ አራት ት/ቤቶች በተለይ
በእያንዳንዱ ት/ቤት ስላለው የተፅዕኖ ሁኔታ በረጃውን በጥልቀት በመዳሰስ ገላጭ የሆነ መረጃ እንዲሰበሰብ ተደርጓል፡፡ ለመረጃ ምንጭነት
አራቱ ት/ቤቶች የተወሰዱ በመሆኑ ለዚህ ጥናት በተግባር የዋለው ኢላማዊ የውስን ጥናት (case study) ዘዴ ነው፡፡
ለዚህ ጥናት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ቃለ መጠይቅና የቡድን ውይይት
(Focus Group Discussion) የመረጃ ማሰባሰቢያ መሣሪያዎች ሆነው አገልግለዋል፡፡ በቃለ መጠይቅ አማካኝነት ከርእሰ መምህራን፤
ከጋይዳንስና ካውንስሊንግ እና ት/ቤቶቹ ከሚገኙበት የቀበሌ ት/ጽ/ቤቶች ተወካዮች አስፈላጊው መረጃ እንዲሰበስቡ ተደርጓል፡፡ እነዚህን መረጃዎች ይበልጥ አስተማማኝ
ለማድረግ በየትምህርት ቤቱ ከተቋቋሙት የተማሪዎች መማክርት እና ወይም የተማሪዎች ፓርላማ አባላት፤ ከተማሪዎች ካውንስልና ወይም
ከሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ኮሚቴዎች እንዲሁም ከሴት ተማሪዎች ክበባት ጋር የቡድን ውይይቶች በማድረግ ተጨማሪ መረጃዎች ለማሰባሰብ
ተችሏል፡፡ የተሰበሰቡት መረጃዎች በገለፃ ዘዴ (qualitative) እንዲተነተኑ ተደርጓል፡፡
መረጃ ይሰበሰብባቸዋል ተብለው ከታሰቡት አራት የቀበሌ ት/ጽ/ቤት ኃላፊዎች ውስጥ ሁለቱ በስራ
መደራረብ ምክንያት መገኘት እና መረጃ መስጠት አልቻሉም፡፡
ክፍል አራት
4. የመረጃ ትንተና ፡-
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ የመንግሥትና የሕዝብ ት/ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች
ትምህርታቸውን በትኩረት እንዳይከታተሉ የሚያደርጉ ወይም የመማር ማሰተማር ተግባራትን የሚያውኩ ሁኔታዎች በተለይም ከ ²Day
home party² አካባቢ እና ተግባር ጋር ቁርኝት ያላቸውን ችግሮች ለይቶ ለማጥናትና የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ
ያመች ዘንድ ከክፍለ ከተሞች ጋር በተደረገው የመረጃ ልውውጥ ችግሮቹ ይበልጥ ጎልተው ይታዩባቸዋል ከተባሉት አራት ትምህርት ቤቶች
ውስጥ ከተለያዩ የት/ቤት ማሕበረሰብ አባላትና የቀበሌ ት/ጽ/ቤቶች የተሰበሰበው መረጃ ከዚህ ቀጥሎ ለትንተና ቀርቧል፡፡ ለጥናቱ
የተመረጡት አራቱም ት/ቤቶች በትንተናው እንዲካተቱ ተደርጓል፣ ለጥናቱ እንደ መረጃ ምንጭነት ተሳትፎ በማድረግ ያገለገሉ የጥናቱ
አካላት ማለትም ተማሪዎችንና የትምህርት ባለሙያዎችን ብዛት እና ስብጥር በተመለከተ በሚከተለው ሠንጠረዥ ተመልክቷል፡፡
ሠንጠረዥ 1፡ የመረጃ ምንጮች
ተ.ቁ
|
ት/ቤት
|
ፆታ
|
የተሳታፊ
ተማሪዎች ክፍል ደረጃ
|
የተማሪዎችአማካሪና
ርእሰ መምህራን
|
የቀበሌ
ት/ጽ/ቤት
|
ጠቅላላ
ድምር
|
|||||
6ኛ
|
7ኛ
|
8ኛ
|
9ኛ
|
1ዐኛ
|
ተ
|
ሌሎች
|
|||||
1
|
ዕድገት በሕብረት
/ቂርቆስ ክፍለከተማ/
|
ወ
|
6
|
7
|
1
|
--
|
--
|
2
|
--
|
14
|
2
|
ሴ
|
6
|
4
|
12
|
--
|
--
|
1
|
1
|
22
|
2
|
||
2
|
አፍሪካ አንድነት ቁ.2
/አራዳ/
|
ወ
|
--
|
2
|
1
|
|
2
|
1
|
--
|
5
|
1
|
ሴ
|
--
|
1
|
2
|
2
|
2
|
--
|
--
|
7
|
--
|
||
3
|
ዶ/ር ሐዲስ 2ኛ ደ/ት/ቤት
/ቦሌ ክፍለ ከተማ/
|
ወ
|
--
|
--
|
--
|
1
|
3
|
2
|
1
|
4
|
3
|
ሴ
|
--
|
--
|
--
|
3
|
3
|
--
|
--
|
6
|
--
|
||
4
|
ከ/12 2ኛ ደ/ት/ቤት
/የካ/
|
ወ
|
--
|
--
|
--
|
1
|
2
|
1
|
--
|
3
|
1
|
ሴ
|
--
|
--
|
--
|
1
|
5
|
1
|
--
|
6
|
1
|
||
|
67
|
10
|
እላይ ከሠንጠረዥ አንድ መመልከት እንደሚቻለው ለጥናቱ ከተመረጡት ት/ቤቶች ውስጥ የመጀመሪያ
ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተማሪዎች በመረጃ ምንጭነት የተሳተፉ ሲሆን ከፆታ አንፃር ሲታይ 52% ሴት ተማሪዎች ሲሆኑ
42% ደግሞ ወንድ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ በተጨማሪ በጥናቱ እንደ መረጃ ምንጭነት በናሙና የተወሰዱት ርእሰ መምህራን የተማሪዎች የምክር
አገልግሎትና የቀበሌ ት/ጽ/ቤት ኃላፊዎች ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ ከአራቱም ት/ቤቶች ርእሣነ መምህራን በተደረገው ቃለ መጠይቅ አስፈላጊው
መረጃ ተሰብስቦ ለትንተና የቀረበ ሲሆን ከቀበሌ ት/ጽ/ቤት ኃላፊዎች ሁለቱን ለቃለ መጠይቅ በተወሰነው ቀጠሮ መሠረት እንዲገኙ በማድረግ
/በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የቀበሌ 15/16 እና ከቦሌ ክፍለ ከተማ የቀበሌ ዐ4/ዐ6/ዐ7 ቀበሌ ት/ጽ/ቤቶች/ መረጃው እንዲሰበሰብ
ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል የእድገት በሕብረት ት/ቤትና የካ ከፍተኛ 12/ 2ኛ ደ/ት/ቤት የተማሪዎች አማካሪዎች ጠቃሚ መረጃዎችን
በመስጠት የተባበሩ ሲሆን በጥናቱ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡
በተማሪዎች የቡድን ውይይት ውስጥ ከ6ኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች እንዲካተቱ የተደረገ ሲሆን
እነዚህም የተመረጡበት ምክንያት ከዚህ የክፍል ደረጃ ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች ከዝቅተኛ ክፍሎች ተማሪዎች በዕድሜም ሆነ በአስተሳሰብ
በአንፃራዊነት የበሰሉ ናቸው ተብሎ በመገመቱና ሃሣባቸውን በነፃ ሊገልፁ ይችላሉ ተብሎ ስለታመነበት ነው፡፡ በቡድን ውይይቱ የተሳተፉ
ተማሪዎች ብዛትና የፆታ ስብጥር ከት/ቤት ት/ቤት የተለያየ ሲሆን ለዚህም ምክንያት ሆኖ የተገኘው በየት/ቤቶቹ ባሉት የተማሪዎች
አደረጃጀት ዓይነትና ስብጥር ነው፡፡ በአጠቃላይ ለጥናቱ እንደ መረጃ ምንጭ እንዲያገለግሉ በይሁንታ (Purposive
Sampling) ናሙና አመራረጥ ዘዴ ከተወከሉት አካላት ከ9ዐ%
በላይ በመገኘታቸው የተሰበሰበው መረጃ በገለፃ ዘዴ እንዲተነተን ተደርጓል፡፡
4.1
. በተማሪዎች የባህሪ ችግሮች ስለመኖራቸው
የተማሪዎች የባሕሪይ ችግር
የመማር ማስተማር ተግባራትን ከሚያውኩት ጉዳዮች እንደ አንድ ዋና ችግር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከአራቱም ት/ቤቶች
