Saturday, August 11, 2012


ምዕራፍ አንድ፡- መግቢያ
1.1.የጥናቱ ዳራ
ከ1940 እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ ባሉት ዓመታት ማንበብን በሚመለከት የተለያዩ የንባብ ንድፈ ሐሳቦች ተቀርፀዋል፡፡ ንድፈ ሐሳቦቹ አንባቢያን በተፈጥሮ ባሕሪ፣ በአካባቢ፣ በመኖሪያ ቤትና በትምህርት ቤት ተፅዕኖ ምክንያት የማንበብ ልምዳቸው እንዴት ሊጎለብት እንደሚችል የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ለዚህ በምሳሌነት የሚጠቀሱት የንባብ ንድፈ ሐሳብ ዕይታዎች አቅመ ንባባዊ (Maturational)፣ ተፈጥሯዊ (Nativist)፣ እድገታዊ (developmental)፣ መገናኛዊ (Connectionist)፣ የስነ ልቦናዊ ስነልሳናዊ (Psycholingustics)፣ ውልደታዊ (Emergent)፣ የማሕበረ-ባሕላዊና (Socio-cultural)፣ የማሕበራዊ ዕውቀት ግንባታ (social constructivist) ናቸው (ብላክ 2006)፡፡
በመጀመሪያ ከ1940 እስከ 1960ዎቹ ባሉት ዓመታት የአቅመ ንባብ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡ ብላክ (2006) እንዳመለከቱት የንድፈ ሐሳቡ ዕይታ ትኩረት ወጣት ተማሪዎችን መደበኛ ንባብ ማስተማር ከመጀመር  በፊት የንባብን ዕውቀት የሚረዱበት የአቅም ደረጃ ላይ መድረስ አለባቸው የሚል ነው፡፡ ተማሪዎች በንባብ ትምህርት ዕውቀትና ክሂል ከማዳበራቸው በፊት በቅድመ ትምህርት ቤት ደረጃ የተወሰነ የንባብ ፅንሰ ሐሳብን ቀድመው ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ለማንበብ ዝግጁ የሆኑት ተማሪዎች መደበኛ የንባብ ትምህርት በሚማሩበት ወቅት ለትምህርቱ እንግዳ አይሆኑም፡፡ ለንባብ ትምህርት ዝግጁነት የሌላቸውን ተማሪዎች ማስተማር ደግሞ አዕምሯዊ ጉዳት ያመጣባቸዋል ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ገሰል (1965) የተባሉት ተመራማሪ የዚህ ንድፈ ሐሳብ ተከታይ ነበሩ፡፡
በመቀጠል ከ1950 እስከ 1980ዎቹ ታዋቂነት አግኝቶ የነበረው ተፈጥሯዊ የንባብ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ነበር፡፡ ብላክ (2006) እንደገለፁት የንድፈ ሐሳቡ አፍላቂዎች (ቾሞስኪ 1957፣ እና ፍሮብል 1897) ናቸው፡፡ ተመራማሪዎቹ እንደሚያምኑት የሰው ልጆች ቋንቋን ለመልመድ ይዘውት የሚወለዱት መሳሪያ እንዳላቸው ሁሉ ንባብን የሚማሩ ተማሪዎችም ልምዳቸውን ለማዳበር የማያቋርጡና የተጠራቀሙ ደረጃዎችን ማለፍ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ተማሪዎች የማሕበራዊና ባሕላዊ ቋንቋቸውን ተፈጥሯዊ መርሐ ግብር ቋንቋን ለመልመድ ይጠቀሙበታል፡፡
የተፈጥሯዊ ንባብ ንድፈ ሐሳብን ተከትሎ የዕድገታዊ ንባብ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ዝነኛ ሆኖ የነገሰው ከ1960 እስከ 1980ዎቹ ባሉት ዓመታት ነበር፡፡ በወቅቱም የንድፈ ሐሳቡ አፍላቂዎች ዕይታ ያተኩር የነበረው በአካባቢ ቅድመ ንባብ ተግባራት ላይ ነበር፡፡ በሽልማትና በቅጣት ተማሪዎች ከስሕተታቸው እንዲማሩ በማድረግ ለንባብ ዝግጁ እንዲሆኑ ባህሪያቸውና ልምዶቻው ይቀረፁ ነበር፡፡ የተማሪዎቹ የንባብ ዝግጁነት የሚመሰረተው በአወንታዊና አሉታዊ ልምዶቻቸው ላይ ነበር፡፡ በዚህ ንድፈ ሐሳብ ተማሪዎች ንባብን አዘውትረው ከተማሩ የማንበብ ፍላጎታቸው ይጨምራል ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ቶርንዳይክ (1971) እና ስኪነር፣ ዌልቦርንና ኮኒል (1990) የንድፈ ሐሳቡ ተከታዮች ናቸው (ብላክ 2006)፡፡
እንዲሁም ከ1960 እስከ 1980 ባሉት ዓመታት የንግግር ድምፆችን መሠረት በማድረግ የመገናኛዊ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ገኖ ነበር፡፡ በወቅቱ መምህራን በመማሪያ ክፍል ውስጥ የህትመት ውጤቶችን በማቅረብ የንባብ ትምህርትን ለማነሳሳት ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ የመገናኛዊ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ንባብን ተግባር ላይ ያውሉት የነበረው በታሕታይ-ላዕላይ   ሞዴል ነበር፡፡ በዚህም በፊደልና በድምፆች አማካኝነት የቃላትን ትርጉም በቀጥታ በማስተማር በተግባር ላይ ይውላል፡፡ ተማሪዎቹ በትንሹ ጀምረው ንባብ ይማሩና ቀስ በቀስ በሰፊው እንዲያነቡ ሰፋፊ ፅሁፎች ይቀርቡላቸዋል፡፡ አንባቢዎቹ ኮዱን ከንባቡ ጋር እያገናኙ አንድ ጊዜ ከተማሩት  እያንዳንዱን ቃል ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት ማንበብ ይችላሉ፡፡ የዚህ ንድፈ ሐሳብ ተከታዮች ፍለስች (1955) እና አዳምስ (1990) ናቸው በማለት ብላክ (2006) ያስረዳሉ፡፡ 
ከዚያም የስነ ልቦናዊ ስነልሳን ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ከ1980 እስከ 1990ዎቹ በነበሩት ዓመታት ተቀባይነት ያገኘ ንድፈ ሐሳብ ነበር፡፡ ብላክ (2006) እንዳብራሩት  እንደዚህ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ተማሪዎች ንባብን በመማር ሒደት በንቃት ስለሚሳተፉ አንብቦ ለመረዳት አይቸገሩም፡፡ ምክንያቱም ንባቡን የሚማሩት በማህበራዊና ባሕላዊ ቋንቋቸው በመጠቀም ነበር፡፡ የንባብ ተግባራት የዕውነተኛና የተጨባጭ ችግር መፍቻ ተደርገው ይታሰቡ ነበር፡፡ ተማሪ ተኮር የሆነው የንባብ ትምሕርት የመማር ተግባራቱና የሚቀርበው ፅሁፍ በዕውነተኛ ሕይወት ላይ ማትኮራቸው ተማሪዎች ለንባባቸው ትርጉም እንዲሰጡት አድርጓል፡፡ በዚህ ንድፈ ሐሳብ ንባብን ለማስተማር ላዕላይ- ታሕታይ ዘዴ ትኩረት ይሰጠው ነበር፡፡ የንድፈ ሐሳቡ ዋነኛ ተከታይ ጉድማን (1968) ናቸው፡፡
የውልደታዊ ንባብ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ታዋቂነትን ያገኘው ከ1980 አስከ 1990 ባሉት ዓመታት ነበር፡፡ እንደ ብላክ (2006) አገላለፅ በዚህ ንድፈ ሐሳብ የፊደልና የንባብ ክህሎት ፅንሰ ሐሳብ የሚጀመረው ከውልደት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን ተማሪዎች በዕውነተኛ ሕይወት የንባብ ተግባራት ላይ ከተሳተፉ እስከ ጎልማሳነት ዕድሜያቸው ድረስ ይዘልቃል የሚል እምነት አለ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት የመጡት ሕፃናት ስለ ንባብ ያላቸው ግንዛቤ የተለያየ ነው፡፡ ይህም ከማንበብ ዝግጁነታቸው ጋር ይያያዛል፡፡ ፒያጄት (1952) እና ክሌይ (1952) የንድፈ ሐሳቡ ዕይታ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው፡፡
ብላክ (2006) እንዳመለከቱት ቆየት ብሎ በ1990ዎቹ አገልግሎት ላይ የዋለው የንባብ ንድፈ ሐሳብ  የማህበራዊ ዕውቀት ግንባታ ንድፈ ሐሳብ ዕይታ ነው፡፡ ንድፈ ሐሳቡ የሚያተኩረው የንባብ ዕድገት የማያቋርጥ ሒደት መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከውልደት ጀምሮ በተለያየ መጠን እያደገ በመሄድ እስከ ሕይወት መጨረሻ ይዘልቃል፡፡ ይህ የሚከናወነው ከሌሎች ቋንቋ ተጠቃሚዎች ጋር ንቁ ተራክቦ በማድረግ ነው፡፡ ተማሪዎች አዳዲስ የንባብ ክሂሎችን የሚለምዱት ሆን ብለውና ሳያስቡት ሊሆን ይችላል፡፡ የንባብ ተግባርና ሚናቸውን የሚወጡትም ከቤተሰቦቻቸው፣ ከማህበረሰቡ ባህላዊና ማህበራዊ አካባቢዎች ነው፡፡ ቪጎትስኪ (1978) በዚህ ንድፈ ሐሳብ ተከታይነታቸው ይታወቃሉ፡፡
በመጨረሻም የማሕበረ-ባሕል የንባብ ንድፈ ሐሳብ ከ1990ዎቹ ቀደም ብሎ እስከ አሁንም ድረስ ተቀባይነት ማግኘቱን አላቋረጠም፡፡ የንድፈ ሐሳቡ የዕይታ ትኩረት እንደሚያመለክተው የተማሪዎች የቋንቋ ባለቤትነት ልምድ በመኖሪያ ቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በባሕልና በማህበረሰብ አካባቢ እኩል አይደለም፡፡ እያንዳዱ ማሕበራዊና ባሕላዊ አውድ የራሱ የሆኑ ልዩ ልዩ ልምዶችና የንባብ ባሕሎች አሉት፡፡ ተማሪዎችም በቤተሰባቸው ታሪኮችና ባህላዊ ልምዶች አስተሳሰብ ስለሚቀረፁ በመማሪያ ክፍል ተግባራቶች ላይ  ይህንኑ ያንፀባርቃሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ንባብ በሚማሩበት ወቅት ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በዚህ ንድፈ ሀሳብ አመንጭነታቸውና ተከታይነታቸው የሚታወቁት ቦርዲዩ (1997)፣ ፍሪቦዲና ሉኪ (1990) እና ፍሪሪ (1973) ናቸው በማለት ብላክ (2006) አስረድተዋል፡፡
ከላይ በዝርዘር ከተጠቀሱት ንድፈ ሀሳቦች በተጨማሪ አመለካከት በተማሪዎች የንባብ ትምህርትም ሆነ ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ አመለካከት በልምድ አማካኝነት የተደራጀ መልስ የመስጠት ዝግጁነት ነው (ኢሰር 1994)፡፡ በሰዎች ባህሪ ላይ ተለዋዋጭ ተፅዕኖን የማሳደር አዕምሯዊና ስሜታዊ ስርዓትም ነው (ሊንዲዝና አሮንሰን 1996)፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚማሩት፣ አብሯቸው የሚቆይ፣ በነገሮች፣ በአስተሳሰቦች፣ በሁኔታዎች ወይም በሰዎች ላይ የሚታይ አወንታዊ ወይም አሉታዊ ግምገማ ነው (ስኪነር 1989)፡፡ ስሜታዊ ይዘት፣ ጠቃሚ ዕምነቶች፣ ቅድመ ጥላቻዎች፣ ወደ አንድ ጎን የማድላት ዝንባሌ፣ አድናቆቶችና ሌሎችም የአመለካከት ምንነት የሚገለፅባቸው ናቸው (ፊልድማን 1996)፡፡ ከማንበብ ጋር በተያያዘ የማንበብ አመለካከት ማለት ንባብን የመውደድና የመጥላት ስርዓታዊ ስሜት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ አንባቢ ሳይንሳዊ ልቦለድን ማንበብ ሲወድ፣ ሌላው አንባቢ የፍቅር ልቦለድ ማንበብ ሊወድ ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አንድ ሰው በተለያዩ ሁኔታዎች ማንበብን እንዲጠላ ወይም እንዲወድ ስለሚደረግ ነው (ፍለድና ላፕ 1983፣ ማክኪና ኪአርና  ኢልስዎርዝ 1995)፡፡
ፊልድማን (1996) እንደሚያስረዱት አመለካከት ስሜታዊ፣ ባህሪያዊና አዕምሯዊ የሚባሉ ሶስት ክፍሎች አሉት፡፡ ስሜታዊ ክፍል  የሚይዘው አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ስሜቶች በአንድ ነገር ላይ እንዴት እንደሚፈጠሩ የሚታወቅበትን ክፍል ነው፡፡ ባህሪያዊ ክፍል አመለካከት ጠቃሚ የሆነ የተለዬ ተግባር ለማከናወን በሰዎች ውስጥ ያለን ቅድመ ጥላቻ ወይም ዕቅድ ይመለከታል፡፡ አዕምሯዊ የሚባለው ክፍል ደግሞ የሚያካትተው ሰዎች አመለካከታቸውን ፣ ዕምነታቸውን  ወይም ሀሳባቸውን ዕውን አድርገው የሚይዙበትን ነው፡፡ የዝምድናቸው መጠን ከፍና ዝቅ ይል እንደሆን እንጅ ማንኛውም አመለካከት በነዚህ ሶስት ክፍሎች ቅንጅት የሚካሄድ ነው፡፡ ቫካ እና ቫካ (1999) የማንበብ አመለካከትን ከስሜታዊ፣ ከባህሪያዊና ከአዕምሯዊ ክፍሎች ጋር ያለውን ጥምረት እንዳመለከቱት የማንበብ አመለካከት ሦስት መሰረታዊ ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ክፍል አንባቢዎች ስለማንበብ ያሏቸው ግምገማዎች ወይም ስሜቶች ስሜታዊ የማንበብ ክፍል ነው፡፡ ሁለተኛው ክፍል አንባቢዎቹ አንድን ንባብ ለማንበብ ሲያስቡና ንባብን በተግባር ሲያውሉት የማንበብ አመለካከታቸውን ባህሪያዊነት ይገለፃል፡፡  በሶስተኛው አዕምሯዊ ክፍል የሚከናወኑት ደግሞ አንባቢያን ስለማንበብ ያላቸው አስተያየቶች  ወይም ስሜቶች ናቸው፡፡
ፊልድማን (1999) እንደገለፁት አመለካከትን ለመበየን የሚያገለግሉ ሶስት ዓይነት ንድፈ ሐሳቦች አሉ፡፡ ከእነሱም መካከል ተግባራዊ ንድፈ ሀሳብ የመጀመሪያው ነው፡፡ የተግባራዊ ንድፈ ሐሳብ አመንጭዎች እንደሚያምኑት አመለካከቶችን መማር የሚቻለው ፍላጎቶችን ለማርካት ሲባል ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ  አዕምሯዊ ንድፈ ሀሳብን ያፈለቁት እንደሚያብራሩት ደግሞ የአመለካከቶች መሰረት መረጃ ነው፡፡ ከዚህ  አመለካከታቸው የተነሳም  አላማቸውን የሚቀርፁት ከልምዳቸው፣ ከሌላ አካልና ከውሳኔ በመነሳት ነው፡፡ በሶስተኛነት ንድፈ ሀሳብን ያፈለቁት የባህሪያዊያን ንድፈ ሀሳብ ባለቤቶች እንደሚሉት በአንድ ወቅት ክስተት በተፈጠረ የጥሩ ወይም የመጥፎ ስሜት አጋጣሚያዊ ክስተትን ከሌሎች በመመልከት አመለካከት ይቀረፃል፡፡ ለምሳሌ ከቤተሰብና ከብዙሐን መገናኛ ሊሆን ይችላል፡፡
አመለካከት የሚበየንባቸውን ንድፈ ሐሳቦች መሰረት አድርገው አመለካከትና ማንበብ ያላቸውን ዝምድና የሚያረጋግጡ ሶስት የንድፈ ሀሳብ ሞዴሎችን ተመራማሪዎች ቀርፀዋል፡፡ ሞዴሎቹ የማዚውሶን፣ የሩድል ስፒከርና የማኬና ሲሆኑ፣ እነሱም በተለይ በማንበብ ሂደት ወቅት አመለካከት ከአንባቢያን ስሜት ጋር ያለውን ዝምድና ይገልፃሉ፡፡ የማዚውሶን ሞዴል (1985) የሚያካትታቸው የአመለካከት ስሜታዊ ሂደቶች ፍላጎት፣ ዕሳቤና አካላዊ ስሜቶች ናቸው፡፡ ሩድልና ስፒከር በማዚውሰን ሞዴል ላይ የቃላት ግንዛቤ በሚል በሞዴላቸው ላይ ንዑስ ሂደት በማካተት  ለማሻሻል ሞክረዋል፡፡ የሁለቱን ንድፈ ሀሳባዊ ሞዴሎች (የማዚውሶንና የሩድል ስፒከር ሞዴሎች) ያሉባቸውን ችግሮች በመመርመር (ማኬና 1994) የተባሉት ተመራማሪ አዲስ የማንበብ አመለካከት ንድፈ ሐሳባዊ ሞዴል ይዘው ብቅ ብለዋል (ስችማይት 2009)፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የሶስቱ ንድፈ ሀሳባዊ ሞዴሎች ባለቤቶች የማንበብ አመለካከት እንዴትና ለምን እንደሚፈጠር በጥናታቸው ግኝት አብራርተዋል፡፡ ማዚውሶን (1994) እንዳመለከቱት አንባቢያንን ለማንበብ እንዲወስኑ የሚያደርጓቸው ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ውጫዊ  አነሳሾችና ውስጣዊ ግለሰባዊ ስሜቶች ናቸው፡፡ እነዚህም የሚያካትቱት የይዘትና የአላማ ግምገማ፣ የተለየና አዲስ አይነት ንባብ የማንበብ ፍላጎት እንዲሁም የንባብ ተግባርን ለማከናወን መነሳሳት ናቸው በማለት ተመራማሪው ጠቅሰዋቸዋል፡፡ የሩድል ስፒከር (1995) ሞዴል  አራት ተራክቧዊ ክፍሎች አሉት፡፡ እነሱም የአንባቢው አካባቢ፣ የዕውቀት አጠቃቀምና ቁጥጥር፣ ሥርዓታዊ ዕውቀትና የአንባቢው ውጤት ናቸው፡፡ የአንባቢው አካባቢ ለንባብ የቀረበውን ፅሁፍ፣ ውይይቶችንና የማስተማር ገፅታዎችን ያካትታል፡፡ እነዚህ የተራክቦ ክፍሎች በመረጃውና በሥርዓቱ ሒደቶች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ከፍተኛ ፍላጎት የሚቀሰቅስ ፅሁፍ ዝቅተኛ ፍላጎት ከሚያነሳሳ ፅሁፍ ጋር ሲወዳደር የሚያሳድረው የማንበብ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ የማክኪና (1994) ሞዴል ንድፈ ሀሳብ ለአመለካከት ለውጥ ዋና ዋና የሚባሉት ሶስት ምክንያቶች ፡- (1) አንባቢዎች ስለንባብ ውጤቱ ያላቸው ዕምነቶች፤ (2) ከንባቡ የሚጠብቁት እምነት ፍላጎታቸውን ለማነቃቃት ያለው ስምምነትና፤ (3) ከንባብ አጋጣሚዎቻቸው የተለየ ውጤት መጠበቃቸው በማለት ይዘረዝራሉ፡፡
አመለካከት ለምንና እንዴት እንደሚፈጠር ተመራማሪዎች የደረሱበትን ውጤት ተመርኩዘው አወንታዊ የማንበብ አመለካከት በወላጆችና በመኖሪያ ቤት አካባቢ፣ በመማሪያ ክፍል ውስጥ፣ በተማሪዎች  አመለካከቶችና ባሕሪ፣ እንዲሁም በመምህራን አማካኝነት እንዴት ማሳደግና ማጠናከር እንደሚቻል አስተያየት ያላቸው ተመራማሪዎች አሉ፡፡ ሁሉም እንደሚስማሙበት የማንበብ አመለካከት እያደገና እየተጠናከረ መሄድ የሚጀምረው በአብዛኛው በወላጆች አማካኝነት ነው (ስፒገል 1994፣ አሌክሳንደርና ፊለር 1976፣ ክላመር 1994፣ ማክኬና ኪአርና  ኤልስዎሪዝ 1995፣ ራስንስኪና ፓዳክ 2000)፡፡
ስፒገል (1994) እንዲሚያስረዱት ወላጆች ለልጆቻቸው የማንበብ አመለካከት አወንታዊ መሆንና የንባብ ስኬታማነት ዋነኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ወላጆች ከሚጫወቷቸው ሁለት ሚናዎች መካከል አንደኛው በመኖሪያ ቤት አካባቢ የሕትመት ውጤቶችን ለልጆቻቸው በማቅረብ የልጆችን የማንበብ ፍላጎት ማነሳሳት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ መፃሕፍትን በመኖሪያ ቤት እያነበቡላቸው መልካም አርአያ መሆን ናቸው፡፡ አሌክሳንደርና ፊለር (1976) እንደሚገልፁት የወላጆችና የመኖሪያ ቤት አካባቢ ለማንበብ አመለካከት ጠቃሚ አስተዋፅኦ ማበርከቱ አወንታዊ አመለካከትን በማጠናከር ከትምህርት ቤቶች ጋር በቅርበት ለመስራት ጠቃሚ ነው፡፡ ወላጆች የልጆቻቸውን የማንበብ አመለካከት እንዴት መለወጥ እንደሚቻል ዕውቀቱ ከሌላቸው በመምህራኑ አጋዥነት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ 
ከወላጆች በተጨማሪ የመማሪያ ክፍል አካባቢ በወጉ መደራጀቱ ለተማሪዎች የማንበብ አመለካከት በጎነት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ አለ (ክራመር 1994፣ አሌክሳንደርና ፊለር 1976)፡፡ አወንታዊ የማንበብ አመለካከት መፍጠሪያ አንዱ መንገድ የንባብ ቁሳቁስን በብዛት በመምረጥ በክፍል ውስጥ ማስቀመጥ ነው፡፡ መምህራኑ በውሰት መፃህፍትም ቢሆን እንኳ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ቤተ-መፃህፍት ለመክፈት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ በመማሪያ ክፍል ቤተ-መፃህፍቱ ተማሪዎቹ የንባብ ናሙናዎችን በማንበብ ፍላጎታቸው ሊነሳሳ ይችላል፡፡ ይሁን እንጅ በቤተ-መፃህፍቱ ለተማሪዎቹ የሚቀርቡት መፃህፍት በፍላጎታቸው መሰረት መሆኑ ግምት ውስጥ ካልገባ ተማሪዎቹ አወንታዊ የማንበብ አመለካከትን አያዳብሩም፡፡ ይህ እንዳይሆን መምህራን ከመማሪያ መፃህፍቱ በተጨማሪ እያዝናኑ የሚያስተምሩ መፃህፍት፣ መፅሔትና ጋዜጦች በቤተ-መፃህፍት ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡
በሌላም በኩል የተማሪዎች አመለካከቶችና ባህሪ የማንበብ አመለካከት አወንታዊ እንዲሆን ምክንያት ይሆናል (ማክኪና፣ኪአርና ኤልስዋርዝ 1995፣ አሌክሳንደርና ፊለር 1976፣ አስኮቨና ፊስችባች 1973)፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የመማሪያ ክፍሎች በመዝናኛ ንባብ ተማሪዎችን ማስተማር በትምህርታቸው ላይ አሉታዊ አመለካከት ያሳድራል የሚለው ንድፈ ሐሳብ ጫና በማሳደሩ ክሂሉ ያላቸው አንባቢዎች ለአሉታዊ ተፅዕኖ ተጋልጠዋል፡፡ በተመሳሳይ በጠንካራና ደካማ አንባቢያን መካከል ያለው ክፍተትም ያሳደረው ተፅዕኖ አለ (ማክኪና፣ኪአርና ኢልስዋርዝ 1995)፡፡ ክፍተቱን ለማጥበብ በዝቅተኛ የክፍል ደረጃዎች ለሚማሩ ተማሪዎችም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ልምዱን መሰረት በማድረግ መምህራን ጎበዝ ተማሪዎችን ከደካማ ተማሪዎች ጋር እያነፃፀሩ የማንበብ አመካከታቸውን መገመት የለባቸውም (አሌክሳንደርና ፊለር 1976)፡፡
በአጠቃላይ ከንድፈ ሐሳቦቹ ለመረዳት እንደሚቻለው የንባብ ንድፈ ሐሳቦቹ ዕይታዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ እንደ ንድፈ ሐሳቦቹ ተከታዮች ዕምነት በተፈጥሮና በአካባቢ ተፅዕኖዎች ምክንያት የማንበብ ልምድ እየዳበረ ይሄዳል፡፡ በነዚህ ብቻ ሳይሆን በአንባቢዎች አመለካከትም በሚደርስ ተፅዕኖ ንባብን የመውደድና የመጥላት ስሜት ሊፈጠር ይችላል፡፡ የማንበብ አመለካከት በልምድ ወይም በመማር ምክንያት  ሰዎች ለአንድ ነገር የሚኖራቸው  አወንታዊ ወይም አሉታዊ አመለካከት ሲሆን፣ ስሜታዊ፣ ባሕሪያዊና አዕምሯዊ ክፍሎችንም ይይዛል፡፡ በተጨማሪም አንባቢዎች ለአንድ ንባብ የሚኖራቸው የመውደድና የመጥላት ሥርዓታዊ ስሜት ነው፡፡ ይህም በተማሪዎች ባህሪ፣ በወላጆች፣ በመምህራን፣ በቤተሰብና በአካባቢ ተፅዕኖዎች ምክንያት እየጎለበተ ይሄዳል፡፡ ይሁን እንጅ የሚካሄደው ጥናት  አመለካከትና ማንበብ ያላቸውን ዝምድና ከሚያረጋግጡት ሶስት የንድፈ ሐሳብ ሞዴሎች መካከል በአሁኑ ዘመን ተቀባይነት ያገኘውን የማኬና (1994) ሞዴል ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ሞዴሉ መሠረት የሚያደርገው አንባቢዎች ስለንባብ ውጤቱ ያላቸውን ዕምነቶች፣ ከንባቡ የሚጠብቁት እምነት ፍላጎታቸውን ለማነሳሳትት ያለውን ስምምነትና ከንባብ አጋጣሚዎቻቸው የተለየ ውጤት መጠበቃቸውን ነው፡፡ የዚህም ጥናት ትኩረት በባሕር ዳር ከተማ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ10ኛ ክፍል ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለውን ተዛምዶ መመርመር ነው፡፡
  1.2.የጥናቱ መነሻ ችግር
