Thursday, September 13, 2012

እንግሊዝኛ ቋንቋ ለምን የሙጥኝ አለን?


                                            በ ፀጋዬ ሽንብር
እንግሊዝኛ ቋንቋ ለምን የሙጥኝ አለን?
ቋንቋ የሰው ልጅን ባህሪያት ፣ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህልና ሌሎች ከእውነት ጋር ተቆራኝተው የሚገኙ ሁነቶችን ፍንትው አድርጎ የሚያሳየን ተግባቦታዊ መሣሪያ ነው፡፡ ‹‹ለምን?›› ቢባል ዛሬ ላይ የምናያቸው፣ የምንሰማቸው፣ የምንዳስሳቸው፣ የምናነባቸው ማናቸውም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ቴክኖሎጂ ነክ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ ነክ ለሆኑ ውጤቶች  ቋንቋ የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ነው የዘርፉ ምሁራን የሚገልፁት፡፡
በሌላ አገላለጽ ከትውልድ ትውልድ ሲወራረሱ ለመጡ የባህል እሴቶች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የተለያዩ ታሪክ ቀመስ ሂደቶችና ተፈጥሮአዊ ክስተቶች ሁሉ በቋንቋ ይገለጻሉ፡፡ የደረስንበት ዘመንም አጠቃላይ እንድምታ ሊተነተን የሚችለውና እንቆቅልሹ ተፈትቶ መገለጽ የሚችለው በቋንቋ ነው፡፡
የቋንቋ አቅም ይህን ያህል ነው ካልን ሁሉም ቋንቋ ላለበት ህብረተሰብ ምሉዕ መሆኑን ደግሞ መዘንጋት እንደሌለብን የተወሰኑ የቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች በቋንቋቸው ተግባብተው ማህበራዊ ህይወታቸውንና የተግባቦት ጥማታቸውን ማርካት ለመቻላቸው እርግጠኛ መሆን እንችላለን፡፡
ሆኖም ግን ከንግግር ባለፈ ለስነ-ፅሑፍ መሣሪያነት በቅተው የታሪክ ዳራቸው ሲመነዘር የአለማችን በርካታ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ትምህርት፣ ባህል፣ ቴክኖሎጂና ሌሎች መገለጫዎችን ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ሰንቀው በመያዛቸው ለጥቅም ብናውላቸው ፋይዳቸው የጎላ ነው፡፡
በሥነ-ጽሑፍ ቋንቋ መሣሪያነታቸው ለጥናትና ምርምር ተጋላጭ ከሚሆኑት ምሁራን ባለፈ ዓለም አቀፋዊ ትኩረትን ይስባሉ፡፡ በእነዚህ ቋንቋዎች መግባባት የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ያሻቅባል፡፡ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የተናጋሪዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይሄዳል እንደማለት ነው፡፡
የቋንቋው ተናጋሪ ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር ደግሞ ቋንቋው ዘመን ለወለዳቸው ቴክኖሎጂዎች መጠቀሚያነት መመረጡ አይቀሬ ነው፡፡ ይን እውነታ ከተቀበልን ጎን ነጎን ልናስኬደው የሚገባ ሀሣብ መሆኑን ተረድተን ልንፀና ይገባል፡፡ ይህን ሀሳብ በዋቢነት ለመደገፍ  በአለማችን በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋና ብዙ ተናጋሪ አላቸው ከምንላቸው ቋንቋዎች መካከል፡- እንግሊዝኛ፣ ቻይንኛና ስፓኒሽ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ቋንቋዎች መካከል ይበልጥ ተስፋፍቷል፣ ሰርጻóል፣ ተቀባይነትን አግኝቶ፡- እንደ አፍ መፍቻ፣ ሁለተኛ ቋንቋና መማሪያ (የውጭ ቋንቋ) ተወስዶ የሚገኘው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው፡፡ ይህ ቋንቋ በተለይም በ15ኛውና በ16ኛው ክ/ዘመን አካባቢ ከቅኝ ግዛት ጋር በተያያዘ አብሮ የተስፋፋና ያደገ ቋንቋ ሲሆን አሜሪካንም በአፍ መፍቻ ቋንቋነት ልክ እንደ እንግሊዞች ማጎልበት ከመቻሏም ባለፈ ኃያልነቷን በተለያዩ ተግባቦት መስኮች የሚንፀባረቅበት በመሆኑ  ቋንቋው ይበልጥ ናኘ፡፡