ተማሪዎች ጋር የተደረገው የቡድን ውይይት በርካታ የሥነ ሥርዓት ችግር ያለባቸው ተማሪዎች በየት/ቤቶች መኖራቸውን አመልክቷል፡፡
እንደ መገለጫ ከቀረቡት ችግሮች መካከል መቅረት፤ ማርፈድ፣ ዩኒፎርም ለብሶ ት/ቤት ያለመገኘት፣ ከመምህራን ጋር መጣላትና መዳፈር፣
በትምህርት ሰአት አቋርጦ መሄድና ሲኒማ ቤቶች መግባት ወይም ሌላ ቦታ መሄድ /በሁለቱም ፆታ/፣ በትምህርት ሰዓት ጠጥቶ መግባት፣
ጫት መቃምና ሲጋራ ማጨስ በሁሉም በናሙና በተካተቱ ት/ቤቶች የሚታዩ የባሕሪይ ችግሮች መሆናቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለነዚህ የባሕሪይ ችግሮች መንስኤዎች ይሆናሉ /ይህ ባሕሪ ያጠቃቸዋል/ ተብለው
በተመረጡት ላይ በቡድን ውይይት ወቅት ነጥረው የወጡት ነጥቦች፡-
§ የመኖሪያ አካባቢ ሁኔታ
§
የአቻ ግፊት mood, fam,
fami, style, go down with Nazi girls በሚሉ አባባሎች /አፍሪካ አንድነት ት/ቤት/ ተፅእኖ ሥር መውደቅ፣
§
የቤተሰብ የኑሮ ሁኔታ የሚያጨሱ፣
የሚጠጡ፣ የሚቅሙና የሚጠጡ ወላጆች መኖር፣
§
የታላላቆች ባሕሪይ መጥፎ መሆንና
ሕፃናት /ተማሪዎች እነሱን መከተል
§
ለታዳጊዎች በተለየ ሁኔታ የተዘጋጁ
ወይም በሚድያ የሚተላለፍ ኘሮግራም ያለመኖር
§
በአንዳንድ ት/ቤቶች ሠዋራና ለመደበቂያ
የሚያመቹ ቦታዎች መኖር
§
አንዳንድ ድርጊቶች የዘመናዊነት መገለጫ
ተደርገው መወሰዳቸውና ተማሪዎች በዕድሜ ምክንያት ሁሉንም የመሞከር ሁኔታ የራስ አስተሳሰብ፣ አስተዳደግ፣ የት/ቤቶች አካባቢያዊ
ሁኔታ /ዕድገት በሕብረት ት/ቤት/
§ ለትምህርታቸው ትኩረት የማይሰጡና ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ፣ የመምህሩ የትምህርት አሠጣጥ ሁኔታና
ችግር፣ አካባቢያዊ ተፅዕኖ /ጫት፣ ከረንቡላ፣ ቪዲዮ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች በት/ቤቶች አካባቢ መኖር/ በቀድሞ ተማሪዎች የሚደረግ
ግንኙነት /በተለይ ሴት ተማሪዎች/፣ የቤተሰብ አቋም /ኢኮኖሚ ሁኔታ/፣ የት/ቤቶች የቁርጠኝነት ችግር እና የቁጥጥር መላላት፣ የመምህርና
ተማሪ ተገቢ ያልሆኑ ግንኙነት /ዶ/ር ሀዲስና ከፍተኛ 12 2ኛ ደ/ት/ቤት/ ዋና ዋናዎቹ ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡
በየት/ቤቶቹ የሥነ ምግባር ችግሮች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ከየት/ቤቶቹ ርእሣነ መምህራንና የተማሪዎች
መማክርት ጋር በተደረገው ቃለ መጠይቅ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በሁሉም ት/ቤቶች በሥነ ምግባር ችግር ምክንያት ርእሰ መምህራን
ጋር ቀርበው እርምጃ የተወሰደባቸውና ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች /ወንድና ሴት ተማሪዎች ጭምር/ መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ አንዷ
ሴት ወላጆቿ ወደ ሥራ ሲሄዱ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የሀሺሽና የሲጋራ ማጨስ ኘሮግራም እስከ ማዘጋጀት ድረስ የደረሰች መኖሯን
/አፍሪካ አንድነት ት/ቤት/ እነዚህም ተማሪዎች ራሣቸው ችግራቸውን ለማማከር እንደሚመጡ፣ ከዚህም ውስጥ ሴቶች እንደሚበዙ ምክንያቱም
ብዙ ሴት ተማሪዎች በወንድ ጓደኞቻቸው የፍቅር ደብዳቤ ስለሚፃፍላቸውና ስለሚጠየቁ የምክር አገልግሎት ለማግኘት እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል፡፡
/ዕድገት በሕብረት ት/ቤት/ በተጨማሪም ከHIV ጋር የሚኖሩ ከቤተሰብ የተጣሉ፣ የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ መወሰን ያቃታቸው በዘመድ
የተደፈሩ፣ ከመምህራን ጋር በፍቅር የወደቁ፣ በሱስ ተጠቂ የሆኑ እና ሌሎች ሚሰጢራዊ በሆኑ ጉዳዮች የምክክር አገልግሎት የሚፈልጉ ተማሪዎች መኖራቸውን ለማረጋገጥ
ተችሏል፡፡ ለምሣሌ፡- በቅርቡ አንዲት የዕድገት በሕብረት ት/ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ በሰፈሯ ወደ
ሱቅ ተልካ ስትሄድ በመንገድ ተጠልፋ በ3 ወንዶች ከተደፈረች በኋላ በምስጢር ለጐረቤት አሳውቃ ስትመረመር የHIV/AIDS ቫይረስ
ተጠቂ ሆና በመገኘቷ ልታማክር መምጣቷን፣ በመሆኑም ልጅቷን በማረጋጋት ላይ እንደሚገኙና ጉዳዩም በጐረቤቷና በመምህርቷ በምስጢር
የተያዘ እንደሆነና ወላጆቿ እስከአሁን ምንም እንደማያውቁ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን ብዙዎቹ ተማሪዎች በራሣቸው ፍላጐት፣ በመምህራንና
በአስተዳደር በወላጆች አማካይነት ከጓደኞቻቸው ምክር እያገኙ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡
4.2
የጓደኛ ጫና ስለመኖሩ
በትምህርት ቤቶች በጓደኛ ጫና ለሲጋራ፣
ለጫት፣ ለመጠጥ፣ ለሀሺሽና ለግብረ ሥጋ ግንኙነት የተገፋፉ ተማሪዎች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡ እንደ ምሣሌ በዕድገት በሕብረት ት/ቤት
ያሉ አንዳንድ የሁለቱም ፆታ ተማሪዎች ጓደኛሞች በትምህርት ሰዓት ከት/ቤት በመውጣት ተያይዘው የሚሄዱ ወንድና ሴት ተማሪዎች ያሉ
መሆኑንና አንዳንድ ጊዜ በሲኒማ ቤቶች ወይም በኤግዚቪሽንና ሌሎች ዝግጅቶች ቦታ ላይ በመቀጣጠር ግንኙነት የሚያደርጉ የሚጠጡና የሚባልጉ
ተማሪዎች መኖራቸውን ከተማሪዎች ቡድን ውይይት የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ጠፍተው ቆይተው የሚመጡ አሉ፣ ብዙ ጊዜ ግን በድብቅ
ስለሚያዝ አይታወቅም፡፡ በዕድገት በሕብረት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት አንዲት የ7ኛ ክፍል ተማሪ በጓደኛዋ ተባብላ ከወንድ ጋር እንድትገናኝ
በመደረጉ አርግዛ ለመውለድ የበቃች መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ለተወሰነ ጊዜ ትምህርቷን ካቋረጠች በኋላ አሁን ተመልሳ ትምህርቷን ልትቀጥል
መቻሏን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተመሣሣይ መልኩ በየካቲት ወር አንዲት ተማሪ በጓደኛዋ አማካይነት ተወስዳ ለአንድ ማንነቱ ለማይታወቅ