በማንበብ አመለካከት ላይ በማተኮር ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች እንደሚገልፁት የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት አወንታዊና አሉታዊ በማድረግ ተፅዕኖ የሚያደርሱ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ እነሱም የመኖሪያ አካባቢ፣ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤትና ፆታ ናቸው (ብላክቢ 2006)፡፡ ከተመራማሪዎቹ መካከል ዱቢንና ዞርካኢያ (2010) እንዲሁም ሊን (2010) የመኖሪያ አካባቢዎች በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ያመጣሉ በሚለው ሐሳብ ተቃራኒ አስተያት አላቸው፡፡ ዱቢንና ዞርካኢያ (2010) ባደረጉት ምርምር በአንድ አካባቢ ለማንበብ ምቹ ሁኔታዎች ካልተሟሉ በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ተመራማሪዎቹ በጥናት ውጤታቸው እንዳመለከቱት አንባቢዎች ለመፃሕፍት መግዣ የሚሆን ገንዘብ በማጣታቸው በብዛት የቴሌቭዥን ስርጭት ስለሚከታተሉ በማንበብ አመለካከታቸው ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የመፅሔት አንባቢዎች ቁጥራቸው ቀንሷል፣ መፃሕፍትን በመደበኛነት የሚያነቡ ጥቂት ሆነው ተገኝተዋል፣ አማካይ የመፃሕፍት የቅጅ መጠን 6% በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሊን (2010) ባካሄዱት ጥናት  በገጠር ወይም በከተማ መኖር በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ እንዳለውና እንደሌለው በማተኮር ጥናት አድርገዋል፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በ12 የመማሪያ ክፍል ተማሪዎች ላይ ነው፡፡ የማንበብ አመለካከት ከትምህርታዊ ንባብ፣ ከመዝናኛ ንባብ፣ ከአጠቃላይ አመለካከትና ከተጨማሪ ጥያቄዎች ጋር ተዛምዶ በተደረገው ዳሰሳ ጥናት የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው  በከተማና በገጠር ትምህር ቤት ተማሪዎች መካከል ልዩነት አልታየም፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ከተለያዩ ጎሳዎች መገኘት በማንበብ አመለካከት ላይ ያለውን አዎንታዊና አሉታዊ ሚና በሚመለከት ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች ያገኙት ውጤት የተለያየ ነው፡፡ በመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ አፍሪካዊ አሜሪካዊያን ተማሪዎች ለማንበብ ባላቸው አመለካከትና አንብቦ በመረዳት መጠን መካከል ስላለው ዝምድና ዌብ (2009) አጥንተዋል፡፡ ተመራማሪው የማንበብ አመለካከት ከተማሪዎች የማንበብ አመለካከት፣ ከጠቅላላ ንባብ፣ ከፆታ፣ ከንባብ ብቃት ጋር ያለውን ተዛምዶ ቃኝተዋል፡፡ በጥናታቸውም ከአምስት ግኝቶች ላይ ደርሰዋል፡፡ እነሱም (1) ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከት አወንታዊ ነው፤ (2) ለጠቅላላ ንባብም አወንታዊ ተዛምዶ ተመዝግቧል፤ (3) ፆታ ከማንባብ አመለካከት ጋር ተዛምዶው በጣም ከፍተኛ ሆኗል፤ (4) የተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የንባብ ብቃት በስታትስቲክስ ተዛምዶ አላሳየም፤ (5) ፆታ በማንበብ አመለካከትና ብቃት ላይ ተፅዕኖ የለውም፡፡ በተመሳሳይ ማክኪና፣ ኪአርና ኢልስዎርዝ (1995) በተለያዩ ጎሳዎች ላይ ባደረጉት ጥናት በመዝናኛና በትምህርታዊ ድርሳናት የማንበብ አመለካከት መካከል ያለው ተዛምዶ አሉታዊ መሆኑ  ታውቋል፡፡ ይህም በሒስፓኒክ፣ በአፍሪካዊ አሜሪካውያንና በነጮች መካከል በተደረገው ጥናት ልዩነቱ በጥቂቱ ተስተውሏል፡፡
በሌላም በኩል ፆታ በማንበብ አመለካከት ላይ ያለውን ተፅዕኖ በተመለከተ በጥናት የተደረሰበት ውጤት ተመሳሳይ ነው፡፡ ሎጋንና ጆንስተን (2009) ፆታ በማንበብ አመለካከት ላይ ተዛምዶ እንዳለው  ይገልፃሉ፡፡ ፆታን ከማንበብ ችሎታ፣ ከንባብ ድግግሞሽና ከማንበብ አመለካከት ጋር ያለው ተዛምዶ ተቃኝቶ የተገኘው ውጤት እንደሚያመለክተው በአጠቃላይ ሴቶች የተሻለ አንብቦ የመረዳት ችሎታ፣ ደጋግሞ የማንበብና እንዲሁም ለትምህርታዊ ንባብ አወንታዊ አመለካከት አላቸው፡፡ በጥናቱ ውጤትም በማንበብ ድግግሞሽና በብቃት ደረጃ መካከል ተዛምዶ ታይቷል፡፡ የወንዶች የማንበብ ችሎታ ከማንበብ አመለካከታቸው ጋር ተዛምዶ እንዳለውም በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ በተመሳሳይ ኩሽና ዋትኪንስ (1996) በፆታ ልዩነት ምክንያት በማንበብ አመለካከት ለረጅም ጊዜ ወጥ ሆኖ በመቆየት ከወንዶችና ከሴቶች ማን የተሻለ እንደሆን መርምረዋል፡፡ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት  በመቃኘት የተገኘው የጥናት ውጤት እንዳመለከተው የመዝናኛና የትምህርታዊ ድርሳናት ወይም ፅሁፎች  የማንበብ አመለካከቶች ውጤት ዝቅ ብሏል፡፡ ሴቶች ከወንዶች ጋር ሲነፃፀሩ ለመዝናኛ ንባብ ያላቸው አመለካከት አወንታዊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የሴቶቹ የማንበብ አመለካከት ከወንዶቹ በላቀ ደረጃ ለረጅም ጊዜ ወጥ ሆኖ የመዝለቅ ሁኔታም ታይቶበታል፡፡ በአጠቃላይ በጥናቱ እንደተጠቆመው ከወንዶቹ ይልቅ የሴቶቹ የማንበብ አመለካከት ለረጅም ጊዜ በዘላቂነት መቆየት እንደሚችል ተረጋግጧል፡፡
ሌሎች ተመራማሪዎች የማንበብ አመለካከትን ከማንበብ ችሎታ ውጤታማነት፣ ከማንበብ ብቃትና ከአንብቦ መረዳት ችሎታ ጋር ያለውን ተዛምዶ አስመልክተው ባደረጉት ጥናት  ያገኙት ውጤት ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ያኮቭ (2010) ባደረጉት ጥናት በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና በንባብ ችሎታ ውጤታቸው መካከል ያለውን ተዛምዶ መርምረዋል፡፡ የተዛምዶው አማካኝ ውጤትም መካከለኛ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ የተዛምዶው ውጤታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ማርቲንዝና ሌሎች (2008) ከማንበብ አመለካከት ጋር በተዛመደ በማንበብ ብቃት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ምክንያቶችን በጥናታቸው ለይተዋል፡፡ የስምንተኛ ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ ሳለበስ (2008) ባደረጉት የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ተዛምዶ ጥናት ተዛምዶው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ለዚህም ተጠቃሽ ምክንያቶቹ ተማሪዎቹ የቀረበላቸውን ንባብ በግልፅና በትክክል ለመረዳት አለመቻል፣ በአካባቢ፣ በወላጆችና በትምህርት ቤት ተፅዕኖ አመለካከታቸው በመዛባቱ ንባብን መጥላታቸው ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የማንበብ አመለካከትንና የአንብቦ መረዳትን ችሎታ በሚመለከት የተደረጉ ተመሳሳይና ተቀራራቢ ጥቂት ጥናቶች አሉ (ታፈረ 2000፣ ዘላለም 2010)፡፡ ጥናቶቹ እንደሚያስረዱት አጥኝዎቹ በማንበብ አመለካከትና በአንብቦ መረዳት መካከል ተመሳሳይ ውጤት አላገኙም ፡፡ ለምሳሌ ታፈረ (2000) በተማሪዎች የማንበብ ዳራና በአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለውን ዝምድና መርምረው በጥናታቸው ውጤቱን እንደገለፁት በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በወላጆችና በመማሪያ መፀሐፍ አማካኝነት በሚገኙ የንባብ ዳራዎች መካከል ጉልህ ልዩነት የታየ ሲሆን፣ ለልዩነቱ ምክንያቱ በተማሪዎች የግል ንባብ የተገኘ የንባብ ዳራ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም የአብዛኛዎቹ ተማሪዎች የንባብ ዳራ ማግኛ መንገድ ወደ ተማሪዎች ግለ ንባብ ያመዘነ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ በጥናቱ ተሳታፊዎች የንባብ ዳራና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ተመስርቶ በተደረገው ንፅፅርም፣ የንባብ ዳራ ማግኛ መንገዶች ከዝቅተኛ እስከ በጣም ከፍተኛ በደረጃ ከተመደቡት የአንብቦ መረዳት ችሎታ ውጤቶች ጋር ጉልህ ተዛምዶ እንዳላቸው ጥናቱ ያሳያል፡፡ ዘላለም (2010) በበኩላቸው ባደረጉት ጥናት የተማሪዎች የማንበብ ልምድ፣ አመለካከትና ምርጫን ቃኝተዋል፡፡ በጥናቱ ውጤት ግኝት መሰረት የተማሪዎቹ የማንበብ ልምድ ጥሩ ሆኖ አልተገኘም፣ የማንበብ አመለካከታቸው አዎንታዊ ነው፣ ከሴቶቹ ይልቅ የወንዶቹ የማንበብ አመለካከት የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡   
መሐመድ (1992) የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች የአማርኛ ቋንቋ ለመማር ያላቸውን ዝንባሌ[ አመለካከት] በሚመለከት ባደረጉት ጥናት የተማሪዎቹ  ዝንባሌ [አመለካከት] አወንታዊ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሱት (በተማሪዎች የመማር አመለካከት ላይ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ ጉዳዬች) ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ የመምህራን የማስተማር ዕውቀትና ዘዴ፣ የተማሪዎቹ ግላዊ ችሎታና የመማሪያ መፃህፍት ተፅዕኖ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ታዛሽ (1992) የ11ኛ ክፍል ተማሪዎችን የአንብቦ መረዳት ችሎታ አጥንተዋል፡፡ በጥናቱም የተማሪዎች አንብቦ የመረዳት ችሎታ ምን ያህል እንደሚመሳሰልና በአንድ የክፍል ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በደረጃቸው የሚጠበቅባቸው የአንብቦ መረዳት ችሎታ ያላቸው መሆንና አለመሆኑን መርምረዋል፡፡ በትንተናው ውጤት መሰረትም ተማሪዎች መካከለኛ የሆነ አንብቦ የመረዳት ችሎታ ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎቹ በደረጃቸው የሚጠበቅባቸውን የአንብቦ መረዳት ችሎታ አካብተው ያልተገኙ ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቱ ተማሪዎች አንብቦ የመረዳት ችሎታቸውን ለማጎልበት የሚያግዝ በቂ የሆነ ትምህርት ስለማይሰጣቸው ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ በተለያዩ ተለዋዋጮች አማካኝነት የማንበብ አመለካከትን በሚመለከት ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር በማዛመድ የተደረጉ ጥናቶችም አሉ (ደምሰው 1995፣ ገደፋው 1993)፡፡ ደምሰው (1995) የመማሪያ መፅሐፍ ምንባቦች የተማሪዎችን የማንበብ ፍላጎት ለመያዝ ያላቸውን ብቃት በሚመለከት አጥንተዋል፡፡ በጥናቱ ውጤት መሰረት የማንበብ ፍላጎት ምንባብን ለማንበብ  ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ ተማሪዎች በመማሪያ መጽሐፍ ውስጥ ላሉት ምንባቦች ፍላጎት አላቸው፡፡ የመማሪያ መፀሐፉ ምንባቦች የተማሪዎቹን ፍላጎት የመያዝ አቅም አላቸው፡፡ በተጨማሪም ምንባቦቹ በአብዛኛው በፍላጎት ላይ ተፅእኖ ከሚያሳድሩ መስፈርቶች አንፃር በአመዛኙ ስኬታማ ለመሆን የቻሉ ናቸው፡፡
ከዚህ ጥናት ጋር በተያያዘ ገደፋው (1993) ተማሪዎች ቋንቋን ለመማር ያላቸውን ፍላጎትና የትምህርት ውጤት ተዛምዶ አጥንተዋል፡፡ በጥናቱ እንደተመለከተው ፍላጎትና የትምህርት ውጤት ዝምድና አላቸው፡፡ ተማሪዎች አማርኛ ቋንቋን ለመማር ያላቸው ፍላጎት ተነሳሽነት ከፍ ሲል የትምህርት ውጤታቸው ከፍተኛ ሆኗል፡፡ በተቃራኒው ፍላጎታቸው ሲቀንስ የትምህርት ውጤታቸውም ዝቅ ብሏል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በመማሪያ መፀሐፍ ውስጥ የተካተቱት ምንባቦች የተማሪዎቹን ፍላጎት መሰረት አለማድረጋቸው ነው ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የመማር ፍላጎት ከቀነሰ የትምህርት ውጤት እንደሚቀንስ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ በዝርዝር እንደቀረበው በውጭ ሐገር በተደረጉት ጥናቶች በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ መካከል ልዩነቱን ያመላከቱ የመኖራቸውን ያህል፣ ተዛምዶ አለመኖሩንም ያሳዩ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ተመራማሪዎች በጥናታቸው የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታን ተዛምዶ ከተፈጥሮ፣ ከአካባቢ፣ ከፆታና ከትምህርት ደረጃ ጋር ለማዛመድ ሞክረዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ከማንበብ ውጤትና ከማንበብ ብቃት ጋር እያገናኙ ዝምድናውን ፈትሸዋል፡፡ ለምሳሌ ዱቢንና ዞርካኢያ (2010)፣ ሊን (2010)፣ ያኮቭ (2010)፣ ኩሽና ዋትኪንስ (1996)፣ ዌብ (2009) መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በሐገር ውስጥ ጥናቶች የታየው ክፍተት የማንበብ አመለካከት ከሌሎች ተለዋዋጮች ጋር እየተመሳከረ አልተጠናም፣ አመለካከትን ብቻውን ወይም አንብቦ የመረዳት ችሎታን በአንድ አቅጣጫ ብቻ በመመልከት የተሰሩ ጥናቶች ናቸው፣ አንዳንዶቹ ጥናቶች ደግሞ በማንበብ ፍላጎትና በመማሪያ መፀሐፍ የንባብ ችሎታን ከተነሳሽነት ጋር እያዛመዱ አጥንተዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ከማንበብ ምርጫቸውና ከማንበብ ልምዳቸው ጋር በማነፃፀር ብቻ ቃኝተዋል፡፡ ለዚህም የዘላለም (2010)፣ የመሐመድ (1992) እና የታፈረ (2000) ጥናትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህም ይህ ጥናት የተስተዋሉትን ክፍተቶች ለመሙላት በባሕር ዳር ከተማ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ ይመረምራል፡፡
የጥናቱ ዋና ትኩረት በባሕር ዳር ከተማ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ተዛምዶ መመርመር ሲሆን፣ በዚህም የሚከተሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ይመልሳል፡-
1.  በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ አለ?
2.  የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታቸውን የመተንበይ ድርሻው ምን ያህል ነው?
3.  በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በፆታ ልዩነት ያሳያል?
1.3. የጥናቱ ዓላማ
የጥናቱ ትኩረት በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ መፈተሽ ነው፡፡ የጥናቱ ንዑስ ዓላማዎች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡-
1.  በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ መኖር አለመኖሩን ለማሳየት፣
2.  የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታቸውን የመተንበይ ድርሻው ምን ያህል እንደሆነ ለማመላከት፣
3.  በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በፆታ ልዩነት እንዳለው ለማሳየት፣
1.4. የጥናቱ አስፈላጊነት
ይህ ጥናት በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለውን ተዛምዶ በማሳየት መምህራን የክፍል ውስጥ የትምህርት አሰጣጣቸውን እንዲፈትሹና እንዲያስተካክሉ ያግዛል፡፡ ስለሆነም ጥናቱ ለመምህራንም ሆነ ለትምህርት ባለሙያዎችና ለተመራማሪዎች የሚከተሉት ጠቀሜታዎች ይኖሩታል ተብሎ ይታሰባል፡-
  1. የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት በአንብቦ የመረዳት ችሎታ ያለውን የትንበያ መጠን ለመገንዘብ ስለሚያስችል ይህንን መሠረት በማድረግ የመማሪያ ክፍል የትምህርት አቀራረብ የማንበብ አመለካከትን እንዲሚያጎለብት መምህራኑ እንዲገነዘቡት ያደርጋል፡፡
  2. በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በፆታና በቤተሰብ ሁኔታ ልዩነት እንዳለውና እንደሌለው ስለሚያሳይ ወላጆች የልጆቻቸውን የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ በመገንዘብ ለችግሮቻቸው ከመምህራን ጋር በመተባበር መፍትሄ እንዲፈልጉ ያግዛል፡፡
3.  የትምህርት ባለሙያዎች በጥናቱ ግኝቶች መረጃ መሠረት የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ በመገንዘብ መምህራን የትምህርት ዕቅድ፣ መርሐ ትምህርትና የንባብ ትምህርት መርሐ ግብር ሲያዘጋጁ የተማሪዎቹን የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ከማጎልበት አንፃር እንዲመለከቱት ይረዳቸዋል፡፡
4.  በርዕሱ ዙሪያ ጥናት ማድረግ ለሚፈልጉ ተመራማሪዎች እንደ መነሻ በማገልገል በሥራ ላይ እንዲያውሉት  ያስችላቸዋል፡፡
1.5. የጥናቱ ወሰን
ይህ ጥናት በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከከል ያለውን ተዛምዶ በመመርመር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በጥናቱ የሚሳተፉት በባሕር ዳር ከተማ፣ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2004 ዓ.ም. ተመዝግበው የሚማሩ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ የተማሪዎችን ቁጥር ለመወሰን ከ10ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በዕድል ሰጭ የንሞና ዘዴ አማካኝነት አንድ የመማሪያ ክፍል ተመርጦ የክፍሉ ተማሪዎች የጥናቱ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ጥናቱ በ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ ብቻ እንዲካሄድ የተፈለገበት ምክንያት ተማሪዎቹ የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በመሆናቸው የዕድሜያቸው ደረጃ፣ የቤተሰባቸው ሁኔታ፣ የአስተሳሰባቸው መጠን፣ የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታቸውን ተዛምዶ ለመለካት ተገቢ ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡ በጥናቱ የሚፈተሸው በተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም በፆታና በቤተሰብ ሁኔታ ልዩነት መኖር፣ በማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለውን ተዛምዶ ብቻ እንጅ ሌሎች ተለዋዋጮችን ለምሳሌ እንደ ዕድሜ፣ የምጣኔ ሐብት ገቢና የመኖሪያ አካባቢ ሁኔታን በመመርመር ውጤቱን አያሳይም፡፡  
1.6. የጥናቱ ውስንነት
ጥናቱ በሚካሄድበት ወቅት የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታን ተዛምዶ ለመለካት  ሊወስኑት የሚችሉ ጉዳዮች  አሉ፡፡ እነሱም ጥናቱ የሚካሄደው በከተማ ትምህርት ቤት ላይ በመሆኑ የተዛምዶውን ውጤት  ከገጠር ትምህርት ቤት ጋር አነፃፅሮ ለመመልከት አያስችልም፤ በተጨማሪም የጥናቱ ውጤት የተማሪዎችን የማንብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ ብቻ ስለሚቃኝ ሌሎች ተዛምዶዎችን ለምሳሌ የማንበብ ልምድና የማንበብ ምርጫን ባለማካተቱ ጉድለት ሊኖርበት ይችላል፡፡
1.7. የቁልፍ ቃላትና የፅንሰ ሐሳብ አጠቃቀም ብያኔ
የጥናቱ ቁልፍ ቃላት የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ሲሆኑ፣ አጠቃቀማቸውም ቀጥሎ በቀረበው ብያኔ መሠረት ነው፡፡
1. የማንበብ አመለካከት፡- ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸውን በሚለካ መጠይቅ ሞልተው በሰጡት ምላሽ መሠረት የሚኖራቸውን አዎንታዊ ወይም አሉታዊ አመለካከት ይመለከታል፡፡
2. የአንብቦ መረዳት ችሎታ፡- በጥናቱ የሚሳተፉት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ችሎታቸውን በሚለካ የአንብቦ መረዳት ችሎታ ፈተና የሚያስመዘግቡትን ውጤት ይመለከታል፡፡