በርግጥም የእንግሊዝኛ ቋንቋ በአለማችን ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ካሉ ቋንቋዎች መካከል የመጀመሪያውን ተርታ እንዲይዝ ያደረገው ከምንም በመነሳት አይደለም፡፡ ቋንቋው ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ የትምህርት፣ የንግድ፣ የዲፕሎማሲ፣ የባህል ሽግግር፣ ለአለም አቀፋዊ ተግባቦት መዋሉን እያየን እንገኛለን፡፡
ከዚህ ባለፈ የእንግሊዝኛ ቋንቋን መሠረት በማድረግ ማህበራዊ ክህሎቶችን ለማዳበር፣ በታላላቅ አለም አቀፍ ጉባዔዎች ተሳታፊ በመሆን ሀሳብ ለመቅሰም፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ዜና ምንጮችን (Electronics and print media) በመከታተል፣ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ለመከታተል፣ የሥራ ዕድልና ለመሳሰሉት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ቋንቋውን መሻት ግድ ሆነ፡፡
ይሁን እንጂ ሰው የግድ እንግሊዝኛ ቋንቋን ባለመጠቀሙና ባለማወቁ የመኖር  ህልውናው የተመናመነ ነው ለማለት አይደለም፡፡ መስረጽ ያለበት ሀሳብ ግን ቋንቋው አለምን በተለያዩ ሁነቶችና መገለጫዎች ያካለለ በመሆኑ ልንማረውና ልናውቀው ይገባል የሚል እንደምታ እናስርጽ ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ ዕውቅ የሥነ - ፅሑፍ ሥራዎች (ዘመን ተሻጋሪ) የምንላቸው ተፅፈው የምናገኛቸው በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመሆኑ ይህን ቋንቋ ተምረንና ከምስጢራቱ ተጋርተን የባህላችን እሴቶችን በራሳችን ቋንቋ መግለጽ እንድንችል የሚያስችለን አቅም ያስፈልገናል፡፡


በእኛስ አገር ያለው እውነታ?
በአገራችን ለእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚሰጠው ሥፍራ የቱን ያህል እንደሆነ ለመገመት በየቀኑ ተጋላጭ የሆንባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ ለንባብ የበቁ የስነ-ጽሑፍ ሥራዎችን  በአይነ ህሊና መቃኘቱ በቂ ይሆናል፡፡ ይህን ሀሳብ ይበልጥ ለማጎልበት ዘመን የወለዳቸው (Language of Digital Age) የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑትን ኮምፒውተር፣ ኢንተርኔት፣ ሞባይል፣ ዲጂታል መቅረፀ ድምጽና የመሳሰሉትን በማሰብ ከዚህ ትውልድ ጋር ያለቸውን ቁርኝትና የሚገለጽባቸውን ቋንቋ ማጤን ያለውን እውነታ እንድንረዳ ያደርገናል፡፡
ይህን እውነታ ከተረዳን የእንግሊዘኛ ቋንቋ  በአገራችን በሚገኙ ት/ቤቶች ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለያዩ መንገዶች መጠናከር አለበት ብለን ልናስብ ይገባል፡፡ በት/ቤቶቻችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ በመደበኛውም  ሆነ መደበኛ ባልሆነው አካሄድ ጭምር ይሰጣል፡፡
የእኔ ማጠንጠኛ ሀሳብ ግን መደበኛ በሆኑት 1ኛ ደረጃና 2ኛ ደረጃ የትምህርት እርከኖችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በተጠቀሱት እርከኖች ትምህርቱ እንደ አንድ ትምህርትና ከፍ ሲልም ከአፍ መፍቻ ቋንቋ በስተቀር ሌሎች የትምህርት አይነቶች የተግባቦት መንገዳቸው እንግሊዝኛ ቋንቋ ሲሆን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎቶች በተግባር የዋሉበትና ተማሪዎች ተክነዋቸው ለተግባቦት እንዲያውሏቸው ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ሥርዓተ ትምህርቱን በመጣረዝ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ይሠጥ አይደለም፡፡
ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎቶችን መሣሪያ በማድረግ የተለያዩ መምህራን የሚያስተምሩትን ትምህርት ተከትለው የክፍል ሥራ፣ የቤት ሥራን የሚሰሩትና ፈተናን የሚፈተኑት በዚህ ቋንቋ ነው፡፡ የተማሪዎች የቋንቋ ክህሎት መዳበር በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ፣ ምን ያህል ቋንቋውን ተረድተው ክህሎቶችን መሠረት በማድረግ ምላሽ ሰጥተዋል? ከሚለው መረዳት ይቻላል፡፡