ሰው እንድትገናኝ ከተደረገች በኋላ ለአንድ ሣምንት እዚያ ከርማ የተመለሰች ሲሆን ወላጆቿ ተደናግጠው ለት/ቤቱ ጥያቄ ቢያቀርቡም
ልጅቷ የት፣ ለምን እና ማን ጋር ከርማ እንደመጣች መናገር ፈቃደኛ ባለመሆኗ ጉዳዩ በስውር ክትትል እየተደረገ እንደሆነ ከርዕሰ
መምህራንና ከተማሪዎች መማክርት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በሁሉም ት/ቤቶች ከሚገኙ ተማሪዎች በአብዛኛው
ከደሃ ቤተሰብ የመጡ በመሆናቸው ገንዘብ የሚሠጣቸው ሰው ካገኙ ሊባልጉና ለአልባሌ ተግባራት ሊጋለጡ እንደሚችሉ መገመት እንደሚቻል
ርዕሰ መምህራንና የተማሪዎች ምክር አገልግሎት መምህራን አመልክተዋል፡፡
§ በአፍሪካ አንድነት ቁ.1 ት/ቤት ርዕሰ መምህር ጋር የተደረገው ቃለ መጠይቅ እንደሚያመለክተው
በቋሚነት ሐሺሽ/ዕፅ የሚያጨሱ ከሌላ ት/ቤት ተዛውረው የመጡ ተማሪዎች እንዳሉና ተማሪዎችን አንድ በአንድ እየመለመሉ ራስ መኮንን
አካባቢ ወደሚገኘውና ‹‹ቻኔል አምስት›› በመባል ወደሚታወቀው ዴይ ሆም ፓርቲ ቤት የሚወስዱ ተማሪዎች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ብዙዎቹን ተማሪዎች አስለምደዋቸዋል፡፡ ይህንን ተግባሩን መተው ባለመቻሉ አንድ ተማሪ ከት/ቤት
ተወግዷል፡፡ በተመሣሣይ መልኩ ካቴድራል ት/ቤት አካባቢ ኮካ-ፑል የሚባል ካፌ ቤት መኖሩንና እዚህ አካባቢ የካቴድራል ተማሪዎች
እንደሚያዘወትሩበት፣ ጋንጃ የሚባል ዕፅም እንደሚያጨሱበትና በሴቶች ተማሪዎች ጭምር የሚዘወተር በመሆኑ ችግሩ ተለይቶ ተማሪዎች በፖሊስ
እጅ ከፍንጅ የተያዙ ቢሆንም እስከ አሁን ምንም የተደረገ ወይም የተወሰደ እርምጃ ያለመኖሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
§ በሌላ በኩል በዕድገት በሕብረት ት/ቤት በሴት ጓደኛ ጫና ከውጪ ሃገር ሰዎች ጋር የሚገናኙ
ሴቶች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡ በተለይ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ እየተመላለሰ ²እረዳችኋለሁ²
በማለት ሴት ልጆችን እንደሚያጠምድ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ከዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ እና ከከ/12 ወደ አልባሌ ቦታ እንደሚወስዷቸውና
እነሱን እንዲመስሉ እንደሚያደርጓቸው፣ በግቢ ውስጥ ጫትና ሲጋራ ይዘው የሚገቡ ተማሪዎች በመኖራቸው ሌሎች ተማሪዎች ወደ እነርሱ
እንዲሄዱ እንደሚያደርጓቸው፣ የተለያዩ ሱሶች ያለባቸው ተማሪዎች የገንዘብ ምንጭ ለማግኘት ብለው ሌሎች ተማሪዎች በሱስ እንዲጠመዱ
እና የገንዘብ ምንጭ እንዲሆኗቸው እንደሚያደርጉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
4.3
የተማሪዎች የኋላ ጀርባ
የባሕሪይ ችግር ያለባቸው እነዚህ ተማሪዎች የኋላ ታሪካቸው ሲታይ ከድሃ ቤተሰብ የመጡ፣ ወላጆቻቸው በጫት፣
በሲጋራና በሌሎች ተመሣሣይ ሱስ በሚያስይዙ ነገሮች ጠላ፣ አረቂና ሌሎች መጠጦች ንግድ ላይ የሚሣተፉና ራሣቸውም በነዚህ ሱሶች የሚታወቁ
መሆናቸው፣ ከቤተሰብና ከሌላም ሥርቆት እንደሚፈፅሙ፣ ለምሣሌ፡- ሁለት
ልጆች ጐላ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሄደው ከሰው ካቦርት ቁልፍ በመስረቅ የሰውየውን ቤት ከፍተው ሲሰርቁ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡
/ዕድገት በሕብረት/፣ እነዚህ ተማሪዎች ተመክረው መመለስ ባለመቻላቸውና ይባስ ብለው የት/ቤቱን እቃ ግምጃ ቤት በመስበር መፅሃፍት
በመሥረቃቸው ጭምር ለሌሎች መቀጣጫ እንዲሆኑ ለአንድ አመት ከት/ቤት እንዲወገዱ መደረጉን ከርዕሰ መምህሩ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
§ በሌላ በኩል በአፍሪካ አንድነት ቁ.1 ት/ቤት የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው ተማሪዎች የሚመጡት
ከእሪ በከንቱ፣ ከዶሮ ማነቂያ፣ ከጣሊያን ሰፈር፣ ከአሜሪካን ግቢ፣ ከተክለሃይኖትና ከፒያሣ አካባቢ ሲሆን እነዚህ አካባቢዎች ደግሞ
በተለያዩ አዋኪ ሁኒታዎች የታወቁ እንደመሆናቸው ከነዚህ አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎች ያላቸውን ባሕሪይ በቀላሉ መግታት እንደሚያዳግት
ከርዕሰ መምህራን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ ለምሣሌ፡- በዴይ ሆም ፓርቲ ከሚሳተፉ ተማሪዎች አንዷ ከዚህ አካባቢ የወጣችና በዚህ ባሕሪዋ
ከቤተሰብ ጋር ተጣልታ በመለያየቷ ከእህቷ ጋር የምትኖር መሆኗን፣ ሌላኛዋ አክስቷ ቤት የምትኖር ሲሆን አንዷ ደግሞ ፒያሣ ሃገር
ፍቅር አካባቢ በሚገኙ ሴተኛ አዳሪዎች አካባቢ የምትኖር መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ከዴይ ሆም ፓርቲ ተሳታፊ ተማሪዎች መካከል አንዱ አባቱ በኤች.አይ.ቪ. የሞቱበትና እናቱም
ቫይረሱ ያለባት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የአንድ ታዋቂ ግለሰብ ልጅ ሆኖ
ነገር ግን ከአባቱ ጋር ብቻ የሚኖር፣ አባቱም ራሱ ሲጋራና ጫት የሚያዘወትርና የሚጠጣ ባጠቃላይ የቤተሰባቸው ሁኔታ የተበላሸ
መሆኑን የተገኙት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
4.4 አዋኪ ሁኔታዎች
§ በአፍሪካ አንድነት ቁ.1 ት/ቤትና በዕድገት በሕብረት ት/ቤቶች አካባቢ ያሉት አዋኪ ሁኔታዎች ለአልባሌ
ተግባራት የሚገፋፉ መሆናቸውን ተማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ አፍሪካ አንድነት ት/ቤት የሚገኘው ፒያሣ ሲሆን ከአትክልት ተራ በአጥር ይለያል፡፡
ብዙ ዓይነት ገበያተኞች ወንድ፣ ሴት፣ ሽማግሌ፣ ወጣት፣ ክርስቲያን፣ እስላም ወዘተ.. ቀኑን ሙሉ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ስለሚውሉ
በተለይ ሴት ተማሪዎች ወደ ት/ቤት ሲገቡና ሲወጡ ከገበያተኞቹ ከባድ ችግርና የፆታ ግንኙነት ጥያቄ ስለሚቀርብላቸው የተማረሩ መሆኑን
ከተማሪዎች የቡድን ውይይት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በአካባቢው ቡና ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶች፤ ቪዲዮ ቤቶች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም በዚሁ በአፍሪካ አንድነት ቁጥር አንድ ት/ቤት አካባቢ በተለይ ሲኒማ ኢትዮጵያ በመኖሩና በሥራ ሰአት የመግቢያ ዋጋ ወደ