ምዕራፍ ሁለት፡- ክለሳ ድርሳን
2.1.አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ግንኙነት
አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ፡፡ ዴይና ባምፎርድ (1982) በጥናታቸው እንደገለፁት አመለካከቶች ሰዎች አንድን ተግባር እንዲያከናውኑ ወይም እንዳያከናውኑ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ አዎንታዊ አመለካከቶች አንድን ነገር ለማድረግ የሚያነሳሱ ሲሆኑ፣ በተቃራኒው አሉታዊ አመለካከቶች አንድን ተግባር በንቃት ለማከናወን  ተነሳሽነትን ይቀንሳሉ፡፡ በተመሳሳይ የማንበብ ተግባርም ግለሰቦች ለማንበብ ባላቸው አመለካከቶች አማካኝነት ተፅዕኖ ይደርስበታል፡፡ የማንበብ አመለካከታቸው አዎንታዊ የሆነ አንባቢያን ማንበብን መለማመድ ሲያፈቅሩ፣ ለማንበብ አሉታዊ አመለካከት ያላቸው ማንበብን ከመጥላታቸውም በላይ በማንበብ ተግባራት ለመሳተፍ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ይህ የሚያመለክተው አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ጥናት ያደረጉት ኮንሊ (1992) እንዳብራሩት የማንበብ አመለካከት ተማሪዎች አንድን ንባብ ለማንበብ ወይም ላለማንበብ ያላቸው ስሜት ሲሆን፣ ይህንን ተፅዕኖ የሚያሳድረው ደግሞ አመለካከት ነው፡፡ በተጨማሪም አዎንታዊ የማንበብ አመለካከት ስኬታማ ማንበብን ሲያጎናፅፍ አሉታዊ የማንበብ አመለካከት አንባቢያን ደካማ ፍላጎት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ አሌክሳንደርና ፊለር (1992) ጨምረው እንዳስረዱት ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከት አዎንታዊ ከሆነ የማንበብ ችሎታ ውጤታቸው ስለሚጨምር ብዙ ያነባሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የማንበብ አመለካከታቸው አሉታዊ ከሆነ ውጤቱ የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡
ሮኢና ስሚዝ (2005) እንዳብራሩት ደግሞ ተማሪዎች ንባብን ለመማር ተግባራትን ሲያከናውኑ በሂደቱ ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩት ነገሮች ዋነኞቹ የማንበብ አመለካከቶች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የቀረበላቸውን ምንባብ ለማንበብ በጐ አመለካከት ያላቸው ተማሪዎች ንባብን ለመማር ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ፣ በጐ ያልሆነ አመለካከት ያላቸው ግን በሂደቱ ለመሳተፍ እንቅስቃሴያቸው ዝቅ ያለ ነው፡፡
ተመሳሳይ ጥናት ያቀረቡት ኮንሊ (1992) እና ሜይ (1990) እንዳመለከቱት የተማሪዎችን የማንበብ አመለካት አዎንታዊ ወይም አሉታዊ የሚያደርጉት መምህራን ናቸው፡፡ ለምሳሌ መምህራኑ በመማሪያ ክፍል ውስጥ አዎንታዊ የማንበብ አመለካከትን የሚያጎለብቱ ልምዶችን ለተማሪዎች ካስተዋወቁ፣ ተማሪዎቻቸው ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ ያነበቡዋቸውን መፅሄት፣ መፀሐፍና መጣጥፍ ወደ መማሪያ ክፍላቸው ይዘው እያመጡ ካነበቡላቸው የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከት አዎንታዊ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ ሙለር (1973) የተባሉት ተመራማሪ በበኩላቸው የማንበብ አመለካከትን ለመለካት በ41 ተማሪዎች ላይ ቅኝት አድርገው ነበር፡፡ የጥናቱ ውጤት  እንደሚያመለክተው የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት በከፍተኛ ሁኔታ ለተፅዕኖ የሚያጋልጠው የመምህራን የማንበብ አመለካከት ነው፡፡ በማንኛውም ክስተት መምህራን የተማሪዎቻቸውን የማንበብ አመለካከት ከተረዱና ከተቀበሉት ለውጥ ያመጣሉ፡፡ ይህንን በሚመለከት ተመሳሳይ ጥናት ያደረጉት ሞዩር (1977) የማንበብ አመለካከትን ከመምህራን የማንበብ ልምድ ጋር አያይዘውታል፡፡ በተጨማሪም መምህራን አዘውትረው የሚያነቡ ከሆነ ተማሪዎቻቸውም የማንበብ አመለካከታቸው አወንታዊ እንዲሆን አርአያ ይሆናሉ፡፡ ይህንን በምርምር ለማረጋገጥ በተደረገው ጥናት አዘውትረው ከሚያነቡና ከማያነቡ መምህራን በመጠይቅ የተሰበሰበው መረጃ ውጤት እንዳመለከተው አንባቢ መምህራን ከማያነቡት በተሻለ ለተማሪዎች የማንበብ አመለካከት አርዓያ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ከዚህ በተለየ ኢስቴስ (1971) የተባሉት ተመራማሪ ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸው የሚለወጥበትን ምክንያት ለማወቅ ጥናት አድርገዋል፡፡ ይህንንም ዕውን ለማድረግ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት መለኪያ መጠይቅ አዘጋጅተው ነበር፡፡ በጥናቱ ከሶስተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከሚማሩ ተማሪዎች መካከል ናሙና በመውሰድ የማንበብ አመለካከታቸውን ለክተዋል፡፡ ከትንተናው የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው ማንበብን በተመለከተ የወጣት ተማሪዎች አመለካከት አወንታዊ ነው፡፡
ከዚህ ምርምር ጋር የሚቃረን ጥናት ያቀረቡት ተመራማሪ ራንስበሪ (1973) ናቸው፡፡ ተመራማሪው በጥናታቸው 65 የጥናት ተሳታፊ ተማሪዎችን፣ መምህራንና ወላጆችን በመምረጥ ለማንበብ የሚያስደስታቸውንና የማያስደስታቸውን ንባብ  እንዲገልፁ አድርገዋል፡፡ ተማሪዎቹ አንድን ንባብ እንዲያነቡና እንዳያነቡ የሚገፋፉት በንባብ መማሪያ  መፃህፍት አማካኝነት መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ወላጆች ንባብን እንዲጠሉት ያደረጋቸው ምክንያት አዘውትረው አለማንበባቸው ነው፡፡ መምህራን በበኩላቸው የማንበብ አመለካከት አወንታዊና አሉታዊ እንዲሆን የሚያደርገው የተማሪዎች አዕምሯዊ ችሎታ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ በጥናቱ ማጠቃለያ ላይ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ተፅዕኖ የሚያሳድርበት ዋነኛ ምክንያት የንባብ ችሎታ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ሒዚግነቶንና አሌክሳንደር (1984) ባካሔዱት ጥናት ደግሞ አወንታዊ የማንበብ አመለካከትን ለማዳበር የመምህራንና የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ገምግመዋል፡፡ በጥናቱ 100 መምህራን በማስተማር ልምዳቸው መሰረት ተመርጠው ንባብን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ሲያስተምሩ ምን፣ ምን ተግባራትን እንደሚያከናውኑ አጠቃላይ መጠይቅ ቀርቦላቸዋል፡፡ በመጠይቁ ላይ ትኩረት በመስጠት የሚጠቀሙባቸውን 9 የማስተማር ልምዶችን በቅደም ተከተል እንዲዘረዝሩ ተጠይቀዋል፡፡ በመጠይቁ የቀረቡላቸው ዝርዝሮችም አንብቦ መረዳት፣ ቃላዊ ንባብ፣ የዝምታ ንባብ፣ ቃላዊ ትርጉም፣ ቃላትን መምረጥ፣ መዋቅራዊ ትንተና፣ የማንበብ አመለካከቶችና የክህሎት ጥናት የሚሉ ነበሩ፡፡ ከመጠይቁ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው በርካታዎቹ መምህራን የማስተማሪያ ክፍለ ጊዚያቸውን ለማንበብ አመለካከት ማጎልበቻነት አይመድቡም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ መምህራኑ ክህሎትን በማስጨበጥ ላይ ስለሚያተኩሩና የክህሎት እድገት የማንበብ አመለካከትን አዎንታዊና አሉታዊነት ለመጨመርና ለመቀነስ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡
ማና እና ማይሽፍ (1987) ከላይ ያለውን ጥናት በመቃረን ባደረጉት ጥናት በዩኒቨርስቲ የስነ-ፅሁፍ ተማሪዎች ለምን ለአሉታዊ የማንበብ አመለካከት እንደተጋለጡ መርምረዋል፡፡ ምክንያቱንም ለመገንዘብ ጥረት አድርገዋል፡፡ ጥናቱን ተግባራዊ ለማድረግ በጥቅም ላይ የዋለው የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያ ተማሪዎቹ ግለ ታሪካቸውን እንዲሞሉ በማድረግ ነበር፡፡ ከተማሪዎቹ ግለ ታሪክ በዳግም ግምገማ ከተገኘው ውጤት ለመረዳት እንደተቻለው በተማሪዎቹ ላይ አሉታዊ የማንበብ ተፅዕኖ ያሳደረው የተማሪዎቹ ወላጆችና መምህራን አርዓያ በመሆን የማንበብ አመለካከታቸው እንዲጎለብት ድጋፍ ስላላደረጉላቸው ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሞሪሰን፣ ጃኮብስና ስዊንያርድ (1999) መምህራን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ለተማሪዎቻቸው የሚያነቡላቸው ግላዊ የመዝናኛ ንባብ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ለመለወጥ ያለውን ፋይዳ በሚመለከት አጥንተዋል፡፡ በመጠይቅ ከተሰበሰበው የማስተማርና ግላዊ የንባብ ልምድ መረጃ ከተገኘው ውጤት ለመረዳት እንደተቻለው መምህራን በአብዛኛው የሚያነቡት የሚያስተምሩትን ትምህርት መፃሕፍት ንባቦችን ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ተማሪዎቹ ማንበብን መሰረት በማድረግ እየተዝናኑ ስለማይማሩ ለማንበብ ያላቸው አመለካከት ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ ወደ መሆን አዘንብሏል፡፡
አፕሊጌትና አፕሊጌት (2004) ያደረጉት ጥናት የመምህራንን የማንበብ ልምዶችና አመለካከቶች የሚመርምር ነው፡፡ በልቅ መጠይቅ አማካኝነት በመምህራን ላይ በተደረገው ቅኝት 54% የሚሆኑት መምህራን የማንበብ ጉጉት የሌላቸው መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ለዚህም ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የተገመተው መምህራኑ በቀድሞ የትምህርት ዘመናቸው ወቅት የማንበብ አመለካከታቸው አሉታዊ ተፅዕኖ አድሮበት ስለነበር ነው፡፡ በጥናቱ ማጠቃለያ  ላይ እንደሰፈረው የመምህራን ማንበብን ያለመውደድ ልምድና የአመለካከት አለመዳበር የተማሪዎቻቸውን የማንበብ አመለካከት በዕጅጉ እንደሚጎዳ ተገልጧል፡፡
የብላክቢ (2006) ጥናት ከአፕሊጌትና አፕሊጌት (2004) የተለየ ነው፡፡ ተማሪዎች እንደሚኖሩበትና እንደተማሩት አግባብ የማንበብ ክሕሎታቸው ዕድገት ለተፅዕኖ ይጋለጣል፡፡ በማንበብ አመለካከቶች ላይ አወንታዊና ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ ለማድረስ ምክንያት የሚሆኑት ጉዳዬች ተፈጥሮ (innate) ፣ ቤተሰብና ትምህርት ቤት ናቸው፡፡ እነዚህ የተፅዕኖ ምክንያቶች ተማሪዎች ለማንበብ በሚነሳሱበት ወቅትና ራሳቸውን እንደ አንባቢ መቁጥር በሚጀምሩበት ጊዜ ማንበብን እንዲወዱ ወይም እንዲጠሉ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ብላክቢ (2006) ጨምረው እንደገለፁት፣ ቤተሰብ በማንበብ ላይ አንዳንድ ተፅዕኖዎች ያሳድራል፡፡ ማህበራዊ መደቦችና የቤተሰብ ባሕል የተማሪዎች ማንነት ላይ ጫና በመፍጠር ተፅዕኖ የሚያሳድረው አመለካከታቸውና የንባብ ተግባራቶች ላይ ነው፡፡ ተማሪዎች በቤተሰባቸው አማካኝነት የማንበብና የመፃፍ ችሎታቸው ሲያድግ አመለካከታቸውም አብሮ ያድጋል፡፡
ሞሮውና ያንግ (1997) በተመሳሰይ እንዳጠኑት ወላጆች በመኖሪያ ቤት ልምዶቻቸው በልጆቻቸው ላይ ተፅዕኖ እንዲሚያሳድሩ ያምናሉ፡፡ የቀን ተቀን የቤተሰብ ተግባራት በልጆች የማንበብ ዕድገት፣ በአመለካከቶቻቸውና በማንበብ ተግባራት የተሳትፎ ፍላጎታቸው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ወላጆች ወይም ልጆችን ተንከባካቢዎች መልካም አርዓያ በመሆን ተፅዕኖ ለማሳደር የሚችሉበት ምክንያት ልጆቻቸው በማንበብ ልምምድ ወቅት ምን፣ እንዴት፣ መቼና ለምን እንደሚያነቡ ስለማያስረዷቸው ነው፡፡
ይሁን እንጁ ማዩንግሱንና ሒኪዩንግ (2002) ባደረጉት ጥናት የማንበብና የአመለካከት ዕድገት የሚመጣው በትምህርት ቤት ብቻ የሚመስላቸው በርካታ ወላጆች እንዳሉ አረጋግጠዋል፡፡ በእርግጥ በቤተሰብ ብቻ ሳይሆን፣ በትምህርት ቤት አማካኝነትም በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አዩናላና ሌሎች (2002) በትምህርት ቤት ውስጥ የማንበብ አመለካከትን ለተፅዕኖ የሚያጋልጡ ናቸው በማለት የዘረዘሯቸው፡- ተማሪዎችን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ለመዝናናት ማስነበብ፣ በራሳቸው ምርጫ ፅሁፎችን እንዲያነቡ ማድረግና በክፍል ውስጥ ለጓደኞቻቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማስነበብ ናቸው፡፡
ጋምብሪል (2004)፣ በጥናታቸው ግኝት እንደደረሱበት መምህራን ተማሪዎችን አዝናኝ ንባቦች መርጠውላቸው ማስነበብ የማንበብ አመለካከታቸው አወንታዊ ቅርፅ እንዲይዝና የራስ ግላዊ ውጤታማነታቸው እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ተማሪዎቹ በመደበኛነት የመዝናኛ ንባብ የሚያነቡ ከሆነ በስፋትና በጥልቀት ማንበብ እንዲለምዱ፣ የማንበብ ክህሎት ብቃታቸው እንዲያድግ፣ የአንብቦ መረዳትና የቃላት ችሎታቸው እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ምናባቸውን ለማስፋት፣ የፈጠራና የክህሎት ዕድገታቸውን ከፍ ለማድረግ ይረዳል፡፡ የጉዝሪ (1999) የጥናት ውጤት ከጋምብሪል (2004) ጋር ይቃረናል፡፡ ተማሪዎች በራሳቸው ምርጫ ብቻ  የመዝናኛ ፅሁፎች ወይም ድርሳናትን መርጠው ማንበባቸው ከራሳቸው ፍላጎትና አመለካከት ጋር የሚገጣጠም ርዕስ እንዲያነቡ ስለሚያደርጋቸው በራሳቸው ሙከራዎች ስሌት ዕውቀትና ልምዶቻቸውን በማስፋት ግላዊ ዓላማቸውን ለማሳካት ያገለግላቸዋል፡፡
ከዚህ ጥናት በተለየ ድሪኸር (2003) እንደገለፁት ተማሪዎች ድምፃቸውን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ከፍ አድርገው እንዲያነቡ ማድረግ አወንታዊ የማንበብ አመለካከታቸው እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ ተማሪዎቹን ከንባብ በኃላ በቁልፍ ሐሳቦች ላይ ማወያዬት ፍላጎታቸውን ያጠናክራል፡፡ አወንታዊ የማንበብ አመለካከታቸውን ያሳድጋል፡፡ ብራስል (2003) እንደጠቀሱት ደግሞ የመዝናኛ ምንጭ ይሆናቸዋል፣ የቃላት ክምችታቸው መሰረት ይይዛል፣ ውጤታማ የንባብ ብልሐቶችን ይማራሉ፡፡
በመጨረሻም ስችማይት (2009) እንደሚገልፁት የማንበብ አመለካከትን በሚመለከት   ተመሳሳይና ተቃራኒ ጥናቶች አሉ፡፡ የጥናቶቹ ግኝቶች የማንበብ አመለካከት በወላጆችና በመኖሪያ ቤት አካባቢ፣ በመማሪያ ክፍል እንዲሁም በተማሪዎችና በመምህራን አመለካከትና ባሕሪ ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ያላቸውን ግንኙነት የሚጠቁሙ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ከተደረጉት ጥናቶች ቅኝት ለመገንዘብ እንደሚቻለው ማንበብና የማንበብ አመለካከት ጥብቅ ግንኙነት አላቸው፡፡ አመለካከት በማንበብ ላይ የሚያሳድረው የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ የማንበብ አመለካከት ተለዋዋጭ ሲሆን፣ ምክንያቶቹም ወላጆች፣ ቤተሰብ፣ መምህራንና አካባቢ የሚያሳድሩት አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም አመለካከትና የማንበብ አመለካከትን ግንኙነት ጠንቅቆ በመረዳት በትምህርት ቤት ውስጥ በተማሪዎች የማንበብ አመለካከት ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ መፈለግ ያሻል፡፡
2.2. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከት
ኩሊክና ኩሊክ (1982) በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በችሎታ አቅም የተደራጀ ቡድን ለአመለካከት ለውጥ ያለውን አስተዋፅኦ በሚመለከት ጥናት አድርገዋል፡፡ ጥናቱ የተካሄደው 52 ተማሪዎችን በከፍተኛ፣ በመካከለኛና በዝቅተኛ ችሎታ ቡድኖች በማደራጀት ነበር፡፡ የጥናቱ ውጤት እንዳመለከተው ተማሪዎችን በቡድን ማደራጀት ለአመለካከት ለውጥ ጠቀሜታ አለው፡፡ በጥናቱ በቡድን የተደራጁት ተሳታፊዎች ለሚማሩት የትምህርት ዓይነት በርካታ አዎንታዊ አመለካከቶችን ሲያሳድጉ፣ በቡድን ያልተደራጁት ግን አመለካከታቸው አሉታዊ ሆኗል፡፡ በቡድን ከተደራጁት መካከልም ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች አመለካከታቸው ከፍተኛ ሲሆን፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ችሎታ ያላቸው የአመለካከታቸው ደረጃ መካከለኛዎቹ መካከለኛ፤ ዝቅተኛዎቹ ደግሞ ወደ ዜሮ የሚጠጋ አመለካከት አስመዝግበዋል፡፡
በተመሳሳይ ሊናና ካሪም (2007) የማንበብ አመለካከት፣ ቤተሰባዊ ቅድመ ሁኔታና በራስ ጥረት መማር በማንበብ ችሎታ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በሚመለከት ጥናት አድርገዋል፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በ4018 የጥናቱ ተሳታፊ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ መጠይቅና አንብቦ የመረዳት ፈተና በማቅረብ ነው፡፡ ከጥናቱ የተገኘው ውጤት እንደጠቆመው የቃላዊ/የአጠቃላይ ትምህርት በራስ ጥረት መረዳት (Verbal/General academic self-concept) የማንበብ ችሎታ ከፍተኛ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም የፆታ ልዩነት በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ እንዳለውና እንደሌለው ተፈትሿል፡፡ በጥናቱ ውጤት እንገተገለፀው ሴቶቹ ተማሪዎች ከወንድ ተማሪዎች በተሻለ አዎንታዊ የማንበብ አመለካከት አላቸው፡፡ ወንዶቹ ተማሪዎች የተሻሉ ሆነው የተገኙት ትምህርትን በራስ ጥረት በመረዳት፣ በራስ ውጤታማነት፣ በማስታዎስ፣ በማብራራትና በመነሳሳት ናቸው፡፡
በተጨማሪም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አስቸጋሪ አጫጭር ታሪኮችን(ንባቦችን) የማንበብ አመለካከት፣ አንብቦ የመረዳትና የማስታዎስ ችሎታ ለመመርመር ግራቪስ፣ ላበርግና ኩኪ (1983) ጥናት አድርገው ነበር፡፡ ለጥናቱ ተሳታፊ 72 ተማሪዎች በደረጃቸው አንብቦ ለመረደት ቀላልና አስቸጋሪ አጫጭር የንባብ ታሪኮችን በማቅረብ ጥናቱ ተካሂዷል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንዳመለከተው አንብቦ ለመረደት ቀላል ለሆኑት ታሪኮች የተማሪዎቹ አመለከካት አዎንታዊ ሲሆን፣ የመረዳትና የማስታዎስ ችሎታቸውም ከ13% እስከ 38% ጨምሯል፡፡
በሌላም በኩል ክሪስቲናና ጆናታን (2011) የታላቋ እንግሊዝ ወጣት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸው ለምን እንደቀነሰ ለማወቅ ጥናት አድርገዋል፡፡ በጥናቱ በ17,000 ተማሪዎች ላይ ለማንበብ አመለካከታቸው መቀነስ የትምህርት ቤት የማንበብ ብቃት፣ የፆታ ወይም የጎሳ ልዩነት ምክንያት እንደሆን ቅኝት በማድረግ ባህሪያቸውን ለመመርመር ጥረት ተደርጓል፡፡ በጥናቱ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከት ከ2005 እስከ 2009 ባሉት አምስት ዓመታት  ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ ምክንያቱ ደገሞ  ወጣቶቹ በማንበብ ስለማይደሰቱ ማንበብን ማቆማቸው ነው፡፡
በመጨረሻም በትምህርት ውጤታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸውን አመለካከት፣ የማንበብ ችሎታ ውጤታቸውንና በራስ ጥረት ማንበብን በማጐልበት የትምህርት ብቃታቸውን ማሳደግ ይቻልና አይቻል እንደሆን ለመመርመር ቲዎዶር (2010) ጥናት አድርገው ነበር፡፡ ጥናቱን ለማካሄድ በትምህርታቸው ውጤታማ የሆኑ ተማሪዎችን በሁለት ቡድን በማደራጀት አንደኛው ቡድን በንባብ ማሻሻያ መርሐ ግብር (Remedial Reading Program) እንዲሳተፍ ሲደረግ ሌላው ቡድን ግን አልተሳተፈም፡፡ በተጨማሪም ሁለቱም ቡድኖች የማንበብ አመለካከት መጠይቅ እንዲሞሉ ተደርጓል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደጠቆመው በንባብ መፍትሄ መርሐ ግብር የተሳተፉት ተማሪዎች ካልተሳተፉት ጋር ሲነፃፀሩ የማንበብ አመለካከታቸው ተሻሽሏል፣ በራስ ጥረት የማንበብ ውጤታማነታቸው ደረጃው ከፍተኛ ሆኗል፡፡
ለማጠቃለል ያህል ከጥናቶቹ ውጤት ለመገንዘብ እንደሚቻለው የሁለተኛ ደረጃ ትህርት ቤት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከት በተለያዩ ምክንያቶች ለተፅኖ ይጋለጣል፡፡ ተማሪዎችን በቡድን ማደራጀት ለአመለካከት ለውጥ ጠቀሜታ አለው፡፡ የማንበብ አመለካከት፣ ቤተሰባዊ ቅድመ ሁኔታና በራስ ጥረት መማር በማንበብ ችሎታ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ አንብቦ ለመረደት ቀላል የሆኑ ታሪኮች(ንባቦች) የተማሪዎቹን የማንበብ አመለከካት አዎንታዊ ያደርጋሉ፤ የመረዳትና የማስታዎስ ችሎታን በእጅጉ   ይጨምራሉ፡፡ በማንበብ የማይደሰቱ ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ ቢሆንም አመለካከታቸውን በተለያዩ ዘዴዎች በማሳደግ ማሻሻል ይቻላል፡፡
2.3. የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ
ሳላበስ (2008) በ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ መኖርና አለመኖሩን በሚመለከት ባደረጉት ጥናት የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ ደረጃው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከትና የትምህርት ውጤታቸው ተዛምዶ እንዳለው ተጠንቶ ተዛምዶው ዝቅተኛ ደረጃ እንዳለው ተረጋግጧል፡፡ በጥናቱ በፆታ ምክንያት የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ልዩነት እንዳለው ታውቋል፡፡ ለዚህም በጥናቱ  እንደ ምክንያት የተጠቀሱት ተማሪዎቹ የቀረበላቸውን ንባብ በግልፅና በትክክል አለመረዳታቸው፣ የንባቡን መዋቅር፣ ይዘትና ቴክስት ለመተቸት አለመቻላቸው ናቸው፡፡
ፒትስቸር (2010) በተመሳሳይ ባደረጉት ጥናት በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የማንበብ ችሎታ ውጤት መካከል ያለውን ተዛምዶ ቃኝተዋል፡፡ በ32 ተማሪዎች ላይ በተደረገው ጥናት የተገኘው ውጤት እንደጠቆመው የተዛምዶው መጠን ዝቅተኛ ነው፡፡ በጥናቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የማንበብ ውጤታማነት መካከለኛ ተዛምዶ ሲኖረው፣ በመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩት ዝቅተኛ ተዛምዶ አስመዝግበዋል፡፡    
ከዚህ ጥናት ጋር በተያያዘ ናንሲ (1989) ከ 1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎችን ለማንበብ ያላቸውን አመለካከትና የማንብ ችሎታ ውጤት ተዛምዶ አጥንተዋል፡፡ በጥናቱ የተሳተፉ 876 ተማሪዎች ከሞሉት የማንበብ አመለካከት መለኪያ መጠይቅና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ፈተና  የተገኘው ውጤት እንደሚያስረዳው (1) በተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከትና የንባብ ውጤታማነት መካከል ተዛምዶው  ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፤ (2) የማንብቦ ችሎታ ውጤታቸው ደረጃው መካከለኛ ሆኗል፤ (3) እስከ ስምንተኛ ክፍል ባሉት የትምህርት ደረጃዎች የማንበብ አመለካከታቸው ቀንሷል፤ (4) ከወንዶቹ ተማሪዎች በተሻለ የሴት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የንባብ ውጤታማነት ተዛምዶ ከፍተኛ ሆኗል፤ (5) የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች የማንበብ አመለካከት አዎንታዊ እንደነበር ተጠቁሟል፤ (6) በሴትና በወንድ ታሪዎች መካከል የማንበብ ብቃትን በሚመለከት ጉልህ ልዩነት አልታየም፤ (7) ዝቅተኛ የማንበብ ችሎታ ውጤት (achievement) ያላቸው ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸውም ቀንሷል::
በተጨማሪም ባስ (2012) የተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የመፃፍ ዝንባሌ ተዛምዶ እንዳላቸውና እንደሌላቸው አጥንተዋል፡፡ ተመራማሪው በቱርክ ሐገር ኒጋዳ ትምህርት ቤት በ450 ተማሪዎች ላይ ባደረጉት ጥናት በመጠይቅ የተሰበሰበው መረጃ ውጤት እንዳመለከተው በማንበብ አመለካከትና በመፃፍ ዝንባሌ መካከል አዎንታዊ ተዛምዶ አለ ፡፡ እንዲሁም የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት የመፃፍ ዝንባሌያቸውን የመተንበይ ድርሻው የጎላ ነው፡፡
በተመሳሳይ ተራቪስ (2010) የተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና ስነፅሁፍ የማንበብ ልምዳቸው ተዛምዶ መኖርና አለመኖሩን መርምረዋል፡፡ ለ18 ወራት በተደረገው ጥናት የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከት፣ የንባብ ልምድና በተጓዳኝም ሥነ ፅሁፍን የማንበብ ተነሳሽነታቸው በመጠይቅ መጠናዊና ዓይነታዊ መረጃ ተሰብስቦ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸው በጐለበተ መጠን ልምዳቸው በመዳበሩ የማንበብ ተነሳሽነታቸው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊለወጥ ችሏል፡፡ በጥናቱ ተማሪዎች ለረጅም ጊዜ እያነበቡ የመቆየት ልምዳቸው በአመለካከታቸው ላይ ለውጥ አልታየበትም፡፡
ከዚህም ሌላ የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ በፆታ ልዩነት ተዛምዶ እንዳለውና እንደሌለው ለመመርመር የተደረጉ ጥናቶች አሉ፡፡ ዊዊ (2009) በቻይና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የፆታ ልዩነት ከአንብቦ በመረዳት ችሎታ ጋር ያለውን ተዛምዶ መርምረዋል፡፡ በመጠይቅና በክለሳ ድርሳን ሪፖርት የተሰበሰቡት መረጃዎች እንዳመለከቱት ሴት ተማሪዎች ከወንድ ተማሪዎች በተሻለ ሁኔታ ብልሐቶችን በመጠቀም፣ የንባብ ጭንቀትን በመቋቋም እንዲሁም አንብቦ በመረዳት ችሎታ የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሮዊል (1972) የማንበብ አመለካከትን የሚለውጡ ምክንያቶችን ለመመርመር ጥናት አድርገዋል፡፡ በጥናታቸውም የማንበብ አመለካከት አንብቦ ከመረዳት ችሎታ፣ ቃላትን ከመለየት፣ ከፆታ፣ ከዕድሜና ከማሕበራዊ ደረጃ ጋር ያለውን ተዛምዶ አጥንተዋል፡፡ ተመራማሪው የጥናቱን ተሳታፊዎች በሙከራ ቡድንና በቁጥጥር ቡድን በመከፋፈል ከሰበሰቡት መረጃ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው የማንበብ አመለካከት በፆታ፣ በዕድሜና በማህበራዊ ደረጃ ተዛምዶው በስታስቲክስ ጉልህ ልዩነት አልተገኘበትም፡፡ ልዩነት የታየው ቃላትን ተገንዝቦ በመለየት ላይ ነው፡፡
በጥናቶቹ እንደተጠቆመው የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ እንዳይጎለብት የሚያደርጉት ምክንያቶች አዎንታዊ የማንበብ አመለካከት እንዲዳብር ትኩረት ባለመሰጠቱ፣ መምህራን የበርካታ ተማሪዎቻቸውን የማንበብ አመለካከት ዝንባሌ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ማከናዎናቸው እንዲሁም ወላጆች ማንበብን የትርፍ ጊዜ ተግባር አድርገው መቁጠራቸው ናቸው (ሮዊል 1972፣ ዊዊ 2009)፡፡                     
ከዚህ በተለየ አቡ-ራቢያ (1996) አመለካከቶችና ባሕላዊ ዳራ በሁለተኛ ቋንቋ አንብቦ ከመረዳት ችሎታ ጋር ያላቸውን ተዛምዶ ከሶስት ማሕበራዊ አውዶች ጋር በማነፃፀር ጥናት አድርገዋል፡፡ በጥናቱ ከተሳተፉት እስራኤላዊ አረብ፣ እስራኤላዊ አይሁድና ካናዳዊ አረብ ተማሪዎች የተገኘው ውጤት እንደሚያስረዳው በራሳቸው ባሕል የቀረበላቸውን ፅሁፍ የተፈተኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች የማንበብ አመለካከትና ፍላጎታቸው እንዲሁም አንብቦ የመረዳት ችሎታቸው የተሻለ ሆኖ ተገኝተል፡፡ የካናዳዊ አረቦቹ ቡድን ውጤት ከእስራኤል አረቦቹና ከአይሁድ አረቦቹ ጋር ሲነፃፀር የቴክስቱ ይዘት ሳይሆን የቴክስቱ ቋንቋ አንብቦ ለመረዳት ተፅዕኖ አሳድሮባቸዋል፡፡
በተጨማሪም ግሪአኒ (1987) የማንበብ አመለካከት፣ የመኖሪያ አካባቢና የማንበብ ፍላጎት ከማንበቢያ ትርፍ ጊዜ (leisure-time reading) ጋር ያላቸውን ተዛምዶ በሚመለከት በጥናታቸው ቃኝተዋል፡፡ ከጥናቱ የተገኘው ውጤት እንደሚያስረዳው የመኖሪያ አካባቢና የማንበቢያ ትርፍ ጊዜ ተዛምዶ አላቸው፡፡ ከሌሎቹ ተለዋዋጮች በላቀ ሁኔታ የማንበብ አመለካከት ከማንበቢያ ትርፍ ጊዜ ጋር በጥብቅ ይዛመዳል፡፡ የማንበብ ፍላጎትና የማንበቢያ ትርፍ ጊዜ ያላቸውን ተዛምዶ በሚመለከት ጥናቱ እንዳመለከተው ለመዝናኛ ንባብ ካልሆነ በስተቀር ትርፍ የማንበቢያ ጊዜ ለትምህርታዊ ንባብ ብዙም ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡
ቡክሆረስት-ሄንግና ፔሪራ (2008) በአንድ የሲንጋፖር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዓመቱ የትምህርት ማብቂያ ተማሪዎች አሉታዊ የማንበብ አመለካከት ሊያድርባቸው የቻለበትን ምክንያት አጥንተዋል፡፡ ለዚህም ትርፍ ጊዜን በንባብ ተግባር ላይ አለማዋል በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ታውቋል፡፡ በጥናቱ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው በማንበብ አመለካከት በሴቶችና በወንድ ተማሪዎች መካከል የጎላ ልዩነት አልታየም፤ ሁሉም የጥናቱ ተሳታፊዎች የማንበብ ውስጣዊ ፍላጎታቸው ግን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡
በአጠቃላይ ከጥናቶቹ ውጤት ለመረዳት እንደሚቻለው የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ተዛምዶ አላቸው የሚሉ ተመራማሪዎች አሉ ለምሳሌ ሳላበስ (2008)፣ አቡ-ራቢያ (1996)ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሌላም በኩል ተዛምዶው ቢኖርም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙ ተመራማሪዎች አሉ (ግሪአኒ 1987፣ ቡክሆረስት-ሄንግና ፔሪራ 2008)ን መጥቀስ ይቻላል፡፡
 2.3. የማንበብ አመለካከት አንብቦ ለመረዳት ያለው ሚና
ወላጆች የማንበብ አመለካከትን ለማሳደግና ለማጠናከር በመኖሪያ ቤት ውስጥ  ሁለት ሚናዎችን  ይጫወታሉ፡፡ የመጀመሪያው ሚና ማንበብን ባህላቸው አድርገው የሚነበቡ ነገሮችን በመኖሪያ ቤት ውስጥ ማስቀመጣቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ሚና በማንበብ ልምዳቸው አማካኝነት  ለልጆቻቸው አዝናኝና አስተማሪ ድርሳናትን እያነበቡላቸው ተፅዕኖ ማሳደራቸው ናቸው፡፡ ወላጆች የማንበብ ልምዳቸውን በማዳበር ለልጆቻቸውም አርአያ ከሆኑ ልጆቻቸው በመኖሪያ ቤት ውስጥ እንዲያነቡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ (ስፓይገል 1994)፡፡ ወላጆችና የመኖሪያ ቤት አካባቢ በአመለካከት ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በጎ ከሆነ በትምህርት ቤት አወንታዊ አመለካከትን ለማጠናከር ለሚደረገው ጥረት በቅርበት አብሮ ለመስራት ያግዛቸዋል (አሌክሳንደርና ፊለር 1976)፡፡
በተጨማሪም ስችማይት (2009) የተማሪዎችን አወንታዊ የማንበብ አመለካከቶች ማሳደጊያና ማጠናከሪያ ናቸው በማለት የሚዘርዝሯቸው 5 መንገዶች አሉ፡፡ እነሱም በመኖሪያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ወላጆች፣ በትምህርት ቤት አካባቢ ያሉ የመማሪያ ክፍሎች፣ በተለያዩ መሳሪያዎች የሚሰበሰቡ የአመለካከት ግምገማዎች፣ የማስተማር ልምዶች፣ የተማሪዎችና የመምህራን አመለካከትና ባህሪያት ናቸው፡፡
ይህንን ሀሳብ በመቃረን ክራመር (1994)፣ ዊየርና ዊየር (1994)ና ብሮፊ (2004) የማንበብ አመለካከትን ለማሳደግና ለማጠናከር የሚቻለው በመኖሪያ ቤት ሳይሆን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ብቻ ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ ለዚህ አባባላቸው በምክንያትነት የሚጠቅሱት የመምህራንና የተማሪዎች የመማሪያ ክፍል ውስጥ ተራክቦ፣ ንቁ የሆነ የመማር መነሳሳት ካለ፣ የመማሪያ መፃሕፍት  በተማሪዎች ፍላጎት መሰረት ከተመረጡ፣ መምህራን በተማሪዎች የመማሪያ ክፍል ውስጥ ቤተ- መፃህፍት ካዘጋጁ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ብቻ የማንበብ አመለካከትን ማሳደግና ማጠናከር ይቻላል፡፡
በዚህ ሀሳብ የማይስማሙት ማክኪና፣ ኪአርና ኢልስዋርዝ (1995) የመምህራንና የተማሪዎችን አመለካከቶችና ባህሪያት ጠንቅቆ በማወቅ የማንበብ አመለካከትን ማሳደግና ማጠናከር ይቻላል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸውን አዎንታዊና አሉታዊ ምክንያት በመገንዘብ ለችግሮቹ መፍትሔ ፈልጎ ያላቸውን ማጠናከር፣ የሌላቸውን መፍጠር ይቻላል፡፡ ልጆች በመኖሪያ ቤትም ሆነ በትምህርት ቤት በትርፍ ጊዜያቸው እንዲያነቡ ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸው፣ ወላጆችና መምህራን ደካማና ጎበዝ እያሉ በአንባቢያን መካከል ልዩነት ካልፈጠሩ፣ መምህራን በትምህርት ቤት ውስጥ  ጎበዝ ተማሪዎች የማንበብ አመለካከታቸው አዎንታዊ ሲሆን፣ የሰነፍ ተማሪዎች ግን አሉታዊ ነው በማለት ተማሪዎችን ካልከፋፈሉ፤ በፃታ ፣በዕድሜና በጎሳ አማካኝነት የማንበብ  ተፅዕኖን አጥንቶ መፍትሔ ከተፈለገ የማንበብ አመለካከትን የትም ቢሆን ማሳደግና ማጠናከር ይቻላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ራሲኒስኪና ፓዳክ (2000) እንዳመለከቱት የተማሪዎች ንባብ ስኬታማ እንዲሆን መምህራን መፃሕፍትን ማንበብ በመውደድ አርዓያ ሊሆኗቸው ይገባል፡፡ መምህራኑ ለተማሪዎቻቸው የማንበብ አርአያ ከሆኑ፣ በመማሪያ ክፍል ውስጥ የማንበብ ፍላጎትን ለማነሳሳት ተቀባይነት ያገኛሉ፡፡ አርአያ በሚሆኑበት ወቅት ከመምህራኑ የሚጠበቀው ክንውን ተማሪዎቻቸው በዝምታ ንባብን ሲያነቡ እንዲመለከቷቸው ማድረግ ሳይሆን፣ ካነበቡት ምንጭ እየጠቀሱ ማንበብ ሕይወታቸውን እንዴት እንደለወጠው ለተማሪዎቻቸው ቢነግሯቸው ተማሪዎችም ከማንበብ የሚገኘውን ጥቅም በመረዳት አንባቢ የመሆን አመለካከታቸው ሊያድግና ሊጠናከር ይችላል፡፡ ጋምብሪል (1996) እንዲሚገልፁት፣ ተማሪዎቻቸው ፈላስፋ፣ ተማራማሪ፣ ደራሲና ሐያሲ እንደሚሆኑላቸው የሚመኙ መምህራን እነሱም ተፈላሳፊ፣ ተመራማሪ፣ ተባባሪ፣ አንባቢ፣ ፀሐፊና ገምጋሚ መሆን አለባቸው፡፡
በተመሳሳይ ራስኒስኪና ፓዳክ (2000) እንዳመለከቱት ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከት አዎንታዊ እንዲሆን የሚፈልጉ መምህራን እነዚህን አራት ጠቃሚ ዕምነቶች አዋህደው መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነሱም(1) ሁሉም ተማሪዎቻቸው ለመማር እንደሚፈልጉ ተስፋ ማድረግ፤(2) ተማሪዎች ወደ መማሪያ ክፍል ይዘዋቸው የሚመጡትን ከማንበብ ጋር የተያያዙ ነገሮች ትኩረት መስጠት፤(3) ተማሪዎች በንባብ ትምህርት ተግባራት ከማይተገብሩት ይልቅ የሚተገብሩትን ተግባር በትኩረት መቃኘት፤(4) በተማሪዎች ፍላጎትና ጠቀሜታ ላይ ተመስርቶ የተቃኘ ማስተማር፣ መማርን ቀላል  እንደሚያደርገው ማመን ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በምርምሮቹ እንደተገለፀው የማንበብ አመለካከት ለተማሪዎች የማንበብ አመለካከት ሚናው የጎላ ነው፡፡ መምህራንና ወላጆች አዘውትረው ለማንበብ ያላቸው አመለካከት አሉታዊ ከሆነ ተማሪዎችም ለማንበብ ያላቸው አመለካከት እየቀነሰ ይሄዳል፡፡