መምህሩ በክፍል ውስጥ እውቀት ለማስረፅ ከተማሪዎች ጋር በሚያካሄደው ተግባቦት  እንቅስቃሴ የተማሪዎች የክህሎት ደረጃ ያለበትን ክትትል የማድረግ ባህል በራሱ ሌላኛው ተማሪዎች ያሉበትን ደረጃ የሚመዝንበት ተከታታይ የምዘና ሂደት ነው፡፡
የመምህሩ በክፍል ዉስጥ የሚያስተምርበት ስነ - ዘዴ  ተማሪን አሳታፊ (active learning and competency based education) የሆነውን መንገድ የተከተለ፣ ተማሪው የእንግሊዘኛ ቋንቋ ክህሎቶችን እንዴት በተግባቦት ያውላቸው፣ ከክፍል ውጭ ከት/ቤቱ ማህበረሰብ ጋር እንዴት ተግባቦት ማድረግ እንዳለበት፡-  የቤት ሥራ ሰጥቼው - ሲመለስ መተግበር አለመተግበሩን ልረዳ፣ በማህበራዊ ህይወቱ ውስጥ ክህሎቶችን ለተግባቦት እንዲያውላቸው እንዴት አመላክቼው እየተገበራቸው መሆኑን ልወቅ የሚሉትና በሕይወት ዘመኑ የእንግሊዘኛ ቋንቋን ከማወቅ ባለፈ ክህሎቶችን በሚገባ ጠንቅቆ ለተግባቦት ማዋል ከቻለ ምንጊዜም ቢሆን በየደረሰበት ተወዳዳሪ (competent) በመሆን የስኬት ባለቤት እንዲሆን ማብቃት ነው፡፡
የክበባት መጠናከር - ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት መዳበር  
በመደበኛው የትምህርት ክ/ጊዜ መምህሩ ምናልባት ዓላማውን ተንተርሶ ማሥረፅ የሚፈልገውን ክህሎት ይበጀኛል ብሎ ያሰበውን ስነ-ዘዴ ተጠቅሞ ሊያስተምር ይችላል፡፡ መምህሩ በክ/ጊዜ ማጠር፣ በተማሪ ቁጥር መብዛት የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ የሁሉንም ተማሪዎች ፍላጎት ሊያሳካና ተሳታፊ የሚሆኑበትን መድረክ አይፈጥር ይሆናል፡፡ የሁሉንም ሥሜት ለመጠበቅ የተለያዩ ሥነ-ዘዴዎችን ተጠቅሞ አላስተማረ ይሆናል፡፡
ከላይ በተገለፁት ምክንያቶችና ሌሎች ያልተገለፁ ሀሳቦች አስገዳጅነት ተማሪዎች የሚጠበቁትን ያህል የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎቶችን ላይሰንቁ ይችላሉ፡፡ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ለትምህርቱ ያላቸው ፍቅር ይቀንሳል፣ ዝንባሌ ያላቸውም ውስጣቸው ይሟሽሻል፤ በሌሎች ትምህርቶች ላይ ሳይቀር ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እየቻሉ ሊዳከሙ ይችላሉ፡፡
እንግዲህ ከላይ ለተጠቀሱት ክፍተቶች ፍቱን የሚሆነው ‹‹የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክበባትን›› በት/ቤቶች ማቋቋም ሲቻል ነው፡፡ ይህን ሂደት ለማሳካት ደግሞ የት/ቤት አስተዳደር፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን፣ ዝንባሌው ያላቸው መምህራንና ተማሪዎች በመሰባሰብ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎታቸውን የተለያዩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ማሳደግ ይችላሉ፡፡
እንደ አብነት መግለጽ ካስፈለገ የንግግር ክህሎታቸውን ለማሳደግ እራሳቸውን እንዲገልፁ፣ ድራማና ሌሎች ተግባቦቶችን እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን በክበቡ አስተባባሪ አማካኝነት ማመቻቸት ይቻላል፡፡ ከሚያደርጓቸው ተግባቦቶች፣ ከሚያደምጧቸው የተቀረጹ ንግግሮች የውይይት ሂደት ሁሉ በማድመጥ ክህሎታቸውን ያዳብራሉ፡፡ ተማሪዎች በክበባቸው ውስጥ ስለሚያስቡትና እንዲያቀርቡ ስለተጠየቁት ርዕስ ጉዳይ በራሳቸው ሃሳብ ጽፈው ያቀርባሉ፡፡ በክበቡ አባላት ሂስ ይሰጥበታል፡፡ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የፅሑፍ ክህሎታቸው የሚዳብርበት መንገድ ተፈጠረ ብንል ያስኬዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲጽፉ የታዘዙትን ሀሳብ አጠናቅረው እንዲያቀርቡ ይበልጥ የሰነቁት ጭብጥ አሳማኝ እንዲሆን ተጨማሪ መጻህፍትን እንዲያነቡ ግፊት ያደርጋል፡፡ የዚህ ነፀብራቅ ምላሹ የንባብ ክህሎታቸውን አብሮ ማየት በመሆኑ ለውጥ በየጊዜው እየታየባቸው ይሄዳል፡፡