3 ብር በመቀነሱ ብዙ ተማሪዎች ከሙሉ አዲስ አበባ በትምህርት ሰአት በመቅረት ወደዚህ ይመጣሉ፡፡ በተለይ ሐሙስ ሐሙስ አዲስ ፊልም
የሚቀየርበት ቀን በመሆኑ ብዙ ተማሪዎች ወደዚያ ይመጣሉ፡፡ በመሆኑም ሲኒማ ኢትዮጵያ ለተማሪዎች ዋና የመገናኛ ቦታ ሲሆን ከዚያ
በኋላ ወደ ዴይ ሆም ፓርቲዎች ወይም ወደፈለጉበት ቦታ በመሄድ አላስፈላጊ ነገሮችን ሲያደርጉ እንደሚውሉ ከተማሪዎች ቡድን አባላት
የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የዕድገት በሕብረት ት/ቤት አካባቢም ከዚህ
አዋኪ ሁኔታዎች የተለየ አይደለም፡፡ በተለያዩ አዋኪ ነገሮች ማለትም በጫት ሱቆች፣ በቪዲዮ ቤቶች፣ በመኪና ማቆሚያ አካባቢዎችና
በመጠጥ ቤቶች የተከበበ በመሆኑ በተለይ ሴት ተማሪዎችን ለማጥመድና በአልባሌ ተግባራት ውስጥ እንዲዘፈቁ ማድረግ አልፎ አልፎ የሚታዩና
የት/ቤት አመራርና ወላጆች ጣልቃ እስከመግባት የደረሱበት ሁኔታ እንዳለና አርግዘው የወለዱ ተማሪዎች እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዶ/ር
ሐዲስ ከ/2ኛ ደ/ት/ቤት አካባቢም ሲሻ ቤቶች፣ ጫት ቤቶች፣ ከረንቡላና ፑል ቤቶች እንደዚሁም ጠላ ቤቶች መኖራቸው ታውቋል፡፡ በተለይ
እዚህ አካባቢ የሌሊት ዳንስ ቤቶች የሚበዙበትና አካባቢው ‹‹ቺቺኒያ›› በመባል የሚታወቅ ሲሆን ቀን ቀን ተዘግቶ የሚውልና ከምሽቱ
3፡ዐዐ ሰዓት አካባቢ የሚከፈት በመሆኑ ለጊዜው ተማሪዎች ላይ የጐላ ተፅዕኖ እንዳላሳደረ የተጠቆመ ቢሆንም፣ ነገር ግን ከዚህ አካባቢ
የሚኖሩ ተማሪዎች ባሕሪያቸው አካባቢውን ስለሚመስል ሌሎቹን ተማሪዎች ወደ ችግሩ የመሳብ ነገር ውስጥ ውስጡን እንዳለ ሴት ተማሪዎች
ያደረባቸውን ፍራቻ ጠቁመዋል፡፡ አካባቢው ቺቺንያ በመሆኑ ስጋት እንዳለባቸውና ሠላም እንደማይሠማቸው ገልፀዋል፡፡
በከፍተኛ 12 2ኛ ደ/ት/ቤትም ተመሣሣይ ሁኔታ ይታያል፡፡ ከት/ቤት ግቢ ውጪ ጫካ በመሆኑ
ከዚህ በፊት የዚሁ ት/ቤት ተማሪዎች የነበሩ ወንዶች ጋር ግኑኝነት የነበራቸው ሴቶች እንዳሉ በሌሎች ሰዎች ተታልለው ተማሪዎች ከግቢ
ውጪ አልባሌ ቦታ የሚውሉበት ሁኔታ የነበረ ሲሆን እስከ ማርገዝና ማስወረድ የደረሱ ሴት ተማሪዎች እንዳሉ ከርእሰ መምህራንና ከተማሪዎች
ምክር አገልግሎት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከመሃል ከተማ እየመጡ በከ/12 2ኛ ደ/ት/ቤት አካባቢ በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች የጫት
መቃሚያና የአልኮል መጠጦች መሸጫ በመክፈት ችግሮች የመከሰት ምልክቶች እየታዩ መሆኑንም ተማሪዎች ገልፀዋል፡፡
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከቀበሌ 15/16 የት/ጽ/ቤት ኃላፊ ጋር ከተደረገው ቃለ መጠይቅ ለመረዳት
እንደተቻለው የዕድገት በሕብረት ት/ቤት አካባቢ ከአዋኪ ሁኔታዎች የፀዳ ያለመሆኑን፣ ጫት በቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ ቪዲዮ ቤቶች መኖራቸውንና
ጫት ቤቶች የማስቃሚያ ቦታዎች ያሏቸውና በተለይ ከአካባቢ ክልሎች የሚመጡ መለስተኛ አውቶቡሶችና ታክሲዎች ጫት መቃም በሚል ሰበብ
በት/ቤቱ ዙሪያ መኪናቸውን እንደሚያቆሙና ሹፌሮችና ረዳቶቻቸው በተለይ ሴት ተማሪዎች ከት/ቤት ሲወጡ አብረዋቸው እንዲሆኑ እንደሚያማልሉአቸውና
አንዳንዶቹን ይዘዋቸው እንደሚሄዱ አመልክተው የተወሰኑትን ቤቶች በሕግ አግባብ በመጠቀም ለማስቆም ሙከራ ቢያደርጉም አንዳንዶቹ የተማሪዎች
ወላጆች መተዳደሪያ በመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት አለመቻሉን በአፅንኦት አስረድተዋል፡፡ የዶ/ር ሐዲስ 2ኛ ደ/ት/ቤት የቀበሌ ትምህርት
ጽ/ቤት ኃላፊም ተማሪዎች ከሰዓት በኋላ እንደሚቀሩና ምክንያቱም በውል እንደማይታወቅ ነገር ግን አልባሌ ቦታ ይሄዳሉ ተብሎ እንደሚገመት
የት/ቤቱ ተማሪዎች የሆኑ በምሽት በመንገድ ላይ በመቆም የሴተኛ አዳሪ ሥራ ላይ ተሠማርተው እንደተገኙ ጠቁመው ይህ ሁኔታ ምናልባት
በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል በቀበሌ 14/6 22 ማዞሪያ አካባቢ የሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ተማሪዎች ለጫትና ለሀሺሽ
እንዲሁም ለአላስፈላጊ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚጋለጡበት ቦታ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
4.5. እየወተሰዱ ያሉ እርምጃዎች
በየትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎችን ከአልባሌ ተግባራት ለመከላከል ተብለው የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች እየተወሰዱ
ሲሆን ዋና ዋናዎቹ፡-
v ለተማሪዎች የምክር አገልግሎት መስጠት፣
v በሥነ ዜጋና በሥነ ምግባር ክበብ በኩልም ጥረት እየተደረገ መሆኑን፣
v በተማሪዎች የአቻ ለአቻ ትምህርት በመሰጠት ላይ የሚገኝ መሆኑን፣
v በፀረ ኤች.አይ.ቪ.ኤድስ ክበብ በኩል ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን፣
v በተለያዩ ፅሑፎች /ፓንፍሌቶች/ ለማስተማር ጥረት እየተደረገ መሆኑን /ዶ/ር ሐዲስ 2ኛ ደ/ት/ቤት/
በክበባት የተደራጀ የምክር አገልግሎት በመስጠትና
ት/ቤቱ በየ15 ቀኑ ከወላጆች ጋር በመገናኘት ምክክር እንደሚያደርግ ጥዋትም ሆነ ከሰዓት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግንና በምክር
መመለስ ባልቻሉ ተማሪዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰድን የሚያካትት ሥራ እየሰሩ መሆኑን የበዕድገት በሕብረት ት/ቤት/ የገለፀ ሲሆን
በአፍሪካ አንድነት ቁ.1 ት/ቤት ደግሞ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በሥነ ተዋልዶ ጤና ክበብ አማካይነት ትምህርት እንደሚሰጥ የተገኙ
መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ሴት ተማሪዎች ወንድ መምህራንን ማፍቀር እንደሚችሉ እንደመብት የተጠየቀበት ሁኔታ መኖሩን እና