ምሥጋና
ጥናቴን ስጀምር የመረጥኩትን ርዕስ ፈር ያስያዘልኝ፣ መረጃ በመስጠት ርዕሰ ጉዳዩ በድረ ገፅና በማጣቀሻ መፃሕፍት እንዲዳብር ያደረገልኝ፣ ከማይሰስተው ዕውቀቱና ካዳበረው ልምዱ ጠቃሚውን ሁሉ ያካፈለኝ፣ የጐበጠውን እያቃና ጥናቴን መልክ ያስያዘልኝ አማካሪየን ተባባሪ ፕሮፌሰር ማረው ዓለሙን ከልብ በመነጨ ስሜት አመሰግናለሁ፡፡
ወንድሜ ዶክተር ጀማል መሐመድ የሕይወቴ ውጥን አሁን ያለሁበት ድረስ ዳር እስከ ዳር እንዲዘልቀና መስመር እንዲይዝ ላደረግከው ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ አንተ ብቻ ሳትሆን ባለቤትህ  ወ/ሮ ዘላለም ጌታቸው የኔን  ዝንባሌና ፍላጎት ለማሳካት ያደረገችውን በጐ ነገር አልዘነጋውም፡፡ ያለናንተ እገዛ ሕልሜ ዕውን አይሆንም ነበርና ምስጋናየ የላቀ ነው፡፡ ፡
ሌላው የማመሰግነው የአማራ ክልል ብዙሐን መገናኛ ድርጅትን ነው፡፡ የትምህርት ጥማቴን በመረዳት የመማር ዕድሉን ሲሰጠኝ ቀለብ እንዳይቸግረኝ የወር ደመወዜን፣ የትምህርት ክፍያ እንዳላጣ የወሰነ ትምህርት ክፍያየን፣ ለጥናትና ምርምሬ የሚሆን ገንዘብና ጋዜጠኛ ጓደኞቼ አይዞህ በርታ ስላላችሁኝ የጀመርኩት እንዲጠናቀቅ አግዞኛል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ እንቅፋት ስለሚበዛብኝ  ወደ ዓላማየ ቶሎ ለመድረስ አልችልም ነበር፡፡
ይህንን ጥናት ሳከናውን የምፅፈው በዕጄ ቢሆን ኖሮ መሰረዝና መደለዙ አቅሜን ተፈታትኖት ድካም ባዛለኝ ነበር፡፡ ጊዜና ገንዘብም በትንሹ አይበቃኝም ነበር፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን እህቴ ረቂቅ ዳኜ (ሉባባ) የሰጠሽኝ ኮምፒዩተር የጉልበቴን ድካም፣ የጊዜየን መባከንና የገንዘቤን ወጭ ቆጥቦልኛል፡፡ በዕውነት እልሻለሁ ሉባባ በእኔ ዕጅ ልፃፈው እንጅ ተያቢዋ አንችው ነሽ፡፡    
አጐቴ ይመር መሐመድና  ባለቤቱ ወ/ሮ ዘነበች ዓሊ አፈሩን ገለባ ያድርግላችሁና ሞት ስለቀደማችሁ የውጥኔን መቋጫ ለመመልከት ባትበቁም ከልጅነት እስከ አዋቂነት ዕድሜየ ስንቅ የሆነኝ የናንተ ፀሎት፣ ምክርና ድጋፍ ነበር፡፡ እኔም ምክራችሁን ሰምቼ፣ ስንቃችሁን በልቼ ይኸው ድረስ ካላችሁብኝ ቦታ ደርሻለሁ፡፡ የናንተን ውለታ የምከፍለውም በዓላማየ ስኬት ነውና አደራችሁን አልበላሁም፡፡
                                                 