የውጭው ተሞክሮም ሆነ በአገራችንም በአንዳንድ የኮሙኒቲ ት/ቤቶች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክበብን በማቋቋም በከፍተኛ ደረጃ የተማሪዎች ቋንቋ ክህሎቶችን በማሳደግና ተነሳሽነታቸው እንዲጨምር ማስቻላቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሱት አይጎልብት እንጂ በከተማችን በሚገኙ ጥቂት 1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶችም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክበባትን በማቋቋም እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም አጠናክረው ባለመያዛቸው ውጤታማነቱ ጎልቶ አልታየም፡፡
በት/ቤቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ መስክ ውጤታማ ትውልድን ለመገንባትና ለማፍራት ክበባት መጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡ ‹‹ለምን?›› ቢባል የእንግሊዘኛ ቋንቋ ክበብ መቋቋም፡- በቋንቋ ዙሪያ በክፍል ውስጥ ያለባቸውን ክፍተት በመለየት ከክበቡ አባላት ጋር በመወያየት መፍትሄ ያፈላልጋሉ፤ ክፍተታቸውን ይሞላሉ፡፡ እርስ በርሳቸው ባለመፈራራትና ባለመተፋፈር ከላይ ለመጠቃቀስ የተሞከሩትን የክህሎቶች ማበልጸጊያ ተግባቦቶችን መፈጸም ያስችላቸዋል፡፡ የልምድ ልውውጥንም ለማድረግ መልካም አጋጣሚን ስለሚፈጥራላቸው የተግባቦት መንገዳቸውን ያሰፋላቸዋል፡፡
የክበቡ አባል በመሆን የተለያዩ አስቂኝ፣ አዝናኝና አስተማሪ ነገሮችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎቶችን መሣሪያ በማድረግ በመማር እየተደሰቱ እውቀት ይገበያሉ፡፡ የቋንቋ ክህሎቶችን ቀስ በቀስ ያዳብራሉ፡፡
በት/ቤት ውስጥ ባሉ የተላያዩ ማህበራዊ፣ ትምህርታዊና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ቋንቋውን በመጠቀም ፅኑ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ በሚኒ - ሚዲያ፣ በት/ቤት በተለያዩ ጊዜያት የሚከበሩ በዓላትን በመንተራስ የራሳቸውን የቋንቋ ፕሮግራሞችን፡- መዝሙርን፣ ግጥምን፣ የተለያዩ ታሪኮችን፣ ቀልዶችን፣ ድራማና መነባንብን በመጠቀም ክህሎቶችን በማውጣት ሊያዳብሩ ይችላሉ፡፡
ከዚህ ውጭ የክበቡ አባላት የተለያዩ ዝግጅቶችን የእንግሊዝኛ ቋንቋን መሣሪያ በማድረግ አዘጋጅተው በዘርፉ ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን በመጋበዝ የህይወት ተሞክሮውን እንዲያጋራቸው ይደረጋል፡፡ ተጋባዥ የዘርፉ እንግዳ  ከተሞክሮው በመነሳት አስተያየትና ምክር የእንግሊዝኛ ቋንቋን ለተግባቦት አውሎ ክህሎቶችን እንዴት ማዳበር እንዳለባቸው ይገልጽላቸዋል፡፡ ከተሰጣቸው ገለፃ በመነሳት በቀጣይ ተጠናክረው እንዲቀርቡና በህብረተሰቡ፣ በአገሪቱ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ መሆን ያስችላቸዋል፡፡
ተሞክሮዎቻቸው አርአያነታቸውን ስለሚያንፀባርቅ በት/ቤቱ የሚገኙ ሌሎች ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ለተመሳሳይ ዓላማ ይነሳሳሉ፡፡ ከሌሎች ት/ቤቶች ጋር ትስስር በመፍጠር የእንግሊዝኛ ቋንቋን ክበብ በማቋቋም የተገኘውን  ለውጥ በማስረዳት ተሞክሮዎቻቸው እንዲሰፋ የሚደረግበት አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች መሠረት በማድረግ በት/ቤቶቻችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክበባት መቋቋም፣ መጎልበትና መስፋፋት መምህሩን ከማገዝ ባለፈ በዘርፉ ውጤታማ ትውልድን ለመፍጠር ልንጠቀምበት የሚገባ አይነተኛ ሥልት ነው!    

No comments:

Post a Comment