ተማሪዎች እስከ ምን ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ ግንዛቤ የተጨበጠበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ ስለዚህ ት/ቤቱ ከተማሪ ወላጆች ጋር በየጊዜው ስለነዚህ ጉዳይና ሌሎች አሳሳች ሁኔታዎች በማጥናት ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው
ይወያያል፡፡
ü ከአማኑኤል ሆስፒታል ባለሙያ በመጋበዝም ትምህርት እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡
ü የትምህርት ቤቱን ሚኒ ሚዲያ በመጠቀም ያስተምራል፡፡
ü በክበቦች አማካይነት ተከታታይ ትምህርት ይሰጣል፡፡
ü አርፋጅና የሚቀሩ ተማሪዎችን ሰብስቦ ይመክራል፡፡
በከፍተኛ 12 2ኛ ደ/ት/ቤት የተለየ ጥረት ብዙ ባይደረግም፡-
§ በምሣ ሰዓት ተማሪዎች ከት/ቤት ግቢ እንዳይወጡ ጥረት እየተደረገ መሆኑ፣
§
የስም ቁጥጥር ጧትና ምሣ ሰዓት ላይ
የሚደረግ መሆኑን፣
§
በየጊዜው ተማሪዎችን የመምከር ሥራ
እንደሚሠራ፣
§ የተማሪዎች መማክርትና የት/ቤቱ አስተዳደር ከት/ቤት የሚቀሩትንና ተገቢ ያልሆነ ባሕሪይ የሚያሳዩትን
ለመምከር ጥረት እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል፡፡
4.6 የተሰጡ ተጨማሪ አስተያየቶች
በናሙና ከተመረጡት ተማሪዎች፣ ርእሰ መምህራን፣ የተማሪ መማክርት፣ መምህራንና የቀበሌ ት/ጽ/ቤት ኃላፊዎች
ቀጥሎ የተዘረዘሩትን አስተያየቶች ሰንዝረዋል፡፡
§ ተማሪዎች ላይ የፀና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ማስተማር አስፈላጊ ነው፡፡
§
የፀጥታ ሐይሎች /ፖሊሶች/ ሕግን
የማስፈፀም ተግባር ማጠናከር አለባቸው፡፡ ምክንያቱም እስከአሁን የሚወሰደው እርምጃ ልል በመሆኑና ጥፋተኛ የሆኑ ተማሪዎችን እጅ
ከፍንጅ ከያዟቸው በኋላ ምንም እርምጃ ሳይወስዱ የሚለቋቸው መሆኑን ስንመለከት ሕግ የሚያስፈፅሙ አይመስሉም በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
§
የት/ቤት አካባቢ ምቹ መሆን አለበት፡፡
ለምሣሌ፡- ከናዝሬት፣ ከደብረዘይትና ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ሹፌሮች መኪናቸውን /ዕድገት በሕብረት/ በት/ቤቱ ዙሪያ በማቆም ጫት
ይቅማሉ፣ ያጨሳሉ፡፡ ተማሪዎች ከት/ቤት ሲወጡ በተለይ ሴቶችን ጠርተው ይጋብዛሉ፣ በዚያው ያጠምዷቸዋል፡፡ ጫት ቤቶች እንዲዘጉ፣
መኪኖች እንዳይቆሙ ት/ቤቱ ከአዋኪ ሁኔታዎች እንዲፀዳ እስከ ምክትል ከንቲባው አሳውቀን እስከ አሁን መፍትሔ የተገኘ ባለመሆኑ ት/ቢሮውም ግፊት ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
§
በትምህርት ሰዓት ሲኒማ ቤቶች ተማሪዎችን
እንዳያስገቡ ቢደረግ፣
§
ወላጆች በየወሩ የልጆቻቸውን አቴንዳንስ
ት/ቤት ድረስ በመምጣት ቢቆጣጠሩ፣
§
በተለያዩ ክበቦችና ተጨማሪ የትምህርት
ኘሮግራሞች በተማሪዎች ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ቢቻል፣
§
ክበባትን ማጠናከር፣
§
ተተኪ መምህራንን መመደብ፣
§
ነጋዴዎች ተማሪዎች ወደ ት/ቤት ሲገቡና
ሲወጡ እንዳያስቸግሩ አትክልት ተራን ከመሃል ፒያሣ ማንሳት፣
§
ተማሪዎችን የሚጠቅማቸውን በራሣቸው
መወሰን እንዲችሉ የሕይወት ክህሎት ትምህርትን በጥልቀት ማስተማር፣
§
የምክር አገልግሎትን አስፍቶ መጠቀም፣
§
አዋኪ ሁኔታዎችን ከት/ቤቶች አካባቢ
ማራቅ፣
§
አግባብነት ያለው ቅጣት መጠቀም
/አርፍደው ሲመጡ በር ከመዝጋት ት/ቤት ግቢ ውስጥ አስገብቶ መምከር/ ፣
§
ተማሪዎች ሊደመጡ ይገባል፣ ተስፋ
የሚያስቆርጡ ነገሮች መቅረት አለባቸው፡፡ አንተ ደደብ የጫት ሱሰኛ ለውጥ የማይገባህ ተብለው መሰደብ የለባቸውም፣ ተገቢ ክብር ሊሰጣቸው
ይገባል፡፡
§
ጓደኞቻቸውን እንደ ሞዴል ተጠቅሞ
ማስተማር፣
§
የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህራን
በክበብ አማካይነት ተገቢ ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡
§
ተማሪዎችን በፍቅር መቅረብ፣ ማድነቅ፣
§
በት/ቤቱ ያሉ መምህራን በተለይ በከ/12 እና በዶ/ር ሐዲስ 2ኛ ደ/ት/ቤት ሁሉም ወጣቶች
ናቸው፡፡ ስለዚህ በምደባ ወቅት ጥንቃቄ ቢደረግ፣ ማለትም ወጣ ወደሚሉ ት/ቤቶች ወጣቶችን ብቻ የመመደብ እና በመሐል ከተማ ያሉት
ት/ቤቶች ደግሞ ነባር መምህራን መሠባሰባቸው ችግሩን አባብሶታልና ቢስተካከል፡
§
አንዳንድ ጊዜ በእይታ ስህተት በተወሰኑ
ት/ቤቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ የሚዲያ ትችት እየቀረበ ስለሆነ ለወደፊቱ ይህ ቢስተካከል፡፡
§
ት/ቢሮው ደካማ አመራር ባለባቸው
ት/ቤቶች ላይ ክትትል በማድረግ እርምጃ ቢወሰድ የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ክፍል አምስት
5. ማጠቃለያና አስተያየት
5.1 ማጠቃለያ
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተማሪዎችን መማር የሚጐዱ ከት/ቤት ውጭ እና በት/ቤት ውስጥ ያሉትን
አዋኪ ነገሮች በመለየት እና የችግሩን ምንጭ በማወቅ ችግሩ የሚቃለልበትን መፍትሔ መጠቆም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በአዲስ አበባ
ከተማ አስተዳደር ት/ቢሮ አማካይነት ጥናት እንዲካሔድ ተደርጓል፡፡
ጥናቱ ችግሩ ይጐላባቸዋል ተብለው የሚታሠቡትን ከክፍለ ከተማ ት/ጽ/ቤቶች ጋር በመነጋገር የተለዩትን
አራት ት/ቤቶች በመምረጥ (Purposive sampling) ከዚህም ለጥናቱ ይበጃሉ የተባሉትን ማለትም በተለያየ አደረጃጀት ላይ
ያሉ ተማሪዎችን፣ የተማሪዎች ምክር አገልግሎት ባለሙያዎችን፣ ርእሰ መምህራንንና የቀበሌ ት/ጽ/ቤቶች ኃላፊዎችን /ተወካዮችን በጠቅላላው
ድምር 77 ሰዎችን በጥናቱ በማካተትና በቃለ መጠይቅና በቡድን ውይይት አማካይነት መረጃዎችን በማሠባሰብ መረጃው እንዲተነተን ተደርጓል፡፡
በተገኘው መረጃ መሠረት የሚከተሉትን ዋና ዋና የጥናቱ ግኝቶች እንደሚከተለው በማጠቃለል ለማስቀመጥ
ተሞክሯል፡፡
§ የተማሪዎችን መማር ከሚያውኩ ነገሮች አንዱ በራሣቸው በተማሪዎች የሥነ ሥርአት ጉድለት የሚከሠት
ሲሆን በተለይም ከትምህርት ገበታ መቅረት፣ ማርፈድ፣ የት/ቤቱን ሕግ ያለማክበር፣ መምህራኖቻቸውን መዳፈርና የመሣሠሉት ሊጠቀሱ የሚችሉ