የይዘት ማውጫ
ምስጋና--------------------------------------------------------------------------------------------------
የይዘት ማውጫ-----------------------------------------------------------------------------------------
የሰንጠረዥ ማውጫ------------------------------------------------------------------------------------
አህፅሮተ ጥናት(አጠቃሎ)-------------------------------------------------------------------------------
ምዕራፍ አንድ፡- መግቢያ
1.1  .የጥናቱ ዳራ-------------------------------------------------------------------------------------
1.2  .የጥናቱ መነሻ ችግር---------------------------------------------------------------------------
1.3  .የጥናቱ ዓላማ----------------------------------------------------------------------------------
1.4  .የጥናቱ አስፋላጊነት----------------------------------------------------------------------------
1.5  .የጥናቱ ወሰን-----------------------------------------------------------------------------------
1.6  .የጥናቱ ውስንነት------------------------------------------------------------------------------
1.7 .የቁልፍ ቃላትና የፅንሰ ሐሳቦች አጠቃቀም ብያኔ-----------------------------------------
ምዕራፍ ሁለት፡- ክለሳ ድርሳን
2.1. አመለካከትና የማንበብ አመለካከት ግንኙነት-----------------------------------------------
2.2. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የማንበብ አመለካከት-----------------------
2.3. የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ-------------------------------
2.4. የማንበብ አመለካከት አንብቦ ለመረዳት ያለው ሚና--------------------------------------
 ምዕራፍ ሶስት፡- የአጠናን ዘዴ
3.1. የጥናቱ ተሳታፊዎች---------------------------------------------------------------------------
3.2. የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች------------------------------------------------------------
  3.2.1. መጠይቅ-----------------------------------------------------------------------------------
  3.2.2. ፈተና---------------------------------------------------------------------------------------
3.3. የመረጃ አተናተን ዘዴ
ምዕራፍ አራት፡- የውጤት ትንተናና ማብራሪያ
4.1.የውጤት ትንተና ------------------------------------------------------------------------------
4.2.የውጤት ማብራሪያ ----------------------------------------------------------------------------