የተማሪዎች የሥነ ሥርዓት ጉድለቶች ናቸው፡፡
§
ለተማሪዎች የሥነ ሥርዓት መጓደል
መንስኤ የሚሆኑ በርካታ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን እነዚህም የመማሪያና የመኖሪያ አካባቢዎች ገፅታ፣ ይዘትና ሁኔታ፣ የአቻ ግፊት፣ የቤተሰብ
አቅም፣ አቋም እና ባሕሪ፣ የተማሪዎች የእድሜ ደረጃና ሁሉን የመሞከር ተፈጥሯዊ ክስተት፣ በትምህርታቸው ተስፋ መቁረጥ፣ በት/ቤቶች
ያለው የተማሪዎች አያያዝ ችግርና ክትትል ማነስ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
§
የቤተሰብ ግንዛቤ ማነስና በተለይም
የወላጆችና የታላላቅ እህት እና ወንድሞች ብልሹ ባሕሪያት ማለትም በተለያዩ ሱሶች መጠመድ እንደዚሁም የመኖሪያ እና የት/ቤት አካባቢዎች
ተማሪዎችን ወደ አልባሌ ቦታ እንዲሄዱና አጓጉል ባሕሪያትን
እንዲለምዱ ብሎም ከትምህርታቸው እንዲደናቀፉ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
እንዲለምዱ ብሎም ከትምህርታቸው እንዲደናቀፉ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
§
ተማሪዎች በአፍላ የወጣትነት እድሜያቸው
ላይ እያሉ በጓደኞቻቸው ግፊት በቀላሉ ወደ ችግር እንደሚገቡ በርካታ ጥናቶች ያረጋገጡት ጉዳይ ነው፡፡ በተመሣሣይ ሁኔታ በዚህ ጥናትም
እንደተደረጋገጠው በልዩ ልዩ ሱሶች የተጠመዱ ተማሪዎች ጋር በቅርብ ያሉ ወይም ቅርብብና ጓደኝነት የመሠረቱ ተማሪዎች ችግር ያለባቸው
ተማሪዎችን በመመለስና ከችግራቸው እንዲወጡ በማድረግ ፋንታ ራሣቸው ወደ ችግር የገቡበት ሁኔታ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡
§
በት/ቤቶች አካባቢ ሆነ ብለው የሚያንዣብቡና
በተለይም መኪና በማቆም እና ጫት በመቃም ተማሪዎች ሲወጡና ሲገቡ በተለይ በሴት ተማሪዎች ላይ ፆታዊ ትንኮሣ በማድረግ እና በልዩ
ልዩ ነገሮች /ቁሣዊ/ በማማለልና በማግባባት ተማሪዎችን አልባሌ ቦታ እንዲውሉ፣ ፆታዊ ግንኙነት እንዲፈፅሙና አርግዘው እንዲወልዱ
ወይም/እና እንዲያስወርዱ በማድረግ በተማሪዎች አካል፣አእምሮና ሥነ ልቦና ላይ ችግር እንዲፈጠርባቸውና ከነጭራሹ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ
እያስገደዱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
§
በት/ቤቶች ያለውን ሁኔታ በተመለከተም
በተለይ በመምህራን በኩል የክትትል ማነስ ተገቢነት ያለው ምክር መጓደልና አዎንታዊ በሆነ መንገድ በተማሪዎች ላይ ተፅዕኖ በማሣደር
ከችግራቸው እንዲወጡ ከማድረግ ይልቅ የተማሪዎችን ሞራል በሚነኩ፣ ተስፋ በሚያስቆርጡ አባባሎችና ቃላት በመጠቀም ለምሣሌ፡- አንተ ደደብ፣ ምንም ቢደረግ አይገባህም፣ ወዘተ… በማለት
እና ተገቢውን ክብር ባለመስጠታቸው ተማሪዎች በመጥፎ ባሕሪያቸው የበለጠ እንዲገፉበት እና ት/ቤትን እንዲጠሉ ማድረጉን የተገኘው
መረጃ ይጠቁማል፡፡
§
ከከተማ ወጣ ባሉ ት/ቤቶች አብዛኛዎቹ
መምህራን ወጣቶች በመሆናቸውና ልምድ የሌላቸው በመሆኑ በተማሪዎች አያያዝና ምክር አሠጣጥ ላይ ተፅዕኖ ያሣደረ መሆኑንና በትምህርት
አሠጣጣቸው / አቀራረባቸው ምክንያት ፣ የተወሰነ ተማሪዎች ከት/ቤት እንዲያረፍዱ
እንዲቀሩና አቋርጠው እንዲወጡ ማድረጉንና ትምህርትን እንዲጠሉና ተስፋ እንዲቆርጡ አስተዋጽኦ ማድረጉን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
§
በት/ቤት አካባቢ ወጣቶችን የሚስቡ
እና ‹‹ የሚያዝናኑ ›› ሁኔታዎች ማለትም ፊልምና ሲኒማ ቤቶች በመኖሩ፣
ከረንቡላና ሌሎች መጫወቻ ቦታዎች መበራከት፣ ጫት ቤቶች ሃሽሽና መጠጥ ቤቶች መኖራቸው እንደዚሁም ‹‹ የቀን ጨለማ ቤቶች ››
(Day home party) ብቅ ብቅ እያሉ መምጣታቸው ተማሪዎች በዚያ አካባቢ በመሄድ ከመማር ይልቅ አላስፈላጊ ነገሮች ላይ ተጠምደው
የሚውሉበት ሁኔታ እየተከሠተ ይገኛል፡፡
§
በት/ቤቶች አካባቢ ችግሩን ለማቃለል
እየተወሠደ ያለ እርምጃ መኖሩን ለማረጋገጥ የተቻለ ቢሆንም ችግሩ አሁንም አሣሣቢ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
5.2 አስተያየት
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ት/ቢሮ ባሉ ት/ቤቶች በመማር ማስተማሩ ሒደት የተማሪዎችን መማር ሊያደናቅፉ
የሚችሉ አዋኪ ነገሮች በመለየት ችግሩን ለማቃለል/ለመቀነስ እንዲቻል በተካሔደው ጥናትና በተሰበሰበው መረጃና የመረጃ ትንተና ከተገኘው
ውጤት በመነሣት የዚህ ጥናት ቡድን የሚከተለውን የመፍትሔ ሃሣብ /አስተያየት/ እንደሚከተለው ያቀርባል፡፡
5.2.1 ተማሪዎችን በተመለከተ
§ ወደ አልባሌ ቦታ እና ሱስ አስያዥ ነገሮች እንዲገቡ የሚያደርጉ ማለትም በራሣቸው ሁኔታ ወደ
ችግሩ የመሣብ ውስጣዊ ግፊትንና ውጫዊ የጓደኞቻቸውን የተዛባ አመለካከትና፣ ቅስቀሣና ማማለል እንዲገነዘቡት የማገዝ፣ የመርዳትና
ጉዳቱን የማሣየት ስራ መሥራት ቢቻል፣
§
ከሱስ እንዲርቁና ራሣቸውን የመከላከል/የማዳን
ክህሎት እንዲያዳብሩ ግላዊና ማሕበራዊ መስተጋብራቸው እንዲያድግ የሚያስችል እገዛና የማመቻቸት ሥራ መስራት ቢቻል ፣
§
በፀረ ድራግ ክበብና በተማሪዎች ምክር
አገልግሎት አማካይነት ጫት፣ እደንዛዥ ዕፅና መጠጥ መውሰድ አሁን
ተማሪዎች ባሉበት ደረጃ ተገቢ አለመሆኑን ይህንን መፈፀም በጥፋተኝነት እርምጃ የሚያስወስድ እና ለራሣቸውም ጐጂ መሆኑን
ተከታታይ ትምህርትና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራት፣
§
የአልኮል መጠጦች፣ የሲጋራና አደንዛዥ
እፆችን የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ጉዳቶች ወይም አሉታዊ ውጤቶች የሚያስገነዝቡ ቀጣይነት ያላቸው ተገቢ የማስተማሪያ ፅሑፎችን ማቅረብ፣
§ የተማሪዎችን ግንዛቤ ለማዳበር የሚያስችል የአቻ ለአቻ ትምህርት ዘዴን መጠቀም ለምሣሌ፡- አርአያ ወይም ምሣሌ የሆኑትን ተማሪዎች በማቅረብ፣ የውይይት
መድረክ በማዘጋጀትና ልምድ ያላቸውን ሰዎች በመጋበዝ ትምህርት መስጠት፡
5.2.2 ወላጆችና ሕብረተሰቡን በተመለከተ
§ ወላጆችንና የአካባቢውን ሕብረተሰብ በንቃት በማሣተፍና ከት/ቤቱ ጋር በጋራ እንዲሠሩ በማድረግ
ተማሪዎች በተለይ ከት/ቤት ውጪ ያላቸውን ተጋልጦ ለመቀነስ ጥረት ማድረግ፣
5.2.3
ት/ቤቶችን በተመለከተ