ምዕራፍ አምስት፡- ማጠቃለያ፣ መደምደሚያና መፍትሔ
5.1. ማጠቃለያ---------------------------------------------------------------------------------------
5.2. መደምደሚያ------------------------------------------------------------------------------------
5.3. መፍትሔ----------------------------------------------------------------------------------------
ዋቢዎች--------------------------------------------------------------------------------
አባሪዎች-------------------------------------------------------------------------------
 ሀ.መጠይቅ -----------------------------------------------------------------------------------------
 ለ.ፈተና ---------------------------------------------------------------------------------------------
 ሐ.የትንተና መረጃ ---------------------------------------------------------------------
ማረጋገጫ ----------------------------------------------------------------------- 











የሰንጠረዥ ማውጫ
ሠንጠረዥ 1 -------------------------------------------------------
ሠንጠረዥ 2 ----------------------------------------------------------
ሠንጠረዥ 3 ------------------------------------------------------------












አህፅሮተ ጥናት
የጥናቱ ዋና ዓላማ የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት ከአንብቦ መረዳት ችሎታ ጋር ያለውን ተዛምዶ መመርመር ነው፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በባሕርዳር ከተማ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በ2004 ዓ.ም. በመማር ላይ የነበሩ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ፣ በቀላል የዕጣ ንሞና ዘዴ የተመረጡ 294 ተማሪዎች በናሙናነት ተወስደዋል፡፡ ለጥናቱ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች በመጠይቅና በፈተና ተሰብስበዋል፡፡ የተሰበሰቡት መረጃዎች በፒርሰን የተዛምዶ ስሌት ቀመር፣ በቀላል ድሕረት ትንተና እንዲሁም በሁለት ናሙናዎች ቲ-ቴስት ስትታስቲካዊ ዘዴዎች ተተንትነው ተብራርተዋል፡፡ በትንተናው መሠረት በማንበብ አመለካከትና በአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ (r=0.053፣ P>0.05) አልታየም፡፡ ይህም የማንበብ አመለካከት ቢጨምርም ቢቀንስም በአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለመኖሩን አመላክቷል፡፡ በጥናቱ የማንበብ አመለካከት አንብቦ የመረዳት ችሎታ ውጤትን ለመተንበይ ያስችል እንደሆን ተመርምሮ ጉልህ የሆነ አስተዋፅኦ (R²=0.003፣ F=0.762, P>0.05) እንደሌለው ተገልጧል፡፡ ከፆታ አንፃር የማንበብ አመለካከት ከአንብቦ የመረዳት ችሎታ ጋር  ተነፃፅሯል፡፡ በዚህም በሁለቱ ፆታዎች መካከል ጉልህ ልዩነት ያልታየ ሲሆን፣ በማንበብ አመለካከትና አንብቦ በመረዳት ችሎታ ሴቶች ከወንዶች የተሸሉ ቢሆንም ልዩነቱ ጉልህ አይደለም፡፡ በመሆኑም መምህራን የትምርት ተመራማሪዎችና ወላጆች እንዲሁም ትምህርትን ከማቀድ እስከ መተግበር ድረስ ባሉት ሂደቶች የሚሳተፉ ሁሉ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታ ጋር በማዛመድ ከመጠቀም ይልቅ ሌሎች ዘዴዎችን ለምሳሌ የማንበብ ተነሳሽነትን ዘዴ እንዲተገብሩ አጥኝው ይጠቁማል፡፡     
    










በባሕር ዳር ከተማ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ

በ ሐሰን መሐመድ ሐሰን

አማርኛ ትምህርት ፕሮግራም
ሒውማኒቲስ ፋካልቲ
ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ


ሰኔ - 2004 ዓ.ም.

የውጤት ትንተናና ማብራሪያ በ ሐሰን መሐመድ ሐሰን


ምዕራፍ አራት፡- የውጤት ትንተናና ማብራሪያ
ጥናቱ ዓላማ አድርጐ የተነሳው በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትናአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለውን ተዛምዶ ለመመርመር ነው፡፡ ለዚህም እንዲረዳ በመጠይቅ አማካኝነት የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት፣ በአንብቦ የመረዳት ፈተና ደግሞ የተማሪዎችአንብቦ መረዳት ችሎታ ውጤት በመረጃነት ተሰብስቧል፡፡ ስለዚህ የጥናቱ ትኩረት የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ በመፈተሽ የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት አቅጣጫ ለማመልከት ነው፡፡ በዚህ ላይ የተመሰረቱት የጥናቱ ውጤት ትንተናና የውጤቱ ማብራሪያ በቅደም ተከተል እንደሚከተለው ቀርበዋል::
4.1.የውጤት ትንተና  
የጥናቱ የመጀመሪያው መሪ ጥያቄ "በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ አለ?" የሚል ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ በፒርሰን የተዛምዶ መወሰኛ ቀመር ተሰልቷል፡፡ ውጤቱም ቀጥሎ በሰንጠረዥ 1 ተመልክቷል፡፡
ሠንጠረዥ 1፣የማንበብ አመለለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ በፒርሰን የተዛምዶ መወሰኛ ቀመር፡፡
ተላውጦ
የናሙና ብዛት
አማካይ ውጤት
መደበኛ   ልይይት
ተዛምዶ
1
2
1.  የማንበብ አመለካከት
2.  የአንብቦ መረዳት ችሎታ 
270
85.49
59.30
11.86
14.50
1.00
0.053*

1.00
                                  የጉልሕነት ደረጃ P>0.05*
በሠንጠረዥ 1 ላይ ለማየት እንደሚቻለው የተማሪዎቹ የማንበብ አመለካከት አማካይ ውጤት ከሚጠበቀው ውጤት (72) ከፍ ያለ (85.49) ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የአንብቦ መረዳት ችሎታቸውም ከሚጠበቀው አማካይ ውጤት (50) በላይ (59.30) ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ነገር ግን በማንበብ አመለካከትና በአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል የታየው ተዛምዶ (r=0.053,P>0.05) ቢሆንም ጉልህ ግን አይደለም፡፡ በተላውጦዎቹ መካከል የታየው የተዛምዶ መጠን የጋራ ባሕሪ በመቶኛ ሲሰላ ከአንድ በታች (0.28%) ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት በሁለቱ ተላውጦዎች መካከል ያለው ተዛምዶ በጣም ዝቅተኛ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይህም የማንበብ አመለካከት መኖር ወይም አለመኖር ከአንብቦ መረዳት ችሎታ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፤ ቢኖርም በጣም አነስተኛ ነው ለማለት የሚያስችል ይመስላል፡፡
በመቀጠልም የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታቸውን የመተንበይ ጉልህ ድርሻ ይኖረው ወይም አይኖረው እንደሆን ለመለየት ትንተና ተደርጓል፡፡ ለዚህም የጥናቱ መሠረታዊ ጥያቄ "የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታቸውን የመተንበይ ድርሻው ምን ያህል ነው?" የሚል ሲሆን፣ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የቀላል ድኅረት ትንተና (Simple Regression) ተደርጓል፡፡ ውጤቱም በሰንጠረዥ 2 ላይ እንደሚከተለው ተመልክቷል፡፡
ሠንጠረዥ 2፣ የማንበብ አመለካከት አንብቦ የመረዳት ችሎታን የመተንበይ ድርሻ በቀላል ድኅረት ትንተና (Simple Regression)

ተላውጦ
የተጋርቶ መጠን
ድኅረታዊ መጣኝ
Coefficient
መደበኛ ድኀረታዊ መጣኝ
Beta (β)
የቲ- ዋጋ
T- Statstics
የስሕተት ይሁንታ
Significance
የማንበብ አመለካከት
0.003
0.065
0.053
0.873
0.383
ጥገኛ ተላጦ = የአንብቦ መረዳት ችሎታ ውጤት
የሠንጠረዥ 2 የቀላል ድኅረት ትንተና (Simple Regression) ውጤት እንደሚያመለክተው የማንበብ አመለካከት በአንብቦ የመረዳት ችሎታ ላይ ያለው ድርሻ (R² = 0.003፣ F=0.762፣ P>0.05) ጉልህ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ይህም ተላውጦው በተማሪዎች የአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ጉልህ ድርሻ ወይም አስተዋፅኦ እንደሌለው ያመለክታል፡፡ ወይም ደግሞ የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት መኖር ወይም አለመኖር በአንብቦ መረዳት ውጤታቸው ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ አይኖርም ማለት ነው፡፡
ተላውጦው በአንብቦ የመረዳት ችሎታ ላይ ያለው ቀጥተኛ ተፅዕኖ ወይም ድርሻ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ በመደበኛ ድህረታዊ መጣኝ (Beta Coefficient) ተሰልቷል፡፡ በዚሁ መሰረት የማንበብ አመለካከት በአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ያለው ተፅዕኖ (β = 0.053፣ t = 0.873፣ P>0.05) ሲሆን፣ ይህም የማንበብ አመለካከት በአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ጉልህ ድርሻ እንደሌለው ያመለክታል፡፡ ከዚህም በመነሳት የማንበብ አመለካከት በአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በጣም አነስተኛ ነው ወይም ጭራሹኑ የለም ለማለት ይቻላል፡፡
ከሠንጠረዥ 2 ለመረዳት እንደሚቻለው በዚህ የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት ድርሻ በአንብቦ መረዳት ላይ የተጋርቶ መጠን መለኪያ (Coefficient of Detrmination) R²=0.003 ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የማንበብ አመለካከት ከአንብቦ መረዳት ችሎታ ጋር 0.3% የልይይት መጠን ይጋራሉ ወይም የማንበብ አመለካከት በአንብቦ የመረዳት ችሎታ ውጤት ላይ በዚህ ልክ ተፅዕኖ አሳድሯል ለማለት ይቻላል፡፡
የዚህ ጥናት ሶስተኛ መሠረታዊ ጥያቄ "በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በፆታ ልዩነት ያሳያል?" የሚል ሲሆን፣ ይህንን ለመመለስ ባለሁለት ናሙና ቲ-ቴስት ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ውጤቱም እንደሚከተለው በሰንጠረዥ 3 ቀርቧል፡፡
ሠንጠረዥ 3፣ የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ በፆታ (በባለሁለት ናሙና ቲ-ቴስት)

ተላውጦ

ፆታ
የተሳታፊ ብዛት
270
አማካይ ውጤት
መደበኛ ልይይት
(SD)
የነፃነት ደረጃ
(df)
የቲ-ዋጋ
(t-test)
የይሁንታ
ስህተት
(Sig.)
የማንበብ አመለካከት

ወንድ

129
84.75
12.32



268


-1.011
0.313
አንብቦ መረዳት
58.84
14.48
- 0.496
0.620
የማንበብ አመለካከት

ሴት

141
86.22
11.50
-1.011
0.313
አንብቦ መረዳት
59.72
14.62
-0.496
0.620
ሰንጠረዥ 3 እንደሚያመለክተው የወንድ ተማሪዎች የማንበብ አመለካከት አማካይ ውጤት (84.75) ከሴቶቹ አማካይ የማንበብ አመለካከት ውጤት (86.22) ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የወንዶች መደበኛ ልይይት (12.32) ከሴቶች መደበኛ ልይይት (14.48) ዝቅ ያለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህም ሴት ተማሪዎች ከወንድ ተማሪዎች የተሻለ የማንበብ አመለካከት ቢያሳዩም (t = -1.011፣ df = 268፣ P=0.313) ልዩነቱ የቲ-ዋጋ ግን ጉልህ ባለመሆኑ ልዩነት አላቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡
በተጨማሪም የተማሪዎቹን የአንብቦ መረዳት ችሎታ (ከሰንጠረዥ 3 ለመገንዘብ እንደሚቻለው) የወንድ ተማሪዎች አንብቦ የመረዳት ችሎታ አማካይ ውጤት ከሴቶቹ ዝቅ ብሎ (58.84) የተገኘ ሲሆን፣ የሴቶቹ ተማሪዎች የአንብቦ መረዳት ችሎታ ከወንዶቹ በልጦ (59.72) ተገኝቷል፡፡ መደበኛ የልይይት መጠናቸው የወንዶቹ (11.50) ሲሆን፣ የሴቶቹ ደግሞ (14.62) መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህም በአንብቦ መረዳት ችሎታ ከወንዶቹ ይልቅ ሴቶቹ ተማሪዎች (t= -0.496 df = 268፣ P= 0.620) የተሻለ ልዩት እንዳላቸው ቢያመለክትም ልዩነቱ የቲ-ዋጋ ጉልህ ባለመሆኑ የጎላ ልዩነት አላቸው ለማለት አያስችልም፡፡
በአጠቃላይ የውጤት ትንተናው እንዳመለከተው የጥናቱን ዓላማ ከግቡ ለማድረስ  በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና አንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለውን ተዛምዶ ለመመርመር ተችሏል፡፡ በጥናቱ ለተነሱት ሶስት ጥያቄዎችም መልስ ተገኝቷል፡፡ በዚህም በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ የለም፡፡ የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታቸውን የመተንበይ ድርሻ የለውም፡፡ እንዲሁም በማንበብ አመለካከትና በአንብቦ መረዳት ችሎታ ከወንድ ተማሪዎች ይልቅ ሴት ተማሪዎች የተሻሉ ቢሆንም ልዩነቱ ጉልህ አለመሆኑ በስታስቲክስ ተገልጧል፡፡
  4.2. የውጤት ማብራሪያ
የዚህ ጥናት ትኩረት በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ መካከል ያለውን ተዛምዶ ይመለከታል፡፡ ስለዚህም በመጠይቅና በፈተና በተሰበሰቡ መረጃዎች አማካኝነት የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት አንብቦ ከመረዳት ችሎታቸው ጋር ያላቸው ተዛምዶ በንፅፅር ታይቷል፡፡ የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታን የመተንበይ ጉልህ ድርሻ በፆታ ልዩነት ያሳይ ወይም አያሳይ እንደሆን ለመፈተሽ በተለያዩ ገላጭና ተንባይ ስታትስቲክሶች ተተንትኗል፡፡
በሰንጠረዥ 1 ላይ እንደሚታየው ይህ የተማሪዎቹ አማካይ የማንበብ አመለካከት አማካይ ውጤት መጠን (85.49) ከአንበቦ መረዳት ውጤታቸው አማካይ ውጤት (59.30) አንፃር ሲታይ (r=0.053፣ P>0.05) ተለዋዋጮቹ የሚጋሩት የጋራ ባሕሪ (0.28%) በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ በማንበብ አመለካከትና በአንብቦ መረዳት መካከል ተዛምዶ አልታየም፡፡ ከዚህ በመነሳት ተማሪዎቹ ከፍተኛ የሆነ የማንበብ አመለካከት ቢኖራቸውም የአንብቦ መረዳት ችሎታቸው ግን አነስተኛ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ተማሪዎቹ ከፍተኛ የሆነ የማንበብ አመለካከት እያላቸው በአንብቦ መረዳት ችሎታቸው ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡበት ምክንያት ምናልባት ተማሪዎቹ የቀረበላቸውን ንባብ በግልፅና በትክክል አለመረዳት ሊሆን ይችላል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎቹ የንባቡን ይዘት፣ መዋቅርና ቴክስት የመተቸት ብቃታቸው አናሳ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህም ምክንያት  በሳላበስ (2008)፣ በፒትስቸር (2010) በናንሲ (1989) ጥናት ከተገለጠው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል ግን የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት ከአንብቦ የመረዳት ችሎታ ጋር ተዛምዶ አለመኖር አቡ-ራቢያ (1996) የቴክስቱ ይዘት ሳይሆን የቴክስቱ ቋንቋ አንብቦ ለመረዳት ተፅዕኖ አሳድሯል ግሪአኒ (1987) የመኖሪያ አካባቢና የማንበቢያ ትርፍ ጊዜ ተዛምዶ አላቸው፤  ቡክሆረስት-ሄንግና ፔሪራ (2008) ትርፍ ጊዜን በንባብ ተግባር ላይ አለማዋል በማንበብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል በሚል ከደረሱበት ድምዳሜ ጋር ተደጋጋፊ አይደለም፡፡ በተጨማሪም የምርምሮቹ ውጤቶች ያልተደጋገፉበት ምክንያት ምርምሮቹ የተካሄዱት በተለያዩ አካባቢዎችና የተለያዩ ባሕላዊ ዳራ ባላቸው ተማሪዎች በመሆኑ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
በትንተናው ለማሳየት እንደተሞከረው ጥናቱ ትኩረት ያደረገበት ሌላው ጉዳይ የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታን  በመተንበይ ረገድ የሚኖረውን ጉልህ ድርሻ ይመለከታል፡፡ በሰንጠረዥ 2 ላይ እንደተመለከተው  የማንበብ አመለካከት በአንብቦ የመረዳት ችሎታ ላይ ያለው ድርሻ (R² = 0.003፣ F = 0.762፣ P>0.05) ሲሆን፣ ይህም ተለዋዋጩ በተማሪዎች የአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ጉልህ ድርሻ ወይም አስተዋፅኦ እንደሌለው ያመለክታል፡፡ ከዚህ ባሻገር የማንበብ አመለካከት በአንብቦ የመረዳት ችሎታ ላይ ያለው ድርሻ (β = 0.053፣ t = 0.873፣ P>0.05) ሲሆን፣ ይህም የማንበብ አመለካከት አንብቦ የመረዳት ችሎታ ድርሻ እንደሌለው ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም በማንበብ አመለካከትነ አንብቦ የመረዳት ችሎታ የተጋርቶ መጠን መለኪያ R² (Coefficient of Detrmination) R² = 0.003 ወይም 0.3% ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት የማንበብ አመለካከት ከአንብቦ የመረዳት ችሎታ ጋር 0.3% የልይይት መጠን ይጋራሉ ወይም በአንብቦ የመረዳት ችሎታ ላይ በዚህ ልክ ተፅዕኖ አሳድሯል ለማለት ይቻላል፡፡ ከጥናቱ ውጤት ለመረዳት እንደሚቻለው የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታን ለመተንበይ ያልቻለበት ምክንያት ተለዋዋጮቹ ተዛምዶ ስለሌላቸው ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ የዚህ ጥናት ውጤት የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታን የመተበይ ጉልህ ድርሻ አለው ከሚለው ከዴይና ባምፎርድ (1982) ከኮንሊ (1992) ከአሌክሳንደርና ፊለር (1992) ከሮኢና ስሚዝ (2005) የምርምር ግኝቶች ጋር ሲቃረን፤ የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታን የመተንበይ ድርሻው የጎላ አይደለም ከሚሉት ከራንስበሪ (1973) ከሒዚግነቶንና አሌክሳንደር (1984) ከማና እና ማይሽፍ (1987) ከሞሪሰን፣ ጃኮብስና ስዊንያርድ (1999) ከአፕሊጌትና አፕሊጌት (2004) ከስችማይት (2009) የምርምር ግኝቶች ጋር ተደጋገፊነት አሳይቷል፡፡
በሠንጠረዥ 3 ላይ እንደተመለከተው የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ በፆታ ልዩነት እንዳለውና እንደሌለው የተደረገው የጥናት ውጤት ትንተና  እንዳመለከተው በማንበብ አመለካከት ሴት ተማሪዎች ከወንድ ተማሪዎች የተሻለ አመለካከት ቢታይባቸውም የቲ- ዋጋ ግን ጉልህ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በተመሳሳይም የሴት ተማሪዎች አንብቦ መረዳት ችሎታ ከወንድ አቻዎቻቸው በልጠው ቢገኙም የቲ- ዋጋ ልዩነቱ ጉልህ እንዳልሆነ ያመለክታል፡፡ በመጠይቅና በፈተና የተገኘው የጥናት ውጤት ከሊናና ካሪም (2007)፣ ከክሪስቲናና ጆናታን (2011)፣ ከዊዊ (2009)፣ ጥናት ጋር ሲደጋገፍ፤ ከናንሲ (1989) ጥናት ጋር በከፊል ይስማማል፡፡  ነገር ግን የጥናቱ ውጤት ከሳላበስ (2008)፣ ከባስ (2012)ና ከተራቪስ (2010)፣ የጥናት ውጤት ጋር አይደጋገፍም፡፡
ከጥናቱ ውጤትና ከክለሳ ድርሳን የተገኙት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ እንዳይጎለብት የሚያደርጉት ምክንያቶች አዎንታዊ የማንበብ አመለካከት እንዲዳብር ትኩረት ባለመሰጠቱ፣ መምህራን የበርካታ ተማሪዎቻቸውን የማንበብ አመለካከት ዝንባሌ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ማከናዎናቸው እንዲሁም ወላጆች ማንበብን የትርፍ ጊዜ ተግባር አድርገው መቁጠራቸው ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ከጥናቱ ውጤት ለመረዳት እንደሚቻለው የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ተዛምዶ የላቸውም፡፡ የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት አንብቦ የመረዳት ችሎታቸውን የመተንበይ ጉልህ ድርሻ የለውም፡፡ በማንበብ አመለካከት ሴት ተማሪዎች ከወንድ ተማሪዎች የተሻለ አመለካከት ታይቶባቸዋል፡፡ ልዩነቱ ጉልህ ባይሆንም የሴት ተማሪዎች አንብቦ የመረዳት ችሎታ ከወንድ አቻዎቻቸው ጋር ሲነፃፀር ብልጫ አለው፡፡ በአሌክሳንደርና ፊለር (1976)፣ ዊየርና ዊየር (1994)፣ በብሮምፊ (2004)፣ በማክኪና፣ ኪአርና ኢልስዋርዝ (1995)፣ በራሲኒስኪና ፓዳክ (2000) እንደተጠቆመው ለነዚህ የጥናት ውጤቶች ግኝት እንደ አሉታዊ ምክንያት የሚጠቀሱት የተማሪዎች የማንበብ አመለካከቶች ብቻ ሳይሆኑ መምህራን በትምህርት ቤት፣ ወላጆች በመኖሪያ ቤት እንዲሁም በአካባቢያቸው በማንበብ አመለካከታቸው ላይ ተፅዕኖ ስለሚያደርሱባቸው ሊሆን ይችላል፡፡










ምዕራፍ አምስት፡- ማጠቃለያ፣ መደምደሚያና መፍትሔ
የጥናቱ መግቢያ፣ ከጥናቱ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ክለሳ ድርሳናት፣ የአጠናን ዘዴና የጥናቱ ውጤት ትንተናና ማብራሪያ በቅደም ተከተላቸው መሠረት ያለፉት ምዕራፎች የትኩረት ነጥቦች ነበሩ፡፡ በዚህ ምዕራፍ ደግሞ ማጠቃለያ፣ መደምደሚያና የመፍትሔ ሐሳቦች ይቀርባሉ፡፡
5.1. ማጠቃለያ
የጥናቱ ዋና ዓላማ የተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶን መመርመር መሆኑ በቀዳሚዎቹ ምዕራፎች ተገልጧል፡፡ በዚህም መሠረት በጥናቱ መልስ እንዲገኝባቸው የተነሱት መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚከተሉት ነበሩ፡፡ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች፡-
1.  በማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ አለ?
2.  የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታቸውን የመተንበይ ድርሻው ምን ያህል ነው?
3.  በማንበብ አመለካከትና በአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በፆታ ልዩነት ያሳያል? የሚሉ ናቸው፡፡
ከላይ የቀረቡትን መሠረታዊ ጥያቄዎች በአስተማማኝነት ምላሽ ለመስጠት እንዲቻልም መጠይቅና ፈተና በመረጃ መሰብሰቢያነት ተመርጠዋል፡፡ ለጥናቱ በሚመች መልኩም ተዘጋጅተዋል፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በባሕር ዳር ከተማ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2004 ዓ.ም. የ10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ተማሪዎቹ የተመረጡት ከዕድል ሰጭ የንሞና ዘዴ ውስጥ በቀላል የዕጣ ንሞና አመራረጥ ዘዴ (simple random Sampling) ነው፡፡ ብዛታቸውም 270 ነበር፡፡ በጥናቱ ዋነኛው የመረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያ መጠይቅ ሲሆን የተማሪዎች የአንብቦ መረዳት ችሎታ ውጤትም በፈተና አማካኝነት ተገኝቷል፡፡ በመጠይቁ የተካተቱት 25 ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እነዚህም በመስኩ በተለያዩ ጊዚያት ምርምሮችን ያካሄዱት ሮዲና አሌክሳንደር (1980) ካዘጋጁት መጠይቅ የተውጣጡ ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹን ለጥናቱ በሚያመች መልኩ ወደ አማርኛ አሻሽሎ በመተርጎም የማንበብ አመለካከትን እንዲለኩ ተዘጋጅተው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡
የፅሁፍ መጠይቁ የአማካሪ ማስተካከያ ታክሎበትና በሙከራ ጥናት ተፈትሾ አስተማማኝ ሆኖ በመገኘቱ ለጥናቱ የሚፈለጉት መረጃዎች ተሰብስበውበታል፡፡ የአንብቦ መረዳት ፈተና ጥያቄዎቹም በአማካሪውና በአማርኛ መምህር ማስተካከያ ተደርጎባቸው በሙከራ ጥናት ተፈትሸው አስተማማኝ ሆነው በመገኘታቸው የጥናቱ ተሳታፊ ተማሪዎችን የአንብቦ መረዳት ችሎታ ለመለካት ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ በመጠይቅና በፈተና የተሰበሰቡት መረጃዎችም የተለያዩ ገላጭና ተንባይ ስታስቲካዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ተተንትነዋል፡፡