§ የተማሪ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ክትትል እንዲያደርጉና ተገቢውን እገዛ እንዲሠጡ ት/ቤቶች የግንዛቤ
ማስጨበጫ ሥራ መስራት፣
§
መምህራን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የማስተማርና
የመከላከል ሥራ መስራት እንዲችሉ ት/ቤቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለመምህራን መስጠት፣
§
የፀረ ድራግ፣ የተማሪዎች መማክርትና
ሌሎች አደረጃጀቶችን በመፍጠርና ቋሚ ኘሮግራም በማዘጋጀት ቀጣይነት ያለው የማስተማር ሥራ መስራት፣
§
በአካባቢ ያሉ አዋኪ ነገሮችን የጫት
መቃሚያ ቦታዎችን፣ የመጠጥ ቤቶችና የመጫወቻ /ከረንቡላ፣ ፑል ወዘተ…/ ቦታዎችን በመለየትና ከሚመለከተው አካል እና የፀጥታ ሃይል
ጋር በመመካከር ለተማሪዎች አስጊ የማይሆኑበትን መፍትሔ ማፈላለግና አደገኝነታቸው ከተረጋገጠም ሕግን በመጠቀም እንዲዘጉ ወይም እንዲነሱ
ማድረግ፣
5.2.4 መምህራንን በተመለከተ
§ ተማሪዎች ከአደንዛዥ ዕፅና ከአልኮሆል እንዲርቁ የሚያስችል ሥራ መስራት፣ በትምህርት አሠጣጡ
ወቅትም በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትኩረት በመስጠትና በማካተት እንዲያስተምሩ ቢደረግ፣
§
በዚህ ጉዳይ መለስተኛ የጥናትና ምርምር
ሥራ /ተግባራዊ ጥናትና ምርምር/ በማካሄድ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የመፍትሄ ሃሣብ ማፍለቅ ቢችሉ፣
§
በተማሪዎችና በወላጆች እንደዚሁም
በተማሪዎችና በት/ቤቱ አመራር መካከል ድልድይ በመሆን በመግባባትና በመናበብ መስራት ቢችሉ፣
§
ለተማሪዎች ተገቢውን ክብር በመስጠት፣
ቀርቦ በማወያየትና ከችግራቸው እንዲወጡ የምክር አገልግሎት የመስጠት ሥራ ቢሠሩ፣
§
ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጥለው አልባሌ
ቦታ እንዳይውሉ መምህራን የማስተማር ሥራቸውን ጠንክረው በመስራት ለሚሠጡት ትምህርት ተፈላጊ መሆናቸውን የሚያረጋግጥና ተማሪው ትምህርቱን
እንዲወደው ወይም ወደ ትምህርቱ እንዲያዘነብል የሚያደርግ ጥረት ቢያደርጉ ተማሪዎችን ሊገቡበት ከሚችለው ችግር በማትረፍ ውጤታማ፣
በመልካም ሥነ ምግባር የታነፁና ሃገር ተረካቢ ትውለድ ማፍራት ይቻላል፡፡
ማጣቀሻ መጽሐፍት /References /
Alcohol and
Drug Problems, Retrieved from http://www.peacehealth.org
Brandon
& Hill, (2002). Substance use and Violence/Delinquency have significant impacts on Academic
Achievement among Middle and High School Students in Washington State.
Department of Social and Health Services.
Brook
David et.al (1994). The Longitudinal Relationship between Drug use and Risky Sexual
Behaviors among Colombian Adolescents. Department of Community and
Preventive Medicine, Mount Sinai School of Medicine, New York, NY, ETATS-UNITS.
The
Higher Education Center for Alcohol and other Drug Abuse and Violence Prevention
(2010). College Academic Performance and Alcohol and other Drug use.
Impact of Peer Substance Use on
Middle School Performance in Washington: Summary.
Retrieved from hspcnews@u.washington.edu,
Jill
Grove (2002). Protective Factors for Illicit Drug use. The Role of Schools in
crime Prevention.
Karen
Cumberland & Matthew Graham ( ). Working with Schools to Prevent Substance
Abuse: A Scan of Trends and Issues. Canadian Center on Substance Abuse.
Kebede
it.al (2005). Kcat and Alcohol use aned Risky Sex Behavior among in-School &
out-of-School Youth in Ethiopia.
Lo’pez
Garcia KS, and Junior ML. (2008). Antisocial Behavior and Alcohol Consumption
by School Adolescents. Rev. Latino-am Information.
Retrieved from www.eerp.usp.br/rlae
Mesfin
Kassaye (1998). ‘Drug’ use among High School Students in Addis Ababa &
Butajira. Faculty of Medicine, AAU, AA. Ethiopia.
The
National Institute for Drug Abuse (1997). Effective Approaches to Substance Abuse
Prevention. Preventing Drug use among Children and Adolescents: A
Research-Based Guide.
Retrieved from http://www.drugstrategies.org
Tilda
Ferhat et.al (2005). Alcohol use, Kcat, Smoking and Risky Behavior among High
School Boys in Kenya. IUSSP.
United Nations Office on Drugs
and Crime (2002). school-based
education
for drug abuse
prevention. UNITED NATIONS, New York. (200220022002
Yeshigeta
Gelaw & Abraham Haile-Amlak (2003). Khat Chewing and its Socio-demographic
Correlates among the Staff of Jimma University. Retrieved from http://ajol.info/index.php
አባሪዎች
በመማር
ማስተማር ንኡስ የሥራ ሒደት በጥናትና ምርምር ኬዝ ቲም
የተማሪዎችን
የመማር ተግባር በሚያውኩ ሁኔታዎች ላይ
ለሚካሄደው
ጥናት መረጃ ማሰባሰቢያ ቃለ መጠይቅ
1. ለርእሰ መምህራን የተዘጋጀ ቃለ መጠይቅ
1.1
በዲስኘሊን ችግር ምክንያት እርስዎ
ተማሪዎችን አነጋግረው ያውቃሉ ?