በመጠይቅ አማካኝነት የተሰበሰበውን መረጃ መሠረት በማድረግ የመጀመሪያው መሪ ጥያቄ  በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ አለ? የሚለው ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር የማንበብ አመለካከት ከአንብቦ መረዳት ችሎታ ጋር ተዛምዶ እንደሌለው የትንተናው ውጤት አመልክቷል፡፡  

በሁለተኛ ደረጃም የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታቸውን የመተንበይ ድርሻው ምን ያህል ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በተደረገው ጥረት ቀላል የድኅረት ትንተና ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በትንተናው መሠረትም የማንበብ አመለካከት በአንብቦ የመረዳት ችሎታ ላይ ያለው ድርሻ (R² = 0.003፣ F = 0.762፣ P>0.05) ሲሆን፣ ይህም ተለዋዋጩ በተማሪዎች የአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ጉልህ ድርሻ ወይም አስተዋፅኦ እንደሌለው አመልክቷል፡፡ (Beta Coefficient) ተሰልቶ የተገኘው ውጤት እንዳመለከተው ደግሞ የማንበብ አመለካከት በአንብቦ የመረዳት ችሎታ ላይ ያለው ድርሻ ተንባይ አለመሆኑን ነው፡፡ በተጨማሪም የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ በስታትስቲክስ ጉልህ ድርሻ የለውም፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተመረመረው መሠረታዊ ጥያቄ  በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በፆታ ልዩነት ያሳያል? የሚለው ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ሴት ተማሪዎች ለማንበብ ያላቸው አመለካከት በአማካይ ውጤት ከወንድ ተማሪዎች አማካይ ውጤት በስታትስቲክስ ጉልህ ብልጫ ቢያሳይም ልዩነቱ ጉልህ ባለመሆኑ የጎላ ልዩነት አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሴቶቹ አንብቦ የመረዳት ችሎታ ከወንዶቹ በስታትስቲክስ ጉልህ ብልጫ ቢያሳይም ልዩነቱ ጉልህ ባለመሆኑ ልዩነት አለ ለማለት አይቻልም፡፡

በአጠቃላይ የጥናቱ ትንተና ውጤት እንዳመለከተው የተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ የላቸውም፡፡ የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታን የመተንበይ ድርሻው ጉልህ አይደለም፡፡ በተጨማሪም የሴቶች የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ በስታትስቲክስ ከወንዶቹ ተማሪዎች ብልጫ እንዳለው ቢያሳይም ልዩነቱ ጉልህ ባለመሆኑ ልዩነት አለው ለማለት አያስደፍርም ፡፡
5.2. መደምደሚያ
የጥናቱን ትንተናና ማብራሪያ መሠረት በማድረግ ከሚከተሉት መደምደሚያዎች ላይ ተደርሷል፡፡
1.  በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ተዛምዶ የለም፡፡
2.  የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታቸውን የመተንበይ ጉልህ ድርሻው ወይም አስተዋፅኦ የለውም፡፡
3.  የማንበብ አመለካከት የአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ በስታትስቲክስ ጉልህ ድርሻ የለውም፡፡
4.  በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በፆታ ልዩነት ቢያሳያይም ልዩነቱ ጉልህ ባለመሆኑ ልዩነት አለ ለማለት አያስችልም፡፡
5.3.መፍትሔ
በዚህ ጥናት የተደረሰባቸውን ግኝቶችና ውጤቶች ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከት ለማጐልበት እንዲቻል የሚከተሉት መፍትሔዎች ተጠቁመዋል፡-
  1. በጥናቱ የተማሪዎች የማንበብ አመለካከት በአንብቦ የመረዳት ችሎታ ያለውን የትንበያ መጠን መገንዘብ ስለተቻለ መምህራኑ ይህንኑ በመረዳት የመማሪያ ክፍል የትምህርት አቀራረባቸው የማንበብ አመለካከትን የሚያሳድግ ብቻ  ሳይሆን  ሌሎችንም ዘዴዎች በአማራጭነት  ቢጠቀሙ፡፡
  2. ጥናቱ በተማሪዎች የማንበብ አመለካከትና የአንብቦ መረዳት ችሎታ መካከል ያለው ተዛምዶ በፆታ ልዩነት እንዳለው ስለሚያሳይ ወላጆች የልጆቻቸውን የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ በመገንዘብ ለችግሮቻቸው ከመምህራን ጋር በመተባበር መፍትሄ ቢፈልጉ፡፡
3.  የትምህርት ባለሙያዎች በጥናቱ ግኝቶች መረጃ መሠረት የተማሪዎችን የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ በመገንዘብ መምህራን የትምህርት ዕቅድ፣ መርሐ ትምህርትና የንባብ ትምህርት መርሐ ግብር ሲያዘጋጁ የተማሪዎቹን የማንበብ አመለካከትና አንብቦ የመረዳት ችሎታ ከማጎልበት አንፃር እንዲመለከቱት ቢጠቁሙ፡፡
4.  በርዕሱ ዙሪያ ተጨማሪ ጥናት የሚያደርጉ ተመራማሪዎች ይህንን ጥናት እንደ መነሻ በማድረግ ከዚህ የተሻለ ጥናት ለማካሄድ ጥረት ቢያደርጉ፡፡ የሚሉት በአጥኝው የቀረቡ የመፍትሄ ሐሳቦች ናቸው፡፡











ዋቢዎች
መሐመድ ዓሊ፡፡ (1992 ዓ.ም)፡፡ ‘‘በባሕር ዳር ከተማ የግዩን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች የአማርኛ ቋንቋን ለመማር ያላቸው አመለካከት፡፡'' ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ የቀረበ ፅሁፍ፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ፡፡ (ያልታተመ)፡፡
መስፍን ኃብተማሪያም፡፡ (2001) የቡና ቤት ስዕሎችና ሌሎችም ወጐች (1976-1999)፡፡ ኤማይ ፕሪንተርስ ኃ.የተ.የግ.ማ፡፡ አዲስ አበባ፡፡
በዓሉ ግርማ፡፡ (2001)፡፡ የሕሊና ደወል፡፡ (2ኛ ዕትም)፡፡ ፋር ኢስት ትሬዲንግ፡፡ አዲስ አበባ፡፡
ባሕሩ ዘወዴ፡፡ (2001)፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983፡፡ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ፕሬስ፡፡ አዲስ አበባ፡፡ 
ታፈረ ወርቁ፡፡ (2000)፡፡ ‘‘በዳንግላ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች የንባብ ዳራና የአንብቦ መረዳት ችሎታ ተዛምዶ፡፡'' ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ የቀረበ ፅሁፍ፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ፡፡ (ያልታተመ)፡፡
ታዛሽ ሰይፉ፡፡ (1992 ዓ.ም)፡፡ ‘‘የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች የአንብቦ መረዳት ችሎታ፡፡'' ለመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ የቀረበ ፅሁፍ፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ፡፡ (ያልታተመ)፡፡
ደምሰው አሰፋ፡፡ (1995)፡፡ ‘‘በ10ኛ ክፍል የአማርኛ መማሪያ መፀሐፍ ውስጥ የሚገኙ ምንባቦች የተማሪዎችን የማንበብ ፍላጎት ለመያዝ ያላቸው ብቃት፡፡'' ለመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ የቀረበ ፅሁፍ፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ፡፡ (ያልታተመ)፡፡
ገደፋው አምሳሉ፡፡ (1993)፡፡ ‘‘የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች አማርኛ ቋንቋን ለመማር ያላቸው ተነሳሽነትና የትምህርት ውጤት ተዛምዶ፡፡'' ለመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ የቀረበ ፅሁፍ፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ፡፡ (ያልታተመ)፡፡
Abu-Rabia, S. (1996). Attitudes and cultural background and their relationship to reading comprehension in a second language: a comparison of three different social contexts. International Journal of Applied Linguistics, 6: 81–105. Doi: 10.1111/j.1473-4192.1996.tb00090.x
Aebersold, J.A., and Field, M.A. (1997). From Reader to Reading Teacher: Issues and strategies for second language classrooms. Cambridge Universty Press.
Alexander, J.E., and Filler, R.C. (1976). Attitudes and Reading. Newark., DE. International Reading Association.
Appllegate, A.J. and Appllegate, M.D. (2004). The Peter Effect: Reading Habits and Attitudes of Preservice Teachers. The Reading teacher, 57, 554-563.
Bas, G. (2012). Correlation between elementary students’ reading attitudes and their writing dispositions. IJGE: International Journal of Global Education - 2012, volume 1 issue 2.  Konya University. Graduate School of Education Sciences.   Konya, Turkey
Blackb, A. (2006). Attitudes to Reading: An Investigation across the Primary Years. Thesis.Master of Education, School of Education, Australian Catholic Universty.
Block, C.C. (1997). Teaching the Language Arts: Expanding Thinking through Student Centered Instruction .Boston: Allyn and Bacon.
Bokhorst-Heng, W. and Pereira, D. (2008), Non-at-risk adolescents' attitudes towards reading in a Singapore secondary school. Journal of Research in Reading, 31: 285–301. Doi: 10.1111/j.1467-9817.2008.00369.x
Christina, C. and Jonathan D. (2011). Young People's Reading and Writing: An In-Depth Study Focusing on Enjoyment, Behavior, Attitudes and Attainment. 2011-00-00.
Cramer, M. (1994). Fosternig the Love of reading: The Affective Domain in Reading Education (PP.74-87).Newyork, DE: International reading Association.
Day, R. and Bamford. (1998). Extensive Readng and In The Second Language Classroom. U.S.A : Cambridge Universty Press.
Dornyei, Z. (2001). Motivational Strategies in the Language Classroom. Cambridge: Cambridge Universty Press.
Dubin, B.V, and Zorkaia, N.A (2010). The changes in the attitude of Russia's Reading public interms of frequency and intensiveness. Russian Education and Society, v52n7 P16-51 Jul. 2010.
Eiser, J. R., (1994). Social Psychology. Attitudes, cognition and social behavior. Cambridge University Press.
Estes, T. H. (1971). A Scale to Measure Attitudes Toward Reading. Journal of reading. 15, 135-138.
Evans, K.M., (1965). Attitudes and Interests in Education. Routlege and Kegan private limited.
Feldman,R.S.,(1996). Understanding Psychology. (4th Ed). McGraw-Hill, Inc.
Feldman,R.S (1999). Understanding Psychology. (5th Ed). McGraw-Hill, Inc.
Frankel, J.R., and Wallen. (2000). How to design and Evaluate Research in education. (4th Ed). Mcgraw Hill.  
Flood J., and. Lapp, D., (1983). Teaching Reading to Every Child. (2nd Ed.). Macmillan publishing Co., Inc.
Gambrell, L.B.,(1996). Creating Classroom Cultures That Foster Reading Motivation. The Reading Teacher, 50, 14-25.
Graves, M.F., Laberge, M.J. and Cooke C. (1983). Efects of previewing difficult short stories on low ability junior high school students comprehension, recall and attitudes. Reading Research QuarterlyVol. 18, No. 3, spring, 1983  
Greaney, V. and Hegarty, M. (1987). Correlates of leisure-time reading. Journal of Research in Reading, 10: 3–20. Doi: 10.1111/j.1467-9817.1987.tb00278.x
Kulik, A.J. and Kulik C.C. (1982). Effects of Ability Grouping on Secondary School Students:  A Meta-analysis of Evaluation Findings. American Educational Research Journalaer.sagepub.com. Doi: 10.3102/00028312019003415. Am Educ Res J September 21, 1982 vol. 19 no. 3 415-428 University of Michigan.
Kush, J.C, and Watkins, M.W. (1996). Long –Term Stability of Children's Attitudes Toward Reading. [Eelectronic Version]. The Journal of Educational Reserch.
Heathington, B.S. and Alexander, J.E. (1984). Do Classroom Teachers Emphasize Attitudes Toward Reading?.The Reading Teacher, 37, 484-488.
Heaton, J.B. (1990). Writing English Language Test. London: Longman.
Heilman, A.W. Blair,T.R.,and Ruphley W.H. (1998). Principles and Practices of Teacing Reading. (9th Ed.).New Jersy prints Hall Inc.

 Lena S.and, Karin T. ( 2007). Influences of Family Based Prerequisites, Reading Attitudes, and Self-Regulation onReading Ability.Contemporary Educational Psychology, v32 n2 p206-230 Apr 2007 Journal of Atricles; Reports – Research.

 Logna, S., and Johnston, R. (2009). Gender Differences in Reading Ability and Attitudes: Examining where these differences Lie. Jornal of Research in Reading, V32 n2 P199-214 May 2009.
Lorene, W.C., (2010). ‘‘Secondary Students' Reading Attitudes and Achievement in a scaffold Silent Reading Program Versus Traditional Sustained Silent Reading.’’ ProQuest LLC, Ph.D.Dsessertaion, Auburn University.
Lynn, H.W. (2010). Difference between third, forth, and fifth Grade students' attitudes to ward reading in relation to community size. Master of education (MED), Bowling Green state Universty, reading 2010.
Madsons, H.S. (1983).Teachniques In Testing. Newyork: Oxford Universty Press.
Martinez, R.S., Tolga, A.o, and Jermy, J. (2008). Influence of Reading Attitude on Reading Achievement: A Test of the Temporal Interaction Model. Psychology in the schools, v45 n10 P1010-1022. Dec.2008.
May, B.F. (1990). Reading as Communication: An Interactive Approach. (3rd Ed.). U.S.A: Macmillan Publishing Company.
Mckenna, M.C., Kear, D.J., and Ellsworth, R.A., (1995). Children’s attitudes to woard reading.A national survey. Reading research quarterly. Retrieved on 01/08/2011 09:59. From http:// WWW.jstor. Org /stable/748205.
Muller, D.L., (1973). Teacher Attitude Towards reading. Journal of Reading. 17, 202-205.
Myers, G.D. (1999). Social Psychology. (6th Ed). The McGraw-Hill Componies, Inc.
Norton,D.E.(1997). The Effective Teaching of Language Arts. (5th Ed.).New Jersy: Prentice Hall Inc. 
Nancy,W.(1989).‘‘ Developmental relationships between Students’ attitudes Toward reading and Reading Achivement In Grades 1 through 8’’. Page 95, Education Specialist Thesis, Universty of Northen Iowa.
Ransbury, M.K. (1973). An Assesment of Reading Attitude. Journal of Reading, 17,25-28.
Rasinski, T., and Padak, N, (1996). Holistic Reading Strategies Teaching Children who Find  Reading Difficult. Prentice Hall, Inc.
 Roe, B.D., and Smith, S.H., (2005). Teaching reading in today's middle schools, Houghton Mifflin Company.
Rrowell, G.C., (1972). An Investigation of Factors Related to Change in Attitude Toward Reading. 972-73* Vol.5,No.4,Fall.
Sallabas, M.E., (2008). Relationship between 8th Grade Secondary School Students' Reading Attitudes and Reading Comprehension skills. Journal of the Faculty of Education. V01, 9, Issue.16 (fall 2008). 141-155. Retrived on http://WWW.web. Inonu. Edu.tr/ efdergi/ sayi 16/08-Rn.pdf.
Schmitt,E.(2009). ‘‘Four Case studies:The reading Attituds and Practices of Teachers and students Grade’’.Thesis,Master of Education in Reading,The graduate College of Bowling Green State Universty.
Skinner, C.E.,(1998). Educational Psychology. (4th Ed).  Prentice-Hall, Inc.

Spiegel, D.L. (1994). A Portrait of Parents of successful readers. In E.H.NewYork ,DE: International Reading association.

Thraves, P., (2010). "An Investigation into Students' Reading Attitudes and Habits Using a Children's Literature Intervention Programme" CPUT Thesis and Dissertations. Paper 296. http://dk.cput.ac.za/td_cput/296

 Theodore S.K. (2010). Reading Achievement, Attitudes towards, Reading and Reading Self-Esteem of  Historically Low Achieving  Students  Journal of Instructional Psychology, v37 n2 p184-188 Jun 2010.Journal Articls; Reports – Research.

 Vacca, R.T.And Vacca, J.L.,(1999). Content Area Reading Literacy and Learning across the Curriculum. (6th Ed). Long Man.
Webb, H.L., (2009). ‘‘The Relationship between African American Middle School Students' attitudes toward Reading and their Reading Comprehension Level’’.  Proquest LLC, Ed.D. Unpublished Dissertation, the University of Memphis.
Wie (Veronica) (2009). ‘‘Gender Difference in Reading Comprehension for Chinese Secondary School Students.’’ A Seminar Paper Research. Master of Science in Education. Unpublished Thesis. The Graduate Faculty Universty of Wisconsin-Platteville.
 Yaacov, P. (2010). A Meta- Analysis of the Relationship between Student Attitudes towards Reading and Achievement in Reading. Journal of Research in Reading, v33 n4 P335-355 Nov 2010.
Zelalem Berhanu. (2010). ‘‘The Reading Attitudes Preferences and Habits of First Year Bahir Dar Universty Studentes with Particular Reference To The faculty of Humanities.’’  Unpublished Master’s Thesis. Humanities Faculty, Bahir Dar Universty.