1.2
ከቀረቡት ተማሪዎች ወንዶች ወይስ
ሴቶች ይበዛሉ ?
1.3
ችግር አለባቸው ተብለው በት/ቤትዎ
የተለዩት ተማሪዎች የጀርባ ታሪካቸው ምን ይመስላል ?
1.4
የሲጋራ፣ የመጠጥና የሌሎች እፆች
ሱስ ያለባቸው ተማሪዎች አጋጥምዎት ያውቃል ? በዚህ ሱስ የተለከፉ ሴቶች አሉ ?
1.5
በየጊዜው ከት/ቤት የሚቀሩ፣ የሚያረፍዱ
ተማሪዎች አሉ ?
1.6
ወንድና ሴት ተማሪዎች በት/ቤት ውስጥ
ተጣልተው ወይም በአስነዋሪ ተግባር ላይ ተሰማርተው /ለምሣሌ፡- ግብረ
ሥጋ ግንኙነት/ አጋጥምዎት ያውቃል ?
1.7
በት/ቤት ውስጥ በጓደኛ ጫና ወይም
ከት/ቤት ውጪ በሥውር ደላሎች ተማሪዎችን ለአልባሌ ተግባራት የሚያማልሉ ሁኔታዎች ወይም ግለሰቦች /ድርጊቶች አሉ ወይ ?
1.8
በት/ቤትዎ ያሉ ተማሪዎች የተለያዩ
ባአላትን ለማክበር የመዝናኛ ኘሮግራሞች በት/ቤት ውስጥ ያዘጋጃሉ
ወይ ?
1.9
በት/ቤትዎ አቅራቢያ ተማሪዎችን ሊያሳስቱ
የሚችሉ መዝናኛ ቦታዎች፣ ፊልም ቤቶች፣ የቀን ዳንስ ቦታዎች፣ ሥውር ቪዲዮ ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች/ጫት መቃሚያ ቤቶች አሉ ወይ ?
1.10 ተማሪዎች ከነዚህ አሳሳች ሁኔታዎች እንዲጠበቁ ምን እየተሠራ ነው ? ያጋጠመ ችግርስ አለ ወይ
?
1.11 በዚህ ጉዳይ ላይ ያለዎት ተጨማሪ አስተያየት አለ ወይ ?
በመማር
ማስተማር ንኡስ የሥራ ሒደት በጥናትና ምርምር ኬዝ ቲም
የተማሪዎችን
የመማር ተግባር በሚያውኩ ሁኔታዎች ላይ
ለሚካሄደው
ጥናት መረጃ ማሰባሰቢያ ቃለ መጠይቅ
2. ለጋይዳንስና ካውንስል ባለሙያዎች
የተዘጋጁ ቃለ መጠይቆች
2.1
እስከ አሁን እርስዎ ጋር በመቅረብ
የምክር አገልግሎት ያገኙ ተማሪዎች አሉ ወይ ? ወንዶች ወይስ ሴቶች ይበዛሉ ?
2.2
በወንዶችና በሴቶች ተማሪዎች ላይ
በአብዛኛው ምስጢር በሆኑ ችግሮች ላይ የምክር አገልግሎት የሚፈልጉ ተማሪዎች አጋጥምዎት ያውቃል ? ከሆነ ምን ዓይነት ምሥጢራዊ
ጉዳዮች ናቸው ?
2.3
በተለያዩ ሱሶች የተለከፉ ተማሪዎች
አጋጥምዎት ያውቃል ? ምን አይነት ሱሶች ? ለምሣሌ፡- ሲጋራ፣
ጫት፣ ሺሻ፣ ሀሺሽ፣ መጠጥና ወዘተ…
2.4
ሴቶችን ወይም ወንድ ተማሪዎችን የሚያስኮበልሉ
የጓደኛ ጫና ወይም ሌሎች ሁኔታዎች በት/ቤታችሁ ተከስቶ ያውቃል ?
2.5
የተጣሉ ወንድና ሴት ተማሪዎችን አስታርቀው ያውቃሉ ? በምን የተጣሉ ይመስለዎታል ?
2.6
በት/ቤታችሁ አካባቢ ተማሪዎችን ለአልባሌ
ተግባራት የሚያማልሉ ሁኔታዎች/ግለሰቦች አሉ ? ለምሣሌ፡- የቀን
መዝናኛ ቤቶች፣ ዳንስ ቤቶች፣ ቪዲዮ ቤቶች፣ ጫት ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች ፣ መጠጥ ቤቶች ወዘተ…
2.7
ያረገዙ ሴት ተማሪዎችን አማክረው
ያውቃሉ ?
2.8
በት/ቤታችሁ ተገቢ ያልሆነ የመምህራንና
የተማሪዎች ፆታዊ ግንኙነት ተከስቶ ያውቃል ?
2.9
ተማሪዎችን ከአልባሌ ተግባራት ለመጠበቅ
ምን መደረግ አለበት ይላሉ ?
2.10 ተጨማሪ አስተያየት ካለዎት ?
በመማር
ማስተማር ንኡስ የሥራ ሒደት በጥናትና ምርምር ኬዝ ቲም
የተማሪዎችን
የመማር ተግባር በሚያውኩ ሁኔታዎች ላይ
ለሚካሄደው
ጥናት መረጃ ማሰባሰቢያ ቃለ መጠይቅ
3. ለቀበሌ ት/ጽ/ቤት ኃላፊዎች
3.1
በቀበሌያችሁ ውስጥ ባሉ ት/ቤቶች
የተማሪዎች ዲስኘሊን ሁኔታ እንዴት ነው?
3.2
በዚህ በኩል ከት/ቤቶች ጋር ያላችሁ
ግንኙነት ምን ይመስላል ?
3.3
በአልባሌ ተግባራት ለምሣሌ፡- በሲጋራ፣ በጫት፣ በሺሻ ፣ በሀሺሽ፣ በመጠጥ ሱሶች የተለከፉ ተማሪዎች አሉ
ወይ ?
3.4
ተማሪዎች በአልባሌ ተግባራት ላይ
እንዳይውሉ ከት/ቤቶች ጋር ምን እያደረጋችሁ ነው ?
3.5
የተማሪዎችን የመማር ሁኔታ የሚያውኩ
ነገሮች በቀበሌያችሁ በተለይ በት/ቤቶች አካባቢ አሉ ወይ ?
3.6
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ምን መደረግ
አለበት ይላሉ ?
በመማር
ማስተማር ንኡስ የሥራ ሒደት በጥናትና ምርምር ኬዝ ቲም
የተማሪዎችን
የመማር ተግባር በሚያውኩ ሁኔታዎች ላይ ለሚካሄደው
ጥናት
መረጃ ማሰባሰቢያ የቡድን ውይይት ጥያቄዎች
4. ለተማሪዎች መማክርት ወዘተ… የተዘጋጁ
የቡድን ውይይት ጥያቄዎች
4.1
በት/ቤታችሁ ምን ዓይነት የሥነ ሥርዓት
/ የባሕሪይ ችግር ያለባቸው ተማሪዎች አሉ ?
4.2
መንስኤያቸው ውጫዊ ወይስ ውስጣዊ
ሁኔታዎች ናቸው ?
4.3
በጓደኛ ጫና ወደ አልባሌ ተግባራት
ለምሣሌ፡- ለሲጋራ፣ ለጫት፣ ለመጠጥ፣ ለሀሺሽ፣ ለግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚገፋፉ ተማሪዎች
አሉ ?
4.4
በአካባቢያችሁ ለዚህ የሚገፋፉ /
የተገፋፉ ተማሪዎች አሱ ?
4.5
ትምህርት ቤቱ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ
ምን እየሠራ ነው ?
4.6
እንደ ት/ቤት አደረጃጀት አባልነታችሁ
በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሥራ ሠርታችኋል ? ወደፊት ምን ማድረግ ትችላላችሁ ?
4.7
ለወደፊቱ ምን መፍትሔ ትጠቁማላችሁ
?
እ ና መ ሰ ግ ና ለ ን !!!
No comments:
Post a Comment